መዘክርነቱ ታሪኩን ለማስታወስ ብቻ ሳይሆን በባህላችን ውስጥ ሥሩን ሰዶ ቤተኛ በመሆን ላለፉት ድፍን መቶ ዓመታት ሲታወስ ኖሯል:: ለካንስ አንድ ድርጊት ታሪክ ተብሎ የሚወራለት፣ የሚተረክለትና የሚጻፍለት ውሎ አድሮ በክዋኔው ውስጥ በሚበቅለው ባህል ጭምር ስለሚደገፍ ኖሯል:: የታሪክ ዘርፍ ተመራማሪዎች አንድን ታሪክ አስታከው የሚወለዱ ባህሎችን ጉዳይ በተመለከተ የሰለጠኑባቸውንና የጻፏቸውን መጻሕፍት እያጣቀሱ ጀባ ቢሉን ለእውቀትም “ለድነትም” ሊያግዘን ይችላል::
መስከረም ሲጠባ፤ ኅዳር ሲታጠን፣
አልክልሻለሁ ልቤን በሣጥን::
በማለት ያንጎራገረውን የፍቅር ርሃብተኛ “አባ በሉ” – “ረ እንዴት ነህ!” ብዬ በማስታወስና ክረምቱን በደህና ስላሸጋገረው ምኞቴን ገልጬለት በርዕሰ ጉዳዬ ላይ ብዕሬ እንዲተልም ልፍቀድለት:: እግረ መንገዴን ግን ለአንባቢዬ “የንባብ ሥራ” ሰጥቼ የማልፈው አንጎራጓሪው “ለምን ኅዳር ሲታጠን” የሚለውን ስንኝ በአንጉርጉሮው ውስጥ እንደጠቀሰ እንዲያስቡበት ነው::
መቶ ዓመት የኋልዮሽ፤
1911 ዓ.ም ወርሃ ኅዳር:: የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ተከትሎ ከአጥናፍ አጥናፍ ዓለምን ጥቁር ከል ያለበሰ አንድ ክፉ የእልቂት ክስተት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአዳም ልጆችን ነፍስ በጭካኔ ነጠቀ:: ከታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ድርጊቱን ሳይሆን አባባሉን ለተመሳስሎ ገለጻ ብዋስ ሃሳቤን ይበልጥ ግልጽ ያደርግልኝ ይመስለኛል::
“ከአንበጣ የተረፈውን ኩብኩባ በላው – “እግዚኦ!”
ከኩብኩባ የተረፈውን ተምች በላው – “ያንተ ያለህ!”
ከተምች የተረፈውን ደጎብያ ጨረሰው – “አቤት! አቤት! አቤት!”
በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የተቀነበቡት የግነት ቃላት የጸሐፊው ናቸው::
ጥቅሱን መጥቀስ ያስፈለገው የድርጊቱ አፈጻጸም ተመሳሳይ ስለሆነ ሳይሆን የአንድምታ ገለጻው ሃሳቤን በደንብ ስለሚያብራራ ነው:: ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በተዓምር የተረፉትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች በማግስቱ ርሃብ ፈጃቸው:: ሰበቡ ሀገራትና ሕዝቦች በጦርነት ተዘፍቀው ማን ሊያርስ፣ ማን ሊጎለጉል፣ ማን ሊያመርትና ማን ሊያበስል – መቼም የጦርነት ደግ የለው::
ከርሃቡ ያመለጡትን “እስፓኒሽ ፍሉ” (በእኛ ቋንቋ የኅዳር በሽታ) አምሽክ አደረጋቸው:: እንደዚያ የከፋ ጥቁር ሞት ዓለማችንን ሰልጥኖባት አያውቅም:: ለማንኛውም ስለ መጀመሪያው የዓለም ጦርነት፣ ስለ “ስፓኒሽ ፍሉ” እልቂትና በሀገራችን አድርሶት ስለነበረው ጉዳት ጥቂት ሃሳቦች ፈነጣጥቄ በማሳረጊያዎቹ አናቅጽም እንደ ሀገር ዛሬ እያጠቃን ስላለው መልከ ጥፉና “ከኅዳር በሽታ” ስለማይተናነሰው ክፉ ደዌያችን የግሌን ጥቂት ሃሳብ ሰንዝሬ ርዕሰ ጉዳዬን አጠቃልላለሁ::
የአንደኛው የዓለም ጦርነት ሰበብ፤
እ.ኤ.አ ጁን 28 ቀን 1914 ዓ.ም አውስትሪያ ሐንጋሪያዊው ተቀዳሚ መስፍን ፍራንዝ ፈርዲናንድ ከባለቤቱ ከልዕልት ሶፊያ ጋር በሳሪያቮ ጉብኝት ላይ በነበረበት ወቅት በብሔር አቀንቃኙና ልክፍተኛ በነበረው ቦስኒያዊ አብዮተኛ ጋብሪሎ ፕሪንስፕ ይገደላል:: ይሄው የልዑሉ ግድያ ሰበብ ሆኖ 32 ሀገራት የተቧደኑበት የጦርነት እሳት ከዳር ዳር ተቀጣጠለ::
በአንድ ወገን ታላቋ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ጣሊያንና አሜሪካ በቃል ኪዳን ተፈጣጥመው ጦርነቱን ሲቀላቀሉ በሌላው ወገን ደግሞ ጀርመን፣ አውስትሪያ ሐንጋሪ፣ ቡልጌሪያና የኦቶማን ግዛቶች ወዘተ. ተሰባስበው እሳት ይተፉ በነበሩ ዘመናዊ መሣሪያዎች ይሞሻለቁ ገቡ::
በመጨረሻም በሃያ ሚሊዮን የሚገመተው የፕላኔታችን ሕዝብ የጉልበተኞች ጭዳ ሆኖ ሲያልቅ በሃያ ሚሊዮን የሚገመቱት ደግሞ ቁስለኛ በመሆን እ.ኤ.አ ኖቬምበር 1918 ዓ.ም ጦርነቱ ተደመደመ:: የጦርነቱ የእልቂት ትራዤዲ ተውኔት መጋረጃው የተጣለው ጀርመን መሸነፏን አምና የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተገዳ በመፈረሟ ሲሆን ይህም ስምምነት የተደረገው በ1918 ዓ.ም ልክ በአስራ አንደኛው ወር፣ ከወሩም በአስራ አንደኛው ቀን ከጠዋቱ ልክ 11 am (በእኛ ሰዓት አቆጣጠር አምስት ሰዓት ላይ መሆኑ ነው::) ዓለማችን ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ መሰል አሰቃቂ ጦርነት እንዳልገጠማት ታሪክ እማኝነቱን ሰጥቷል::
የጦርነት ማግስቱ “እስፓኒሽ ፍሉ”፤
1918 ዓ.ም የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ ማግስት ውሎ ሳያድር ዓለማችን “እስፓኒሽ ፍሉ” በመባል በሚታወቀው የኢንፍሉዌንዛ ተስቦ ወረርሽኝ መቅሰፍት በመመታቷ ሌላ የሞት እልቂት ምድርን አጠለሻት:: ዓመት ከምናምን ገደማ የቆየው ይህ ክፉ ወረርሽኝ ከ20 እስከ 40 ሚሊዮን የምድራችንን ዜጎች እንደፈጀ ይታመናል::
“እስፓኒሽ ፍሉ” ወይንም “ላ ግሪፕ” በመባል የሚታወቀው የኢንፍሉዌንዛ ተስቦ በስፔን ስም የተሰየመው በሽታው እዚያ ስለተከሰተ ሳይሆን በአንጻሩ ሀገሪቱ የበሽታውን ስም እንድትሸከም የተደረገው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ገለልተኛ ሆና እጇን አጣጥፋ ስለተቀመጠችና ወረርሽኙም በደጃፏ ስላልታየ ነበር:: “ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ ስፓኝ ባልዋለችበት ስያሜው የተሰጣት “በጦርነቱ የተሳተፉት ሀገራት ቀንተውባት ሊያበሳጯት ስለፈለጉ ነው” የሚሉ የታሪክ ጥቁምታዎች ሹክ ይሉናል::
እንዲያውም በበሽታው የትውልድ ሀገርነት የሚታሙት ፈረንሳይ፣ ቻይናና ታላቋ እንግሊዝ ሲሆኑ የመጀመሪያው ታማሚ በሽተኛ የታየው በአሜሪካዋ የካንሳስ ግዛት የጦር ካምፕ ውስጥ ስለነበር “ታላቋ ጉልበተኛ አሜሪካም” ከሀሜት አልተረፈችም:: ለማንኛውም የዓለማችንን የሚሊዮን ዜጎች በር የዘጋው ክፉ ደዌ ወደ እኛ ሠፈር ብቅ ብሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እንደምን እንዳረገፈ እናስታውስ::
የኅዳር በሽታ መዘዙ፤
በተለያዩ ስሞች የሚታወቀው “እስፓኒሽ ፍሉ” በእኛ ሀገር የተሰጠው ስም በአማርኛ “የኅዳር በሽታ”፣ በአፋን ኦሮሞ ደግሞ “ዱኩበ ቂሌንሳ” (የንፋስ በሽታ) የሚል ነበር:: በሽታው በ1911 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1918) የኅዳር ወር ዜጎቻችንን እያረገፈ በመገስገስ አዲስ አበባ የደረሰው በኅዳር ወር ስለነበር ስያሜው “የኅዳር በሽታ” ሊባል የቻለው በዚሁ ምክንያት ነው:: በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች በሽታው ቸነፈር እየተባለም ይጠራ ነበር::
የወረርሽኙ ስፋት በታሪክ የተዘገበው እንደሚከተለው ነው፤ “በሽታው በሀገራችን ውስጥ በነፋስ አማካይነት ተዛምቶ ወረርሽኙ ከጥቅምት ጀምሮ በየሰው ቤት እየገባ ይጥላቸው ጀመር:: በመጀመሪያ እንደ ሣልና ጉንፋን እድርጎ ይጥላል:: ከዚያም በሽተኛው ላይ ትኩሳት ይግለበለባል:: በማስከተልም ያስለቅሳል:: ነስር ያስነስራል፣ ተቅማጥና ውጋት አስከትሎም አእምሮን በማወክ ከሦስት እስከ አራት ቀናት አሰቃይቶ ይገላል::
የዓይን ምስክሩና የታሪክ ጸሐፊው መርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ በመጽሐፋቸው ውስጥ የወረርሽኙን ስፋት የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር፤ “አንዳንድ ስፍራ ቤተሰቡ በሙሉ ይታመም ስለነበር አስታማሚ በማጣት በርሃብና በውሃ ጥም ብዙ ሰው ተጎዳ:: ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ ሁለት፣ ሦስት መቶ ከዚህም በላይ ይሞት ጀመር:: በአንድ መቃብርም ሁለትና ሦስቱን ሬሳ እስከ መቅበር ተደረሰ:: አንዳንዶችም ሰዎች ሬሳ ተሸካሚ በማጣት በግቢያቸው ውስት ቀበሯቸው::”
“አፍላው በሽታ የቆየው ከኅዳር 7 እስከ 20 ለ14 ቀናት ያህል ነበር:: በተለይም ኅዳር 12 ቀን የኅዳር ሚካኤል ዕለት ብዙ ሰው ሞተ:: በዚያን ሰሞን መቃብር የሚቆፍርና ሬሳ ተሸክሞ የሚወስድ ሰው ለማግኘት ችግር ሆነ:: በቤተሰቡ ውስጥ ከበሽታው ያመለጡ ሲገኙ ሁለት ሰዎች ሬሳ ተሸክመው እየወሰዱ ይቀብራሉ:: ባል የሚስቱን፣ አባት የልጁን፣ ሬሳ እየተሸከመ ወስዶ ቀበረ:: ደግሞ አንዱ መቃብር ይቆፍርና ሬሳ ለማምጣት ወደ ቤቱ ሄዶ ሬሳ ይዞ ሲመለስ ሌላው ቀብሮበት ያገኘዋል::”
“ቤተሰቡ በሙሉ በታመመበትም ስፍራ ብዙዎች በየቤታቸው እየሞቱ አውሬ በላቸው:: ለጉዳይ አዲስ አበባ የመጣ እንግዳም እየታመመ መግቢያ ቤት አጥቶ በየመንገዱ እየወደቀ አውሬ በላው:: በዚያ ወራት በአዲስ አበባ የነበረውን ጭንቀት በስፍራው ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ:: አዲስ አበባ ላይ የሞተው የሕዝብ ቁጥር ዘጠኝ ሺህ ይሆናል ተብሎ ተገመተ:: በሽታው በአዲስ አበባ ብቻ አልተወሰነም ወደ ባላገርም ተላልፎ ብዙ ሰው ፈጅቷል:: ሆኖም በባላገር የአዲስ አበባን ያህል አልጠነከረም ይባላል:: በዚህ በሽታ በመላው ኢትዮጵያ እስከ 40 ሺህ ሞቷል:: በበሽታው ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንንና ልዕልት ወይዘሮ መነን በጠና ታመው ነበር:: ንግስተ ነገሥታት ዘውዲቱም አልጠናባቸውም እንጂ እንዲሁ ታመው ነበር::” (መርስዔ ሀዘን ወልድ ቂርቆስ፤ የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ)::
የትርክቱ መቀስቀሻ ሰበብ፤
ይህ የኅዳር በሽታ በታሪክነቱ የመቶ ዕድሜ ቢያስቆጥርም ዛሬም ድረስ በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን በዕለተ ሚካኤል በየመንደሩ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል ወግ ይዘከራ:: ጥላሁን ገሠሠ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ለዘመኑ አዲስ ዓመት ብሥራት የበሽታን ዓይነቶች በመሉ እየረገመ ያንጎራጎረው ለዚህ የኅዳር በሽታ መዘከሪያ ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገምቻለሁ:: ጥቂት ስንኞችን ላስታውስ፤
ዘላላም አይጉዳን ገብቶ በሽውታ፣
ተነቅሎ ይጥፋልን የሳንባ በሽታ::
ጉንፋን ኢንፍሉዌንዛ ቁርጥማትም ሁሉ፣
ይጥፉ ካገራችን ሕዝቡን ሳይጨርሱ::
የበሽታን ዓይነት በሙሉ ጠራርጎ፣
ከቆሻሻ ጋር ጎርፉ ሙልጭ አርጎ፣
ፈሳሽ የወንዝ ውሃ ተውሳኩን ይውሰደው፣
ጤና መሆንን ነው እኛ የምንወደው::
ትውስታችንን በመቶ ዓመቱ ላይ ብቻ ዘክሮ መደምደሙ ልክ አይመስለኝም:: ጥቂት ስለ ሀገራችን ሁኔታ መቆዘሙ አግባብ ይሆናል:: በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀንን እያስታወሱ የአካባቢን ቆሻሻ እየሰበሰቡ ማቃጠሉ መልካም ተግባር ነው:: በየቀኑ ቢሆን ደግሞ እጅግ ግሩም ይሆን ነበር::
ከቁሳዊው ቆሻሻ በዘለለ ግን ለዓመታትና ለወራት በፖለቲካ ወለድ የእርስ በእርስ ሽኩቻ ቆሻሻ ስንፋለም መክረማችን አሌ አይባልም:: በዚህ የነውጥና የለውጥ ሂደት አሸናፊና ተሸናፊ የመፈጠሩ ጉዳይ አይቀሬ ስለሆነ ብዙ ጉዳዮችን ታዝበናል:: ብዙ ጉዳቶችንም አስተናግደናል:: በአሸናፊነትና በተሸናፊነት ጎራ የለዩ ቡድኖችንም አስተውለናል:: ከጦርነቱ ፍልሚያ በአሸናፊነት ተወጥተናል የሚሉ ኃይላት ተሰባስበው “የብልፅግና ፓርቲ ፈጥረናል” ብለው አራስ ፓርቲያቸውን እሹሩሩ ማለት ከጀመሩ ጥቂት ቀናት ተቆጥረዋል:: አኩርፈናል ባዮቹም ፊታቸውን አጥቁረው ይበጀናል ያሉትን መስመር እያሰመሩ ለፖለቲካዊ ፍልሚያ ራሳቸውን እያሟሟቁ እንዳሉ እየሰማን ነው:: ለምን እየሰማን ብቻ ከአፋቸው እያደመጥን ጭምር ነው እንጂ::
በውጥር በተያዘው በዚህ ሀገራዊ የፍልሚያ ማግሥት ሌላ “ዘመናይ የኅዳር ወረርሽኝ” አገርሽቶ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተማሪዎቻችን በዘመን ወለዱ የፖለቲካ ኢንፍሉዌንዛ እያስነጠሱ እንዳሉ እያስተዋልን ነው:: ወረርሽኙ ሞትም፤ ከትምህርት ገበታ ላይ መኮብለልንም አስከትሏል:: በዚሁ የጀብደኛ ፖለቲከኞች ሤራ እስከ መቼ ልጆቻችንን እየቀበርን እንኖራለን? እስከ መቼስ የእድር ጡሩንባ እየሰማን እንደነግጣለን? ረ እስከመቼ ነጩን ሸማችንን የሀዘን ከል እየነከርን ጠቋቁረን አደባባይ እንውላለን?
የጠቆረው ቀናችን እንዲፈካ፣ የተተረማመሰው ሀገራዊ ጣጣችን እንዲሰክን ወገኔ ሆይ የኅዳር ወርን በፍቅር እጣን ለማጠን እንጨክን:: የጥላችን ቆሻሻ ሰብስበን እናቃጥል:: የሰላምን አዋጅ እያወጅን መረጋጋትን እንስበክ:: የሃይማኖት አበው፣ ተማርን የምንል ዜጎች፣ የማሕበራዊ ትስስር ቤተኞች፣ በንግድ ስራ የተሰማራን ዜጎች፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ተብዬዎች፣ ዜጎቻችን በሙሉ የኅዳር ወርን የፍቅር እጣን እያጠንን ሰላምን እናውጅ፣ የጎሰኝነትና የብሔር ትምክህተኝነትን አጉል ድንፋታ አደብ እናስገዛ፣ በምናገኘው መድረክ ሁሉ የሰላምን ርግብ እየለቀቅን የዘንባባ ዝንጣፊ እናውለብልብ:: “የኅዳር ተስቦ ሳይሆን የኅዳር ሰላም” ዝማሬያችን ይሆን:: ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012