ከደሴ ኮምቦልቻ መንገድ 36 ኪሎ ሜትር ላይ የጨቆርቲ መንደር ትገኛለች፡፡ ከመንደሯ በስተግራ በኩል አራት ኪሎ ሜትር ዳገታማውን የእግር መንገድ ከተጓዙ በኋላ ገታ መስጊድ ይደረሳሉ፡፡ መስጊዱ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ በታዋቂው ምሁር በሐጅ ቡሽራ መሐመድ አማካይነት መመስረቱ ይነገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምሁሩ በህይወት ዘመናቸው በርካታ ምሁራንን ከማፍራታቸው ጎን ለጎን ከ500 በላይ የእስልምና መጽሐፍትን በእጃቸው መጻፋቸው ይነገራል፡፡
መስጊዱ መውሊድን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ ደማቅ ክብረ በዓል የሚደረግበት ሥፍራ ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠር የሃይማኖቱ ተከታይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ ይጐርፋሉ፡፡ የገታ መስራች የሐጅ ቡሽራ መሐመድና የቤተሰባቸው የመቃብር ቦታ በአካባቢው የሚገኝ ሲሆን በመስጊዱ ዙሪያም ብዙ ሙስሊሞች ይኖራሉ። አሁን ላይ የገታ መስጊድ የዕለት ተዕለት አምልኮ ሥርዓቱን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ቅርስና ምዝገባ
እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በተቆጠሩት ሺሕ ዓመታት ውስጥ ሃይማኖቱን መሠረት ያደረጉ በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ተፈጥሯዊ ቅርሶችን አፍርቷል፡፡ ዩኔስኮ እንደ ድሬ ሼህ ሁሴንና የሶፍ ዑመር ዋሻ ያሉ የሚዳሰሱ ቅርሶች በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ተይዘዋል፡፡ በሌላ በኩልም ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል የሐረሪ ውርሻቶ (አሹራ) በዓል ለማስመዝገብ ቀደም ብሎ የተጀመረ ሥራ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አንድን መንፈሳዊ ወይም ቁሳዊ ባህል በቅርስነት ለመመዝገብ የተለያዩ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 209/92 ቅርሶቹን በሦስት ደረጃ ይከፍላቸዋል፡፡ ተነቅለው ወደየትም ቦታ መሄድ የማይችሉ ሐውልቶች፣ የእምነት ተቋማት ቤተ ክርስቲያናትና መስጊዶች፣ የአርኪዮሎጂና ፖሊዎንቶሎጂ ቦታዎች የመሳሰሉት ቋሚ ቅርሶች ይላቸዋል፡፡
ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የሚባሉት ደግሞ እንደ ብራና ጽሑፎች፣ ጥንታዊ የዕደ ጥበብ ሥራዎች፣ የየብሔረሰቡ የወግ ዕቃዎችና የመሳሰሉት ሲሆኑ ለሕገወጥ ዝውውር የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሦስተኛው የቅርስ ዓይነት የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ የሚባለው ነው፡፡
ዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ2003 (1995 ዓ.ም.) የማይዳሰሱ ቅርሶች ሀብቶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለማስተዋወቅ የወጣ አንድ ስምምነት አለ፡፡ ስምምነቱን ኢትዮጵያ በ1998 ዓ.ም ፈርማለች፡፡ በዚህ መሠረትም በአገሪቱ የሚገኙ አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎቻቸው፣ ትውን ጥበባት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ የዕደ ጥበብ ክህሎትና ማኅበራዊ ክዋኔዎች፣ ፌስቲቫሎች በማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ዝርዝር ይመዘገባሉ፡፡
የቅርሱ ፋይዳ፣ ለታሪክና ባህል ጥናት ያለው ጠቀሜታ፣ በሥነ ጥበባዊና በኪነ ሕንፃዊ አሠራር ጥበብ ልዩ መሆኑ፣ በዕድሜው ጥንታዊ የሆነና የአንድን ዘመን የታሪክና የባህል አሻራ የሚያሳይ፣ የተሠራበት ቁስ ውድ መሆኑ፣ ሌላው ለሳይንስና ምርምር ያለው ጠቀሜታ የጎላ ከሆነ በቅርስነት ለመመዝገብ መስፈርቱን አሟልቷል ማለት ነው፡፡
እስካሁን ድረስ የተመዘገቡ ቅርሶች ቁጥር በተንቀሳቃሽ ቅርሶች ደረጃ ወደ 70ሺህ፣ በቋሚ ቅርስ ደረጃ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶችን፣ መንደሮች እንደ ሾንኬ ዓይነት፣ የአርኪዮሎጂና ፖሌዎንቶሎጂ ቦታዎች በተመለከተ 2ሺህ 500 ተመዝግበዋል፡፡
አርኪዮሎጂስቱ ሐሰን ሰኢድ (ዶ/ር) በቅርስ አያያዝና የማስተዋወቅ ሥራ በተለይም የእስልምና መሠረት ባላቸው ቅርሶች ላይ ሰፊ ክፍተት እንደሚገኝ በመጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ የተለያዩ አዋጆችና ስምምነቶች ለእስላማዊ ቅርሶች መጠበቅና መመዝገብ ሽፋን የሚሰጡ ቢሆኑም ማንኛውም ቅርስ የሚሰጠውን ቦታ እያገኙ አለመሆኑን በተለያዩ ጥናቶቻቸውም ላይ ጠቁመዋል፡፡
‹‹አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሊያውቃቸው ቀርቶ የእምነቱ ተከታይ የሆኑ እንኳን ያውቃቸዋል ለማለት አያስደፍርም፤›› በማለት ለቅርሶቹ ተገቢው ትኩረት እንደተነፈጋቸው ‹‹እስላማዊ ቅርሶች ዓይነትና ስርጭት ከሰሜን ሸዋ እስከ ደቡብ ወሎ›› በሚል በ2008 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ እንዳስነበቡ ይታወቃል፡፡
በመጽሐፋቸው በአማራ ክልል አልዩ አምባ፣ አበዱል ረሱል፣ ጎዜ፣ ጎንዶሬ፣ ገታ፣ ጀማ ንጉሥ፣ ሾንኬ፣ ጠለሐ፣ ገዶ፣ ዶዶታ፣ ጡርሲና በተባሉ ቦታዎች የሚገኙ የእስላማዊ ቅርሶች ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ አሳይተዋል። እንዲሁም በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ የሚገኙ ገቸኔ፣ ጨኔ፣ ገበሮች፣ ካይር አምባ፣ አሊ ግምብና መጠቅለያ በተባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችም የጽሑፋቸው አካል ነበሩ፡፡
በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ እስላማዊ ቅርሶች መካከል ‹‹የመለሳይ አገር መስጊድ›› አንዱ ነው፡፡ የመለሳይ አገር መስጊድ ከፍታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአግባቡ አለመያዙን በዙሪያው የሚገኙ ፍርስራሽ የድንጋይ ቤቶች እንደሚመሰክሩ ዶክተር ሐሰን በመጽሐፋቸው ይተርካሉ፡፡ መስጊዱ ስያሜውን ያገኘው ከኢማም አህመድ ጦር እንደሆነ ይነገራል፡፡ ወደ ጎን 24 ሜትር፣ ቁመቱ ደግሞ 3 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ ያለው የመለሳይ መስጊድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሌሎች በርካታ ነገር ግን ያልታወቁ እስላማዊ መሠረት ካላቸው ቅርሶች በተቃራኒው በብዙኃኑ የሚታወቁ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ የሶፍ ዑመር ዋሻም ተገቢውን ትኩረት አግኝተዋል ማለት እንደማያስደፍር አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ።በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን አናጅና በተባለ ቦታ የሚገኘው ድሬ ሼህ ሁሴን ነው፡፡ በድሬ ሼህ ሁሴን በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚከበሩ በዓላት መካከል ‹‹ዛራ ገልገላ ጎበና›› ይጠቀሳል፡፡ ድሬ ሼህ ሁሴን የእስልምና እምነት ተከታቶች በዓመት ሁለት ጊዜ በአረፋና ለሼህ ሁሴን የትውልድ ቀን በዓላት ፈጣሪያቸውን የሚያመልኩበት ቦታ ነው። በዓላቱ እስከ 15 ቀናት እየተከበሩ የሚቆዩ ሲሆን፣ ምዕመናን በሥፍራው ቆይተው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን ያከናውናሉ።
አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት በቅርስ አጠባበቅና አያያዝ ዙሪያ ለሚታዩ ችግሮች ማኅበረሰቡ በተለይም ሙስሊሙ ተወቃሽ ነው። በጥንታዊ መስጊዶች የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ያላቸውን ፋይዳ አለመረዳት ዋናው ችግር ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እንደ ብሔራዊ ቅርስ ሳይሆን የአንዱ ወገን ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዚህ ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመሥራቱ ዋና ዋና ክፍተቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም30/2012
ዳግም ከበደ