ጥበብ ብዙ አፍቃሪና ወዳጅ አላት። በእርሷ የሚጠሩ ጥቂቶች መሆናቸውም ዋጋዋን ከፍ ሳያደርገው አልቀረም። የጥበብን ዋጋ የተረዱ ነፍሶች እልፍ ዘመን ወደፊት አሻግረው አሳይተዋል፤ ያለፉ ምዕት ዓመታትን ማስቃኘት ችለዋል። አንዳንዶች ሥነ ውበትን አድንቀውበት ሲያልፉ ሌሎች በብልሃት ትውልድ አንጸው አገር ገንብተውበታል።
«እኛ ኪነጥበብን መጠቀም ባለብን ደረጃ አልተጠቀምንበትም። ይህን ያልኩት ከልቤ ነውና፤ የተለመደ ሂስ ነው ተብሎ አስተያየቴ እንደማይተው ተስፋ አደርጋለሁ። ኪነጥበብ ሁሌም አስፈላጊ ሆኖ አሁን ደግሞ የበለጠ አስፈላጊነቱ ይጎላል። በዚህ ጊዜ እንደ ማኅበረሰብ በርካታ ህክምናዎች ያስፈልጉናል። መቅደምም መፍጠንም ያለበት ደግሞ የአስተሳሰብ ህክምና ነው።»
ይህን የተናገሩት የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ናቸው። «የት ተገኝተው?» ላለ መልሱ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አዘጋጅነት «ብሌን ኪነጥበባዊ የሰላም ምሽት» በሚል ስያሜ ባሳለፍነው ረቡዕ ታኅሣሥ 17 ቀን 2011ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደ የኪነጥበብ ምሽት ነው።
የዐይን ብሌን እና ሰላም በአንድነት የተወሱበት ይህ መድረክ በአቢሲኒያ የሥነጥበብ ተማሪዎች ኅብረ ዝማሬ ተከፍቶ በቅርቡ የተለዩንን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን በማሰብ ቀጥሎ፤ በገጣምያንና ወግ አቅራቢዎች ሲደምቅ፤ በሚኒስትሮች ንግግርና ድርጊት ደግሞ ሞገስን ተሞልቶ አምሽቷል። በክብር እንግድነት የተገኙትና ከታዳምያን እንደ አንዱ ሆነው ባለተለመደ ሁኔታ እስከፍጻሜው የቆዩት የሰላም ሚኒስትሯ ብቻ ሳይሆኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ጭምር ነበሩ።
ብሌን እና ሰላም
እነዚህ ቃላት ለሰዎች ስያሜነት ብቻ የሚያገለግሉ አይደሉም፤ ሕይወት ካለው ፍጡር ጋር ሕይወት ተዘርቶባቸው የሚኖሩና የሚያኖሩ ናቸው፤ አሉኝ ያለ ሁሉ የሚሳሳና የሚጠብቃቸው። ሰዎች የሚወዱትን ሰውም ሆነ ነገር ዐይኔ አልያም ብሌኔ ይሉት የለ? ድምፃውያን በሙዚቃቸው፤ ጸሐፍት በጽሑፍ ሥራዎቻቸው፤ «ብሌኔ…ዓይኔ…በአንቺ የመጣ በዓይኔ መጣ…» ሲሉ ከብሂሉ ተውሰው የወደዱትን ከዐይን ብሌናቸው አመሳስለው አሞካሽተውበታል።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ያዘጋጀውና ብሔራዊ ቴአትር ማምሻውን ከ11 ሰዓት ጀምሮ ተቀብሎ ያስተናገደው የኪነጥበብ ምሽት፤ የዐይን ብሌንን ከሰላም አቆራኝቶ የሰላምን ዋጋ ከቃል በዘለለ ለሁሉም በቀረበ መልኩ ለማስረዳት የሞከረ መርሐ ግብር ነበር። በመድረኩ የቀረቡ ሥራዎችም ሰላምና ፍቅር እንዲሁም አገር ላይ አተኩረዋል። አዳዲስ ስሜትን የሚፈጥሩ በጥበብ የተዋዙ ሃሳቦች ለታዳሚ እናም ወደፊት ለሚመለከት ሁሉ ቀርበዋል።
የመርሐ ግብሩ አዘጋጀ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ደራሲና ጋዜጠኛ አቶ አበረ አዳሙ የዝግጅቱ ዓላማም ይህ እንደነበርና በቀጣይነትም የሚሠራው በዚህ ላይ እንደሆነ አስቀድመው ገልጸው ነበር። «አሁን በአገራችን ሰላም ብሔራዊ አደጋ ተደቅኖበታል። እኛ ግን ሰላማችንን እንደ ዐይናችን ብሌን እንጠበቃ የሚል መልዕክት ያለው ነው» ሲሉ ገልጸው ነበር።
አቶ አበረ እንዳሉትም የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ከስሙ አስቀድሞ አንጋፋ እየተባለ በመጠራት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብን በማረቅ በኩልም ቀዳሚና ፋና ወጊ ሆኖ ሊቆም ያስፈልጋል። ይህም ራሱን የቻለ የኪነጥበብ ምሽት ለዚህ ሃሳብ የመጀመሪያው ዕርምጃ ሳይሆን አልቀረም።
የዝግጅቱን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ፤ እንዲህ ሲሉ በማኅበሩ ስም ሃሳባቸውን አካፍለዋል፤ «…በመልካም አስተዳደር እጦትና ኢ- ሰብዓዊ ድርጊቶች ሲማረር የኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ በጨለማ ውስጥ እንደተወረወረ ትንታግ ብልጭ ያለውን ፖለቲካዊ ለውጥ ከተስፋነት ወጥቶ ብርሃኑ ጎልቶ ጨለማውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይገፍልኛል ብሎ በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቀው ሳለ፤ እዚህም እዚያም የሚታየው ሁከት በእጅጉ ያሳስባል።»
ታድያ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር አባላትም ከሕዝብ የወጡ እንደመሆናቸው ሕመሙን ሁሉም እንደሚጋራ አንስተው፤ ይህም ጥበባዊ የሰላም ምሽቱን ሰላምን አንስቶ ለማዘጋጀት ምክንያት እንደሆናቸው ጠቅሰዋል። «ሰላም የግለሰቦች ብቻ ወይም ለመንግሥት የሚተው ጉዳይ አይደለምና» አሉ።
የኪነጥበብና የፖለቲካ እይታ
«ጥበብ የተጣላን አስታራቂ፣ የተለያየን አገናኝ፣ የተራራቀን አቀራራቢ፣ የተከፋን አስደሳች፣ የፈዘዘን አነቃቂ፣ የደከመን አበረታች፣ ያዘነን አጽናኝ፣ የሰነፈን አጠንካሪ፣ ወኔ ያጣን አጀጋኝ፣ የይቻላል ሞገስን የምታጎናጽፍ ናት» አሉ፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው።
ታድያ በአገራችን አገር በቀለ የሆነውን ጥበብና እውቀት ከኋላ ቀርነት ቆጥረን አለመጠቀማችን ያስከፈለንን ዋጋ ከወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ጋር በማያያዝ አንስተዋል። እናም ለኪነጥበብ ባለሙያው እንዲህ አሉ፤ «የኪነጥበብ ባለሙያዎች ያሰባችሁት እንዲሳካ ሁላችሁም በራሳችሁ አቅምና እይታ በጥበብ መሪነት የማንም መሣሪያ፣ ተላላኪና መልዕክተኛ ሳትሆኑ ለሕዝብና ለአገር ጥቅም የሚበጁ ሥራዎችን መሥራት ይኖርባችኋል።…አጥፊውን ከጥፋቱ እንድትመልሱ ትውልድም እንድትቀርጹ ይገባልና ጅምሩን ለማጠናከር በሁሉም የአገራችን ክፍሎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን በማስተካከል ተግባር ላይ እንድታተኩሩ አደራ እላለሁ» አሉ። አሁን ያለውን ኪነጥበባዊ እንቅስቃሴም «ከመቅረት መዘግየት ይሻላል» ሲሉ ርብርቡ የሚበረታታ መሆንና አብሮ መሥራት አሁንም እንደሚጠበቅ ገለጹ።
ፖለቲካ በሰፈሩ ማን አለብኝ እንዳለና ደረቱን እንዳሳበጠ ጎረምሳ፤ ሌላውን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ሁሉ አጥፎ የተጽእኖው ዱላ ማረፊያ አድርጓቸዋል። ለዚህ ነው፤ ስለሰላም እየተነሳ በመካከል ፖለቲካ ጣልቃ ቢገባ ነገሩ አዲስ የማይሆነው። ኃይል አላት የሚባልና አገር የመነቅነቅ አቅም ያለው ኪነጥበብ እንኳ በፖለቲካ አቅሙን የተነጠቀ ይመስላል።
በእርግጥ ኃይልና አቅም ያጣው ኪነጥበብ ሳይሆን የኪነጥበብ ባለሙያው መሆኑ ግልጽ ነው። የዚህም ምክንያት የወገናቸውን ድምፅ በብዕራቸው አሰምቶ አዲስ መንገድ ለማሳየትና ለማሰማት የሚፍጨረጨሩ ጥቂቶች በአንድም በሌላም መንገድ ታስረዋል። እናም፤ ምንም እንኳ ጥበብ አገር እንድትመራ ብንጠብቅም አንዳንዴ የፖለቲካን «ቸርነት» ስትማጸን ማስተዋላችን አይቀሬ ነው።
አሁን ያለው የአገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኪነጥበቡ ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽእኖና ተስፋ ስንመለከት፤ ይህን የሁለቱን ዘርፎች ትስስር በሚገባ ማየት እንችላለን። ያም ሆነ ይህ፤ አሁን ለሁሉም እንደመጣ በሚታመነው መልካም አጋጣሚ ኪነጥበብም የድርሻውን ሊጠቀም ይገባል። ይህን አጋጣሚም አለመጠቀም ኪሳራ የሚያስከትል ነው።
«እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል
አገር የሌለ እንደሁ ወዴት ይደረሳል» እንዲሉ፤ ጥበቡም የሚያድገውና የሚበለጽገው፤ ጠቢቡም በግብሩ የሚጠራው በገዛ አገሩ ነውና፤ ለማኅበራዊ አገልግሎት ቅድሚያ መስጠት ከባለሙያዎቹ ይጠበቃል። አጋጣሚውን መሠረት መጣያ አድረጎ መጓዝ ካልተቻለ ግን፤ ኪነጥበብ በፖለቲካ ጡንቻ ስር መቆየቱ አይቀርም። አሁን ላይ ዝናን ወይም ሀብትን ሳይሆን፤ ሰውን ማትረፊያና ማፍሪያ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን መተግበር ለአገሩ ከሚያስብ ዜጋ ይልቁንም የጥበብ ነገር ከገባው የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ጥበብ የነካው…
ማዶ ለማዶ ሆነው የማይተያዩ ዘመናትን እንደመሰላል ደግሞም እንደ ድልድይ አገልግለው ከሚያገናኙት መካከል ጥበብና የጥበብ ክዋኔዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በዚህም ተግባር የሚፈሩትና የሚተዉት ነገር ሳይኖር፤ በሥነ ውበት ፋይዳቸውም ይሁን ለማኅበረሰባዊ አገልግሎታቸው በጎውን ሃሳብ ያቀብላሉ፤ ያመላክታሉ። ሹማምንት ጥፋታቸው ማጣቀሻ እንዳይሆን ስለሚሰጉ አይወዷቸውም፤ ባለስልጣናት ሊገለገሉባቸው ይፈልጋሉ እንጂ አያግዟቸውም።
ለምን? ጥበብ እውነቱን መረር አድርጎ አንዳንዴም በፈገግታ አዋዝቶ የሚናገርበት የራሱ መንገድ ስላለው። ለምሳሌ በብሌን የኪነጥበብ ምሽት ላይ ከቀረቡ ሥራዎች መካከል አንዱን ግጥም ላንሳ። ግጥሙን ያቀረበው ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ነው። «ከጦርነት ጋር ጦርነት» ይሰኛል። ከስንኞቹ ቆንጥሬ ላቅርብላችሁ፤
«ሰላም እንሁን ብንራብ፣
ሰላም እንሁን ብንጠማም፣
ከረሀብ ጦርነት ይሻላል ይሉትን ነገር አንሰማም።
…ረሀብ ዘመዳችን ነው…ረሀብ ወዳጃችን ነው አብረነው ብዙ ኖረናል፣
በዘመን ትውውቅ አድገን በዘመን ተከባብረናል።
ጦርነት ነው ጠላታችን እርስ በእስር የሚያጫርሰን፣
አርባ ዓመት የተጓዝነውን በአርባ ቀን የሚመልሰን።»
ረሀብ እንዲህ በግጥም ሲቀርብ፤ አውነቱ ቀለል ብሎ ይዋጥልናል። ጦርነት በዚህ መልኩ ሲገለጽ ያለንበት እንድንቃኝ ያስገድደናል። እንደው በዕለቱ ከቀረቡት ሥራዎች መካከል ይህን አነሳሁ እንጂ፤ በጥበብ የወዙ ኃያል ቃላትና ቁጣዎች፤ የትውልድ ወቀሳዎችና ቁጭቶችን ታዳሚው አጨብጭቦና ስቆ ሰምቷቸዋል። እንግዲህ እያደር ሲታወስ የቆመውን በማጽናት፤ የሚንገዳገደውን በማረጋጋት አንዳች ፋይዳ ሳይኖረው አይቀርም።
የሰላሙ መድረክ ትዕይንቶች
በነገራችን ላይ በዚህ የኪነጥበብ ምሽት በሼህ ሁሴን ጂብሪል ላይ የሚያተኩር አጠር ያለ ዲስኩርና ዳሰሳ ከመንዙማ ጋር ቀርቧል። ዳሰሳውን ያቀረቡት ዶክተር መሐመድ ዓሊ ኢድሪስ ሲሆኑ፤ የሼህ ሁሴንን የግጥም ሥራዎችና ምን ያህል ትንቢት ተናጋሪ እንደነበሩ በጥቂቱ ዘርዘር አድርገው አብራርተዋል። ምሽቱም ሼህ ሁሴንን የሚዘክርና የሚያስብ ነበርና በነበረው ሰዓት ለታዳሚው መቅረብ የሚችል መረጃ ቀርቧል።
እንዳልነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ አንጋፋዎቹ አያልነህ ሙላት፣ ጌታቸው በለጠ እንዲሁም ወጣት ገጣምያን በዚህ ዝግጅት ተሳትፈዋል፤ ሥራዎቻቸውንም አቅርበዋል። ከነዛ ጥበባዊ ክዋኔዎች በተጓዳኝ የመንግሥት ባለስልጣናት ሱታፌና ቅርበት ምን ያህል አቅምና ኃይል እንዳለው ማየት ይቻላል።
እንዲህ ነው፤ መርሐ ግብሩን ምክንያት በማድረግ በሰላም ስም ዳቦ ተቆርሶ ነበር። ሚኒስትሮቹ በክብር እንግድነት ዳቦውን የቆረሱ ሲሆን፤ ለይስሙላ መቁረሻውን ይዘው ለመቅረጸ ምስል ብቻ የሚቀር ፈገግታን አላሳዩም። ይልቁንም የተቆረሰውን ዳቦ በሰፌድ ይዘው አዞሩ፤ በሰላም ስምም እንካችሁ አሉ።
ይህ ትህትና በሥራ ሰዓት ሳይሆን ማምሻውን በተካሄደ የኪነጥበብ ድግስ የታየ ነው። በዕለቱ እስከ መርሐ ግብሩ ፍጻሜ ከቆዩት ሁለቱ ሚኒስትሮች ወይም የመንግሥት ባለስልጣናት ድርጊት ለየግላችን የምንወስደው ምሳሌ እንዳለ ሆኖ፤ የኪነጥበብ ባለሙያው ፈቃደኝነታቸውንና እሺ ባይነታቸውን በጥበብ ተጠቅሞ አገርንም ዘርፉንም እንዲያገለግል እንደሚጠበቅበት ግን ልብ ሊባል ያስፈልጋል። የጠየቅነውን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑትን ካገኘን፤ አጠገባችን እስኪያመጡት መጠበቅ ሳይሆን ቀርቦ መውሰድን ይጠይቃልና።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ይህን የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን የኪነጥበብ ምሽት አመስግነው ትብብር ካስፈለገም የሚኒስቴሩ ቢሮ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል። ይህም እንግዲህ «ሜዳውና ፈረሱ» ነውና፤ የኢትዮጵያን ደራስያን ማኅበርም የመሠረቱትን አንጋፋ፣ በሕይወትም በሙያም ልምድ ያካበቱና ብዙ ማለት የሚችሉት ባለሙያዎቹ የሚገኙበትን መድረክ አመቻችቶ በመቀጠል አገልግሎቱን እንደሚያሰፋ፤ ቃሉንም እንደሚያከብር እናምናለን። በታኅሣሥ ወር 17ኛው ቀን የተካሄደው የኪነጥበብ ምሽት ግን ይህን በሚመስል መልኩ ተካሂዷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011
ሊዲያ ተስፋዬ