«መውሊድ አል-ነቢ» ወይም «መውሊድ አን-ነቢ» በአጭሩ «መውሊድ» ማለት የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን ነው፡፡ ቱርካውያን ደግሞ «መውሊዲ ሸሪፍ» ይሉታል፡፡ ትርጉሙም «የተቀደሰው ልደት» እንደማለት ነው፡፡ ፋሪሳውያንም «ሚላድ ፓየምባረ ኢክራም» ሲሉ ይጠሩታል፡፡ የታላቁ /የቅዱሱ ነቢይ ልደት እንደማለት ነው፡፡ አልጀሪያውያን በበኩላቸው ‹‹መውሊደ ነቢ ሻሪፍ›› ሲሉት የቅዱሱ ነቢይ ልደት ቀን ማለታቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹የውም አነቢ›› ማለትም የነቢዩ ቀን ብለው በየቋንቋቸው የሚጠሩት አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት በዓል ማለት ነው፡፡
ሱኒዎች ይህን በዓል በወርሐ ረቢዓል አወል 12ኛው ቀን ሲያከብሩት ሺዓዎች ደግሞ በወርሐ ረቢዓል አወል 17ኛው ቀን ከኢማም ጃዕፈር አል-ሳዲቅ ልደት ጋር አብረው ያከብሩታል፡፡ መውሊድ በወርሐ ረቢዓል አወል ይውላል፡፡ የዓረብኛው የቀን አቆጣጠር በጨረቃ የመሬት ዑደትን መሠረት ያደረገ ስለሆነ ከኢትዮጵያም ሆነ ከአውሮፓውያን አቆጣጠር ጋር ይለያያል፡፡ መውሊድ ከሳዑዲ ዓረቢያ በስተቀር በሁሉም የሙስሊም አገሮች ብሔራዊ ክብረ በዓል መሆኑን የሚናገሩት ጋዜጠኛና ደራሲ ተሾመ ብርሃኑ ናቸው፡፡
የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን በብዙ አገሮች
መከበር ከመጀመሩ በፊት ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድ ወደ ተወለዱበት ቤት በመሄድ ጸሎት ያደርሱ ነበር። ይህም ነቢዩ ሙሐመድ የተወለዱበት ቤት የኸሊፋ ማህዲ ሚስት በነበረችው እና የሐሩን አል-ረሺድ እናት በሆነችው፣ በዓል-ኸይዙራን ወደ መስጊድነት ተቀየረና ብዙ ምእመናን ተሰብስበው ጸሎታቸውን የሚያደርሱበት ስፍራ ሆነ፡፡ የልደት ቀናቸው መከበር የጀመረው በግለሰቦች ተነሳሽነት እንደሆነም አንዳንድ መረጃዎች ቢያመለክቱም፣ በራቢዓል አወል በ12ኛ ቀን ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ባለው በዕለተ ሰኞ ይከበራል፡፡ ቀዳሚ ነው የሚባለው የነቢዩ ሙሐመድ መውሊድ ሱፊዎች የከብት መስዋዕት እያቀረቡ፣ ችቦ እያበሩ፣ እየበሉና እየጠጡ ያከብሩት እንደነበረ ‹‹ኢንሳይክሎፒዲያ ኢስላም›› እና ‹‹ኢንሳይክሎዲዲያ ብሪታኒካ›› የተባሉት አውደ ጥበባት ይገልፃሉ፡፡
ኮንሳይንስ ኢንሳይክሎፒዲያ ፈ-ኢስላም በሚል ርዕስ፣ ጎርዶን ዲ. ኒውባይ በ2006 ባሳተሙት አውደጥበብ (ገጽ 146-147) እንደሚገልጡት ‹‹የነቢዩ ሙሐመድ የልደት ቀን የውዳሴ ግጥሞችን በማቅረብ፣ ማርን ጨምሮ ጣፋጭ ምግቦችን በመመገብ ነው የሚከበረው፡፡ አህለል በይት የሚባሉት ሙስሊሞች ደግሞ ቁርዓን በመጥራት፣ ስጦታ በመለዋወጥ ያስታውሱታል፡፡ በግብጽ ውስጥ መውሊድ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት መከበር የጀመረው በ12ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
እዚህ ላይ መውሊድን የሚያከብሩ ሙስሊሞች
እንዳሉ ሁሉ የማያከብሩ ሰለፊዎች ወይም የሸኽ አብዱልውሀብ ተከታዮች ወይም አህለል ሐዲስ ተብለው የሚጠሩ ሙስሊሞች እንዳሉ አቶ ተሾመ ይናገራሉ፡፡ የነብዩ ሙሐመድን የልደት ቀን ከሚያነውሩ ሰለፊዎች መካከል የሳዑዲ ዓረቢያ ታላቁ ሙፍቲ ዓብዱል ዓዚዝ ኢብን ዓብደላ ኢብን በዓዝ፣ የመስጅድ አል-ሐረም ኢማም የሆኑት ዓብዱራሕማን አል-ሱዳይሲ፣ ዛኪር ናይክ ይገኙበታል፡፡
በሰለፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ኢብን ታያሚያ የተባሉ ትልቅ ሊቅም መውሊድ እንዳይከበር ከልክለዋል፡፡ የአልአዝሃር ዩኒቨርሲቲው ሙፍቲ ዓለ ጎማ፣ ዩሱፍ አልቃርዳዊ፣ ሙሐመድ አል-ዓለዊ፣ የቆጵሮሱ ታላቁ ሙፍቲ አል-ሐቁዲን፣ የሙስሊም ወንድማማች ንቅናቄው መሥራች ሙሐመድ ዓለዊ አል-ማሊኪ፣ የየመኑ ሙፍቲ ሐቢብ ዓሊ አል-ጂፍሪ፣ የዳዕዋት ኢ-ኢስላም መሥራች ሸኽ ኑሕ ሐ ሚም ኬለር፣ የቦሲኒያው ሙፍቲ ሙስጦፋ፣ ታላቁ የሕንድ ሙፍቲ አኽታር ራዛ እና ሌሎች በርካታ የሱኒ ሊቃውንት የነብዩ ሙሐመድ ልደት መከበር እንዳለበት ያምናሉ፡፡
በብዙ አገሮች የነቢዩ ሙሐመድ ልደት በሚከበርበት ጊዜ ‹‹ቃሲዳ አል-ቡርዳ›› በሚል ርዕስ በ13ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈው የግጥም መጽሐፍ የሚነበብ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያሉ አገሮች ደግሞ በራሳቸው ሊቃውንት የተገጠሙትን የውዳሴ ግጥሞች በዜማ ያቀርባሉ፡፡
በግጥሞቹም ውስጥ የነቢዩ አወላለድ፣ የእናታቸው፣ የአባታቸው እና የቤተሰቦቻቸው ታሪክ፣ የነቢዩ ሙሐመድ የልጅነት፣ የወጣትነትና የአዋቂነት ዕድሜ ክንውኖች፣ ስለደግነታቸው፣ አርቆ አስተዋይነታቸው፣ ነብይነታቸው፣ ስለመጀመሪያው ራዕይ፣ በመጀመሪያ ሙስሊም ስለሆኑ ተከታዮቻቸው፣ ስለገጠማቸው ፈተና ይካተታሉ፡፡ ስለሆነም በፓኪስታን በተለይም በዑርዱ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ይከበራል፡፡
በፓኪስታን ዋና ከተማ በኢስላማባድም 31 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል፡፡ በክልል ዋና ከተማዎች ደግሞ 21 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል፡፡ በፊልም ቤት የሚታዩት ፊልሞች እንኳን መንፈሳዊ እንጅ ዓለማዊ አይሆኑም። በተለይም ላሆር በሚገኘው ሚናሬ-ኢ- ፓኪስታን በሚባለው መስጂድ በራቢዓል አወል 11ኛ እና 12ኛ ቀን ሌሊት ላይ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ያከብሩታል።
ይህንን አከባበር ከሕዝብ ብዛት አኳያ በዓለም አንደኛ እንደሆነ የሚመሰክሩ አሉ፡፡ በኢንዶኔዥያ፣ በባንግላዴሽና በሕንድም እንደዚሁ። በዚህ ጊዜ የታላላቅ የእስልምና እምነት አባቶች መቃብሮችም ይጎበኛሉ፡፡ በአፍሪካም በኬንያ በታንዛኒያ፣ በቱኒዝያ፣ በግብጽ፣ በማሊ፣ በሱዳን በከፍተኛ ደረጃ ይከበራሉ፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓመት ውስጥ 3000 ጊዜ ያህል ይከበራል፡፡ ይኸውም በአገራችን በዳና፣ በንጉሥ፣ በገታ፣ በነጃሺ፣ በድሬ ሸኽ ሑሴን ወዘተ እንደሚከበረው መሆኑ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም30/2012
ዳግም ከበደ