እነሆ ምሳሌ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ዓይነሥውራንን ተደራሽ ለማድረግ መጻሕፍትን በድምጽ ቀርጾ ስለማስፋፋት ከጋዜጠኞች፣ ከተራኪ አርቲስቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
ውይይቱም ባለፈው ማክሰኞ ታህሳስ 16 ቀን በኔክሰስ ሆቴል የተደረገ ነው፡፡ ይህንን ሁነት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የሚተላለፈው ብራና የተባለው የሬዲዮ ፕሮግራም ጥቆማ ይሰጣል፡፡ ይህን ፕሮግራም ሰምቶ ነበር ወጣት አቤል አያሌው ውይይቱ ወዳለበት ቦታ የሄደው፡፡
አቤል ዓይነ ሥውር ነው፤ ለዚህም ሬዲዮ ባለውለታው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህንን የውይይት መድረክ እንኳን የሰማው በሬዲዮ ነውና፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታ ለዓይነ ሥውራን ምቹ ሁኔታ የለም፡፡ መጻሕፍት በድምጽ ተቀርጸው አይቀመጡም፡፡ ለዚህም በአሜሪካን አገር ኮሎሮዶ ግዛት ያለውን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ ያነሳል፡፡ በኮሎሮዶ ‹‹ናሽናል ፌዴሬሽን ኦፍ ዘ ብላይንድ›› የተባለ ድርጅት በፌዴሬሽን ደረጃ ተቋቁሞ ነው የሚሰራው፡፡ ይህ ፌዴሬሽን ለአይነ ሥውራን መደረግ ያለበት ነገር ሁሉ እንዲደረግ ይከታተላል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብዙ የአካል ጉዳተኛ እያለ የዚህ አይነት አሰራር የለም፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነት ተሞክሮ ካላቸው አገራት ልምድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ያሳስባል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ካሱ ደግሞ ሌላ ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ የድምጽ ቤተ መጻሕፍት በተለያዩ የዓለም አገራት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ግን ቤተ መጻሕፍት ማለት መጽሐፍ ብቻ ያለበት ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አይሄድም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጻፈው ይልቅ ያልተጻፈው የስነ ጽሑፍ ሀብት ይበልጣል፡፡ ስነ ቃሎች፣ ተረትና ምሳሌዎች በቃል ደረጃ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ቀርጾ ማስቀመጥ ለዓይነ ሥውራን ብቻ ሳይሆን ለማንም የሚያስፈልግ ነገር መሆኑን ያብራራሉ፡፡
በሌላ በኩል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የዕድሜ ባለጸጎች ሀሳብም መቀመጥ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ‹‹አዛውንት ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት ናቸው›› የሚለው ለምን በወሬ ብቻ ይሆናል? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ቤተ መጻሕፍት ናቸው ከተባለ የእነዚህ ሰዎች ሀሳብ ተቀርጾ መቀመጥ አለበት፤ ሰዎቹ ያልፋሉ፤ እውቀታቸው ግን አያልፍምና ተሰንዶ መቀመጥ አለበት፡፡
የተማሩ የሚባሉት ራሳቸውም ይጽፉት ይሆናል፡፡ ገጠር ውስጥ ያሉ ብዙ ነገር የሚያውቁ ትልልቅ አባቶች አሉ፡፡ የእነዚህ አባቶች እውቀት ተቀርጾ መቀመጥ አለበት፡፡ ለዓይነ ሥውራን ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰው በድምጽ የተቀመጠ መረጃ አስፈላጊ ነው፡፡ አገርኛ ተረቶችና ስነ ቃሎች አለመሰናዳታቸውም ያሳዝናቸዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ እምነት አንድ መጽሐፍ በድምጽ ሲተረክ የበለጠ አንባቢን ይፈጥራል እንጂ መጽሐፍ እንዳይሸጥ አያደርግም፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርን ምሳሌ ያነሳሉ፡፡ ፍቅር እስከመቃብር በብዛት የተሸጠው ከተተረከ በኋላ ነው፡፡
የተወዳጅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን መሥራች አቶ እዝራ እጅጉ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› የተሰኘውን የአምባሳደር ዘውዴ ረታን ግዙፍ መጽሐፍ እና የአገር ባለውለታ ሰዎችን ግለ ታሪክ በድምጽ እንዲተረክ አድርጎ በሲዲ አሳትሟል፡፡ እዝራ ይህን በማድረጉ እድለኛ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡
የድምጽ ቤተ መጻሕፍት እንዲጀመር አነቃቂ ይሆናል ብሎም ያስባል፡፡ ሥራውን አይቶታልና መሥራት እንደሚቻልም ይመሰክራል፡፡ ይህ ሲሆን ግን መገናኛ ብዙኃን ላይ አንድ ችግር መኖሩን ይጠቅሳል፡፡ የክምችት ክፍላቸው በአግባቡ ጥቅም ላይ አይውልም፤ ለሰው ለመስጠትም ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ከ50 ዓመት በላይ የቆዩ ክምችት ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ብዙ ናቸው፡፡ የመሪዎች ድምጽ፣ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ግለታሪክ አላቸው፤ ግን ይሄ ወደ ህዝብ እንዲደርስ አልተሰራበትም፡፡ በመሆኑም ህጋዊ በሆነ አሰራር ከመገናኛ ብዙኃን የክምችት ክፍል መገዛት እንዳለበት እዝራ ያሳስባል፡፡
በውይይቱ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የድምጽ ክምችት ክፍል የሚያስፈልገው ለዓይነ ሥውራን ብቻ አይደለም፡፡ ከማንበብ ይልቅ በመስማት ሀሳብን መያዝ የሚፈልግም ይኖራል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎችና ሌሎች ሰራተኞችም ሥራ ሳይፈቱ እውቀትን ማግኘት ይችላሉ፡፡ በዋናነት ግን ለዓይነ ሥውራን ደግሞ የበለጠ ታስቦበት ሊሰራ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
ወጣት ሲሳይ ሰማኸኝ የችግሩን አስከፊነት እንዲህ ይናገራል፡፡ ‹‹በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 አዲስ ዜማ የሚባል ፕሮግራም አለ፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ መጽሐፍ ተቀንጭቦ ይተረካል፡፡ ያንን ትረካ ከሰማሁ በኋላ መጽሐፉን ማንበብ የበለጠ ያጓጓኛል፤ ሃሳቡ ተቀንጭቦ በመቅረቡ የባሰ ውስጤ ተረብሾ ይቀራል። በመሆኑ መተረክ ካለበት ተሟልቶ ነው መተረክ ያለበት››
የብሄራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኑአምላክ መዝገቡ እንደሚሉት በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ያለው የዓይነ ሥውራን ቤተ መጻሕፍት ለይስሙላ ብቻ ነው፡፡ የብሬል መጻሕፍት ቢኖሩም በቁጥር አነስተኛ ናቸው፡፡ አሁን የታሰበው ነገር መጻሕፍትን በድምጽ የማስቀመጥ ሥራን ማስፋፋት ነው፡፡
የሚያነቡትም ከዚህ በፊት የመተረክ ልምድ ያላቸው የጥበብ ሰዎች ናቸው፡፡ በቀጣይ ይህን አጠናክሮ ለመሥራት ከደራሲዎች፣ ከተራኪዎችና ሆነ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ከባለቤትነት መብት ጋር ባለው የአሰራር ደንብ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2011
በዋለልኝ አየለ