በ2009 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 የተቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፤ ቀደም ሲል ቤት በማስተዳደር ተወስኖ የነበረው ተግባሩ ቤት መገንባትም ሆነ ማስገንባት፣ መሸጥና መግዛት ተጨምረውለት ወደስራ ገብቷል፡፡ ሲቋቋም የተሰጠውን ዓላማ ለማሳካትም በርካታ የእርምትና ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ የጀመረ ሲሆን፤ በቅርቡ ያደረገው የንግድ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ደግሞ በርካታ ቅሬታዎችን ያስተናገደ ሆኗል፡፡ እኛም በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮርፖሬሽኑ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ መልክ መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት ምን ነበር? በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ምን ተግባራት አከናውኗል?
አቶ ረሻድ፡- ተቋሙ በተለያዩ ስያሜዎች፣ ተጠሪነቱም ለተለያዩ ተቋማት ሆኖ ከአርባ አመት በላይ የቆየ ነው፡፡ ይህ ተቋም ደግሞ መጀመሪያ ሲቋቋም ሲያስተዳድራቸው የነበረውም ከመኳንንትና ከመሳፍንት የተወረሱ ትርፍ ቤቶችን በአዋጅ 47/67 የተወረሱ ቤቶችንና ከዚያ በፊትም በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተሰሩ ቤቶችን ነበር፡፡ ደርግ ወደ ስልጣን ሲወጣም ከተወረሱት ቤቶች ባለፈ አፓርታማዎችንና ሌሎችም በርካታ ቤቶችን በሰፊው ስለገነባ፤ ተቋሙ እነዚህንም ሲያከራይና የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ለአርባ ዓመታት ቢቆይም፤ የእድሜውን ያክል አላደገም፤ ለውጥም አላመጣም፡፡
በተለይም በኢህአዴግ መንግስት ቀድሞ የተጀመሩ የልማት ግንባታዎች በመቆማቸውና ተቋሙም ያሉትን ቤቶች ብቻ እያደሰና እየጠገነ ለማስተዳደር ተገድዷል፡፡ ሆኖም ከ27 አመት በኋላ መንግስት በተለይም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ ያለውን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ተገንዝቦ ክፍተቱን ለመሙላት በአዲስ መልኩ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ ተቋቋሟል፡፡ በእነዚህ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥም ይህንን የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ሰፊ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ለዚህም ከአደረጃጀት ጀምሮ የአመራርና የሰራተኛ ምደባ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የማያሰሩ አሰራሮችን፣ መመሪያዎችን ደንቦችና ሌሎች ኦፕሬሽናል ማንዋሎችን በማውጣት ወደስራ ተገብቷል፡፡ ያለውን ሃብት መለየት፣ ግምታቸውን ማወቅ፣ ሃብቶቹን በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደርና ገቢንም ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትም ተከናውነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሁለት ዓመታት ጉዞው ተግባራት መካከል በቅርቡ የተካሄደው የንግድ ቤቶች የዋጋ ማሻሻያ አንዱ ነው፡፡ ሆኖም ማሻሻያው ለበርካቶች የቅሬታ ምንጭ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለመሆኑ የዚህ ማሻሻያ መነሻ ምንድን ነው? ጭማሬው የተጋነነ ይመስላልና ማሻሻያው ሲደረግ ምን ያህል በጥናት ተደግፎ ነው?
አቶ ረሻድ፡- ተቋሙ ኮርፖሬሽን ሆኖ ሲቋቋም ከተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ የሚያስተዳራቸውን ቤቶችም ሆነ የሚገነባቸውን ቤቶች የኪራይ ተመኑን እያየ፣ እየከለሰ ማሻሻያ ማድረግ የሚል የህግ መነሻ ነው ያለን፡፡ ይህ ደግሞ በተቋምም ሆነ በገበያው ከወቅቱ ጋር ያለውን አለመጣጣም ማስተካከል፤ ብሎም ለስራው የሚያግዝ ገቢን የሚያስገኝ ተመጣጣኝ ትርፍ ማስገኘት ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ በነጻ ገበያው ተወዳድሮ እንዲያሸንፍ ለማስቻል ክፍተቶችን መሙላት ነው፡፡
ወደዚህ ተግባር ለመግባት ደግሞ መጀመሪያ በደንብና መመሪያው መነሻነት ሌሎች ባለሙያዎችን ጨምረን ጥናት አካሂደናል፡፡ በዚህም የኛ ቤቶች ስንት ብር ነው የሚከራዩት፤ ነባራዊ ሁኔታው ምን ይመስላል፤ ከገበያው ጋር ስናስተያየውስ ምን ይመስላል፤ የግሉ ምን ይመስላል፤ የቤተክህነት ምን ይመስላል፤ የአዲስ አበባ መስተዳደር በሚያሰራቸው ቤቶች የሚያከራያቸው ሱቆች ስንት ይከራያሉ፤ የሚለውን ነው ለማየት የሞከርነው፡፡ ጥናቱም ሰፊ አስተያየት የተሰጠበትና መጠይቆች ተዘጋጅተው ከእኛ ከአንድ ሺህ በላይ ናሙና ተወስዶ ከሌሎች ተከራዮችም ናሙና ተወስዶ ለረዥም ጊዜ የተከናወነ ነው፡፡ በጥናቱ መሰረትም የኛ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ለረጅም ጊዜ ያልተከለሰ፣ መመሪያውም መቼ እንደወጣ በግልፅ የማይታወቅ፤ በህጉ ላይ የተቀመጠው የአንድ ካሬ ሜትር ዋጋ ከ24 ብር እስከ 65 ብር መሆኑንና ከወቅቱ ገበያ ጋርም ያለመጣጣም መሆኑ ነው የታየው፡፡
ለምሳሌ፣ በካሬ ሜትር አስር ሳንቲም አለ፤ በዚህም ከአንድ ብር በታች የሚከራዩት ቤቶች ወደ አራት ነጥብ ሁለት በመቶ ናቸው፡፡ 42 በመቶ የሚሆኑት ቤቶችም በካሬ ሜትር ከአስር ብር በታች ተከራይተው ያሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መርካቶ አካባቢ የእኛ በካሬ ሜትር አስር ሣንቲም አለ፤ ጣና ገበያ አካባቢም በካሬ ሜትር 24 ብር ነው፤ የሌላው ግን 2ሺ900 ብር ነው፡፡
ይህ ክለሳ የመደ ረጉ ምክንያ ትም፣ አንደኛ ዋጋው ለረዥ ም ጊዜ ሳይከለስ በመ ቆየቱ ሲሆን፤ ሁለተ ኛም የአሰራር መዘበራ ረቅ በመታየቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የሚያ ከራያቸው ቤቶች ከዓ ርባ ዓመት ለሚዘል ጊዜ በመደበኛነት የከ ራዩ አሉ፤ በመሃልም የሚለቀቁ ቤቶች ሲኖሩ በጨረታ የተያ ዙ ቤቶች አሉ፤ በ2004 ዓ.ም ደግሞ በአከራይ ተከራይ የወሰዱ አሉ፡፡ ይህም በእኛና በግለሰብ ቤት መካከል ብቻ ሳይሆን በእኛ ተከራዮች መካከ ልም ልዩነቶች እንዲ ኖሩ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ፣ በጨረታ የወሰዱት ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ፤ በመደበኛ የወሰዱት ግን የሚከፍሉት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአብነት፣ በጨረታ ወስደው 40ሺ ብር ሲከፍሉ የነበሩ በአዲሱ ስሌት በተደረገው ቅናሽ ወደ 18ሺ ብር ወርዷል፡፡
የዋጋ ማሻሻያው ያስፈለገበት ሦስተኛ ጉዳይ ተከራዮቹ የሚሰጡትን አገልግሎት ሲሆን፤ ሕብረተሰቡ ሊገነዘበው የሚገባው ነገር እነርሱ የሚሰጡት አገልግሎት ከግለሰብ ተከራይተው ከሚሰሩት ጋር አንድ አይነት ነው፡፡ እነርሱ ግን ከግለሰብ ጋር ለምን ታወዳድሩናላችሁ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ እኛ የምንለው ደግሞ፣ ገበያው በአንድ ቅርጫት ነው ያለው፤ በዚህ ድጎማ መሰረት የተለያየ ምርት አምርታችሁ ለማህበረሰቡ የምትሰጡት አገልግሎት ቅናሽ ያለው ቢሆን ኖሮ የድጎማው ተጽዕኖ ወደ ህብረተሰቡ ደርሷልና እሰየው ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ የቀበሌ መዝናኛ ሌላ ቦታ አስር ብር የሚሸጥን ማኪያቶ አራት ብር ይሸጣል፡፡ እዚህ ላይ የተደረገው ድጎማ ወደ ህብረተሰቡ ደርሷል፡፡ ነገር ግን ከእኛ አንድ ሺህ እና ሁለት ሺህ ብር እየተከራዩ በአስርና ሃያ ሺህ ብር ከሚከራዩት እኩል ማኪያቶና ቡና አስርና አስራ አምስት ብር ይሸጣሉ፡፡ ይህ ቀላል ማሳያ ነው፡፡
እናም ሰዉ መሳሳት የሌለበት እዚህ ጋ ነው፡፡ የአንዳንዱ አስደንጋጭ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አራምቤ ሆቴል የመንግስት ነው፤ ፈረንጆች ሁሉ ያድራሉ፤ ብዙ አልጋ ያለውና ባለ ስምንት ፎቅ ነው፡፡ ሆኖም በወር 30ሺ ብር ነው የሚከፍለው፡፡ እርሱ ግን ይሄንን በቀን ሊሰራው ይችላል፡፡ በተመሳሳይ፣ ፒያሳ ባቅላባ ቤት ስድስት ሺ ብር፤ ጆሊ ባር አምስት ሺ ብር፤ ቱሪስት ሆቴል 13ሺ ብር፤ ሮሚና ካፌ ሦስት ሺ ብር ነው በወር የሚከፍሉት፤ በዚህ መልኩ የሚገለጹ በርካታ ቦታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ሂደት ደግሞ የዋጋ አለመመጣጠን አምጥቷል፡፡
እናም ቢዚህ መልኩ ያለውንና አዲሱን የኪራይ ተመን አቅርቦ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትሃዊነቱን እየው ቢባል፤ እንደሚባለውና እንደሚጮኸው ስላይደለ ውጤቱ ጥሩ አይደለም፡፡ ያልተሰሙ ድምጾች አሉ የምንለውም ለዛ ነው፡፡ አንድ አካል በዚህ ዋጋ ለአርባ ዓመት መጠቀሙ በራሱ ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ቤቶች የ100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረቶች ናቸው፡፡ ከመሳፍንቱና መኳንንቱ የተወረሰ ቤትም ቢሆን ከሚስኪኑ አርሶአደር እህል ዘርፎ ነው ያ ቤት የተሰራው፡፡ በደርግ ጊዜ የተሰሩት ሕንጻዎችም ከሚስኪኑ አርሶአደርና ነጋዴ ተሰብስቦ ነው፡፡ ስለዚህ ንብረትነቱ የኮርፖሬሽኑም ሆነ የሌላ ሳይሆን የ100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም በማሻሻያው ከተጮኹት ይልቅ ያልተሰሙ የ100 ሚሊዮን ህዝብ ድምጾች አሉ፡፡
በእነዚህ ቤቶች ያሉ ሰዎች ግን አርባ ዓመት ሰርተው ተጠቅመዋል፤ ፎቅም ሰርተዋል፡፡ ሆኖም ይሄን ያደረገ አካል በቃኝ እያለ አይደለም፡፡ ፍትሃዊነት ከተባለም በዚህ ጊዜ ነገር ፍለጋ ነው ከማለት ይልቅ በቀናነት መመልከት ይገባ ነበር፡፡ ለውጡን ያመጣው እኮ የእኩል ተጠቃሚነት መጥፋት የወለደው ጥያቄ ነው፡፡ አሁንም ቄሮ ወይም ፋኖ ወይም ሌላው አካል መጥቶ እንዲታገል መጠበቅ የለበትም፡፡ እኛም የባለፈው ስህተታችንን አይተን የተጣመሙ ነገሮችን ማስተካከል ነው ያለብን፡፡
አራተኛው ጉዳይ ሳይለፉ መጠቀም በመስፋፋቱ ነው፡፡ በዚህም ቁልፍ እየተቀበሉ አምስትና ስድስት ሚሊዮን ነው የሚሸጠው፡፡ በዚህ ሂደት 11 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሱቅ እናውቃለን፡፡ እዚህ መጥቶም ስንት ብር ነው የምትጨምሩት እኛ ቁልፍ እንገዛለን ነው የሚባለው፡፡ ይሄ ሕገ ወጥነት ነው፡፡ አንድን ሱቅ በጥሬ ገንዘብ 11 ሚሊዮን ብር አውጥቶ የሚገዛ አካል አስርና ሃያ ሺ ብር ክፈል ሲባል ለምንድን ነው እግሬንና ራሴን የሚባለው?
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሊታይ የሚገባው የጥገናና እድሳት ጉዳይ መነሳቱ ነው፡፡ ዘመናዊ አልሆነም፤ ቤቱ አይጠገንም፤ ወዘተ. እየተባለ ሁሉም ቅሬታ ያነሳል፡፡ ሆኖም 160 እና 120 ብር ተቀብለን እንዴት ነው የምንጠግነው? ለአመራርና ለሌሎችም ተቋማት በዓመት 40 ሚሊዮን ብር ነው የምናወጣው፡፡ ታዲያ ይሄን አገልግሎት ለመስጠት ከየት ነው የሚመጣው? ይህ ተቋም 43 ዓመት ሰርቶ አንድ ቢሊዮን ብር ካዝናው ውስጥ የለም፡፡ ሰዉ ግን ከሶስትና ከአራት ፎቅ ስንት ሚሊዮን ነው በዓመት የሚያገኘው፡፡ አሁን የተጠየቀው ቀድሞ የተጠቀመበትን ሂሳብ አይደለም፤ ወይም ውጣና ጨረታ ይውጣ አይደለም፡፡ ይልቁንም አሁን ለተጀመረው የቤት ልማት ዘርፍ ጥቂት አስተዋጽዖ እንዲኖረው እና በዚህ እድል ያልተጠቀሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵ ያውያንም እንደ ዜጋ ይጠቀሙ የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማሻሻያው ምንም በጥናት የተደገፈ ቢሆንም ከ43 ዓመት በላይ ሳይታይ የቆየ ስራ ድንገት ሲከናወን ከስህተት የጸዳ ስራ ነው ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡ ታዲያ በንግድ ቤቶቹ ላይ የተደረገውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመመልከትና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ያስቀመጣችሁት አቅጣጫ ይኖር ይሆን?
አቶ ረሻድ፡- ምንም እንኳን በጥናት ታግዘን በጥንቃቄ ብንሰራና አጽድቀን ወደስራ ብንገባም ስህተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት፤ ሂደቱን ዝግ ሳናደርግም በትግበራው የመጀመሪያዎች ቀናት ሂደቱን እያየን ነበር፡፡ የቅሬታ አሰራር አስቀምጠንም ነው ወደትግበራ የገባነው፡፡ በዚህም ቅሬታ በቅርንጫፍ ደረጃ እንዲቀርብ፤ በቅርንጫፍ ደረጃ የማይፈቱም በእኛ ደረጃ እንዲፈቱ ብለን አዋቅረንና የቅሬታ መሙያ አዘጋጅተን፣ የቅሬታ መመሪያ ለማስፈጸምም ኮሚቴ አቋቁመን በየደረጃው ስንሰራ ነበር፡፡ በዚህም መጀመሪያ አካባቢ የተወሰኑ ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ በጣም የተጠቀሙ የተወሰኑ ቡድኖችም በየቅርንጫፉ እየሄዱ አንቀበልም እያሉና እያስተባበሩም ውል የገቡትን ሁሉ ወደኋላ እንዲመለሱ የማድረግ ሁኔታ ነበረ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት፣ ዕንባ ጠባቂ፣ ሚዲያና ሌሎችም ቦታዎች ሲሄዱም ነበር፡፡
አሁን በበርካቶች የሚነሳው በካሬ ሜትር 509 ብር ሆነ የሚለው ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሙሉ ያልሆነ መረጃ ነው፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ተመን ሲያወጣ፣ አንደኛ፣ በግልና በቤተ ክህነት የሚያከራዩ ቤቶችን የከፍተኛ ዋና አማካይ እና የዝቅተኛ ዋና አማካይ በመውሰድ የእነዚህ አማካይ ከሆነው 848 ብር ላይ 60 በመቶውን ብቻ ነው የወሰደው፡፡ ሁለተኛም የቤቶቹ ደረጃ፣ የቦታው ደረጃና የቤቱ ወለል ስፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ10 እስከ 30 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረትም ተቋሙ የሚያከራያቸው ቤቶች እንደየደረጃቸው በካሬ ሜትር ከ509 እስከ 73 ብር ድረስ እየቀነሰ በሚሄድ ትመና ነው የሚከፈልባቸው፡፡ በዚህም መሰረት በካሬ 509 ብር የሚከፍሉት 70 ቤቶች (አንድ በመቶ) ብቻ ናቸው፡፡
ሆኖም ቅሬታው ሁለት መቶ ብር ነበር አስር ሺ ብር ገባብኝ ነው፡፡ እንደ ዜጋ ሲታሰብ አሁን ላይ በሁለት መቶ ብር የንግድ ቤት ይቅርና ማደሪያ የሚሆን የቆርቆሮ ቤት እንኳን አይከራይም፡፡ ሁለት መቶ ብር እየተከፈለ አርባ ዓመት መጠቀሙ በራሱ ወንጀል ነበር፡፡ የብዙ ሰው ጥያቄና ብዥታም ይሄን ያክል ጨመሩባቸው ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ቦታዎች በተጨበጭ ከሌላው ጋር ስናስተያይ ትክክል ነው ወይ አደለም የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን በባቡር መስመር ዝርጋታ ወይም በሌላ ምክንያት በስራቸው ላይ ተጽዕኖ የፈጠረባቸው ቦታዎች የዘርፍ ለውጥ ማድረግ ካለባቸው እንዲለውጡ ይደረጋል፡፡ በፊት በተወሰደ ፈቃድ ብቻ ነበር መስራት የሚቻለው፡፡ አሁን አማራጭ ይፈጠርላቸዋል፡፡ በጥቅሉ ግን ማሻሻያውን ተከትሎ ለተነሳው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የቅሬታ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ሲሆን፤ ታህሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ምላሽ ይሰጥባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ማሻሻያውን ተከትሎ ተከራይ ተቋማት ሰራተኞችን እየቀነሱ ሲሆን፤ በምርቶቻቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ጭማሪው የኑሮ ውድነት ላይ የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይችላል የሚል ስጋትም አለ፡፡ ይሄን በተመለከተስ ምን የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ረሻድ፡- እኔ እዚህ ጋር የተለየ አመለካከት አለኝ፡፡ እውነት ሰራተኛ ቀጥሮ እዚህ ጋር እነርሱ በሰበሰቡት ልክ በትክክል እየከፈሉ ነው ወይ የሚለውን ነገር እንደምናውቀው ነው፡፡ እዚህ ጋር ካፌ በአንድና በሁለት ሺህ ብር እየተከራየ አምስት መቶ እና አንድ ሺህ ብር ነው ለሰራተኛው የሚከፍለው፡፡ አሁን ላይ ሰራተኛን የማባረር ወይም የመቀነስ እርምጃ ውስጥ ከገቡም ጉዳዩን የፖለቲካ ገጽታ ለማስያዝ ስለፈለጉ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ለሰራተኛ የሚከፍሉት ዝቅተኛ ስለሆነ አሁንም ለመቀነስ የሚያበቃቸው ምክንያት የላቸውም፡፡ የዋጋ ጭማሪን በተመለከተም የአካባቢው ገበያ ስለሚገድባቸው ዋጋ ለመጨመር ይቸገራሉ፡፡ ሆኖም ሰራተኛ ሲቀንሱም ሆነ ዋጋ ሲጨምሩ የሚከታተል ሌላ አካል አለ፡፡ ሚዲያውም መስራት ያለበት በዚህ መልኩ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚከናወኑ ያልተገቡ እርምጃዎች ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ የዋጋ ማሻሻያ በንግድ ቤቶች ላይ የሚያቆም ነው፤ ወይስ የመኖሪያ ቤቶችንም ይመለከታል?
አቶ ረሻድ፡- እነዚህ ሁለቱ ባህሪያቸው ይለያያል፡፡ ወደ መኖሪያ ቤት ስንመጣ ብዙዎቹ አቅም የሌላቸው ናቸው፡፡ በአንድ ጊዜ ብናደርገው ደግሞ ከእኛ የንግዱንም የመኖሪያ ቤትም የተከራዩ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ደግሞም አሉ፡፡ አንዴ ጫና ከምንፈጥር፣ ከገበያውም ከፍትሃዊነቱም አኳያ በጣም ሰፊ ክፍተት ያለው የንግድ ቤቶች አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው አንዲት ሦስት በአራት የሆነች ትንሽ ክፍል ያውም በከተማ ዳርቻ ሁለት ሺህ ብር እየተከራየ ነው የሚኖረው፤ የእኛ ቤቶች ግን አንድ ግቢ መቶ ሃያ ብር ቢበዛ ሁለት መቶ ወይም ሦስት መቶ ብር ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፍትሃዊነት ጥያቄ ስለሚያስነሳ ይሄን ከፈጸምን በኋላ ቀጣይ ጥናት አድርገን የምንሄድበት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በኮርፖሬሽኑ ባለ ብልሹ አሰራር ምክንያት ቤቶቹ በዘመድና በዘር እየተላለፉ ይሰጡ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይሄን አሰራር ፈትሾ ከማረም አኳያ ምን ታስቧል? አሁንስ ከዚህን መሰል ብልሹ አሰራር በጠራ መልኩ ለማከናወን ምን ያህል ራሳችሁን አዘጋጅታችኋል?
አቶ ረሻድ፡- ይሄ በሰፊው ሲወራ የሚሰማ ጉዳይ ነው፤ በተጨባጭም የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ ከአሰራር መመሪያና ደንብ አኳያ ሲታይ ምንም ክፍተት የለም፡፡ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ጀምሮ ቤት ለማን ይሰጣል፣ ምን አይነት ቤት ለማን ይሰጣል፣ እንዴት ይጠየቃል፣ እንዴት ይስተናገዳሉ፣ የሚል የቤት አስተዳደር መመሪያ አለ፡፡ ትልቁ ነገር መመሪያውን መፈጸም አለመፈጸም ላይ ነው፡፡ በተጨማሪ አሁን ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ቤቶቹ በማን ተያዙ የሚለውን ነገር ከቤት ቆጠራ ጋር አያይዘን ብዙ ነገር ነው ያገኘነው፡፡
ትልልቅ የሚባሉትና በቤት ግንባታ ዘርፍ ላይ ተሰማርተውም ትልቅ የመንግስት ቤትና ጊቢ ይዞ ይገኛል፡፡ በአንጻሩ ግን ማደሪያ አጥቶ የሚንከራተት አለ፡፡ በሌላ በኩል፣ ሀብት ኖሮትና የራሱን ሁለትና ሶስት ቤት እያከራየ ያለ ባለሃብት አለ፡፡ አመራርም ሆኖ ቤት እያለው የመንግስት ቤት የሚጠቀመውንም የለየንበት አግባብ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ አንዳንድ ክልሎችና ብሔራዊ ድርጅቶች አቋም ወስደው አዲስ አበባ ውስጥ ቤት ያለው ያስረክብ ብለው የጀመርነው ነገር አለ፡፡ ባለሃብቶችንም ወደ እርምጃ ከመግባታችን በፊት መልሱ ብለን በቀና መንፈስ እያናገርን ነው፡፡
አንዳንዱም የወሰደውን ቤት በአምስትና አስር ሺ ብር አከራይቶ ለእኛ ሁለትና ሦስት መቶ ብር እየከፈለ አውሮፓና አሜሪካ የሚኖር አለ፡፡ በቆጠራው አግኝተን ስንለጥፍ ግን ለህክምና ሄጄ ነው እንጂ የምኖርበት ነው ብሎ እግድ እያመጣ የሚያደናቅፍ አለ፡፡ በዚህ ስድስትና ሰባት ወራት ውስጥ ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ቤቶች በዚህ አግባብ የተያዙትን መልሰናል፤ ለሚገባውም ሰጥተናል፡፡ አሁንም ግን ብዙ የሚቀሩ ስላሉ በዚሁ አግባብ ለሚገባውና ለተቸገረው መሆን አለበት በሚል እየተሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮርፖሬሽኑ የሚያስተ ዳድራቸውን ቤቶች በአግባቡ ስለማያውቃቸው ቤቶቹ ለሶስተኛ ወገን እየተላለፉ፣ መጋዘኖችም በግለሰቦች እጅ ታጥረው እየተያዙ ነው፤ ቤቶቹም ለምን ተግባር እንደሚውሉ ስለማይከታተል የዜጎች ማሰሪያና ማሰቃያ መሆናቸው ይገለጻል፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት? ለቀጣይስ ምን መፍትሄ አስባችኋል?
አቶ ረሻድ፡- ቤቱን አያውቀውም የሚለው ነገር ትክክል ነበር፡፡ የምታስተዳድረውን ቤት አለማወቅ ደግሞ አሳፋሪ ነው፡፡ አንድ ሰው ጥያቄ ሲያቀርብ ቤት ፈልግና አምጣ ነው የሚባለው፡፡ የቤቶቹ መገኛ ቦታ አይታወቅም ነበር፡፡ ስለዚህ ቤቶቹ በሚቆጠርበት ወቅት ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ታብሌቶችን ተውሰንና ስልጠና ሰጥተን ሌሎች ሰዎችም ጨምረን ኤክስ ዋይ ኮኦርዲኔት ነው የወሰድነው፡፡ ይሄንንም ከጉግል ኤርዝ ጋር አይያዘን ቤቶቹ ያሉበትን ቦታ፣ የቤቱ መጠንና ያለበት ሁኔታ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በአግባቡ አስቀምጠናል፡፡ የማህደርና ይዞታ ማናበብ ተግባርም ተከናውኗል፡፡
ቤቶቹን ለምን ተግባር እንደሚውሉ ከመቆጣጠር አኳያ በኪራይ በሚቀመጠው ውል መሰረት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በግለሰቦችም ይሁን በመንግስት ተቋማት ቤት ውስጥ ምን እየተሰራ ነው ብሎ ለመከታተል አይቻልም፡፡ ይሄን የመከታተል ኃላፊነትም የሌላ አካል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተነገረው ተግባር እጅጉን አሳዛኝ ነው፡፡ እነዚህ ቤቶችም በሂደት የደህንነት መስሪያ ቤት በራሱ ካርታ አውጥቶባቸው የሚጠቀምባቸው፤ ኮርፖሬሽኑም ኪራይ የማይቀበልባቸው ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮርፖሬሽኑ በአዲስ መልኩ ሲቋቋም ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ የመኖሪያ ቤት የመገንባት የቀደመ ተግባሩ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለመሆኑ ይሄን ለማከናወን የሚያስችል ምን ዝግጅት እየተደረገ ነው? ወደተግባርስ መቼ ይገባል? የሚገነቡት ቤቶችስ በምን መልኩ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ይሆናሉ?
አቶ ረሻድ፡- የቤቶቹ ግንባታ መነሻ የቤት እጥረት ሲሆን፤ ግቡም ለፌዴራል መንግስት አመራሮችና ለመንግስት ሰራተኞች በተለይም ተጽዕኖውን መቋቋም ላልቻሉና ለተረሱት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ፍላጎት እያረካንና አቅም እያጎለበትን ስንመጣም እራሱን ማገዝ ለማይችለው ህብረተሰብ ቤት በማቅረብ ለማገዝ ነው፡፡ ቤቶቹም ግንባታውን በሚያግዝ መልኩ ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ መንግስት እየደጎመ ተደራሽ የሚሆኑ ሲሆን፤ ዓላማውን መሰረት በማድረግ አገልግሎት የሚሰጥበት ሂደት ነው፡፡
ቤቶቹ ከዚህ በፊት ምንም ሳይዘጋጅ በ2010 ዓ.ም ይገነባሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ነገሮች እንደታሰቡት ባለመሆኑ እስካሁን የግንባታ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ መሰረት አሁን ላይ ቴክኒኩ አልቆ ኮንትራክተር መረጣ ላይ ተደርሷል፤ ወደፋይናንሱም ተገብቷል፡፡ በመሆኑም በአምስት ሳይቶች ላይም እስከ አስር ፎቅ ያላቸው መንታ ህንጻዎች በመጀመሪያ ዙር የሚገነቡ ይሆናል፡፡ በእነዚህ ሳይቶችም በጥር ወር ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ ግንባታቸውም አቅምና ልምድ ባላቸው ተቋራጮች እንዲከናወን በማድረግ በጥራት ሳንደራደር ከአስራ ስምንት ወር እስከ ሃያ አራት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ረሻድ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
ወንድወሰን ሽመልስ