ከወዲያኛው ማዶ አንድ ስልክ ተደወለልኝ። ደዋዩ እንግዳ ሰው አልነበሩም። በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ላይ አንቱታን ያተረፉት ሰዓሊ ሉልሰገድ ረታ ነበሩ። ለረጅም ጊዜ እንተዋወቃለን። በአዲስ አበባ በቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ ወልድ ፍቅር ሕንጻ፤ አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ ‹‹መክሊት›› የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ማዘጋጀታቸውን አብስረውኝ ከድግሳቸው እንድቋስ ግብዣቸውን እነሆ አሉኝ። በአገር ውስጥ እና በተለያዩ የዓለም አገራት በርካታ ሥራዎቻቸውን ለዓመታት ያሳዩ ሰው ናቸው። እንዲህ አይነት ታላቅ ግብዣ በቸልታ አይታለፍምና ጊዜ ሳላጠፋ ከቦታው ደረስኩ።
መልክታቸው የገዘፈ ለዓይን ማራኪ የሆኑ ሥራዎቻቸውን በአንድነት ያሰባሰበ አውደ ርዕይ በአዲስ ፋይን አርት እየኮመኮምኩ ጭውውታችንን ቀጠልን። በዚህ ጊዜ አንድ ውልብ ያለብኝን ጥያቄ ለማንሳት ተገደድኩና ‹‹ለመሆኑ በሥራዎቾዎ ላይ የሴቶች ምስል በብዛት መንፀባረቃቸው ከምን መነሻ ይሆን በማለት ማብራሪያ ጠየኩ›› ያገኘሁት መልስ አንጀት የሚደርስ ነበር። የርሳቸው መሠረት፤ አመጣጣቸው ከእናታቸው እንደሆነ አስረዱኝ።
ስለዚህ እናት ምን እንደሆነች፣ እህት ምን እንደሆነች፣ ጓደኛ ምን እንደሆነች፣ ሚስት ምን እንደሆነች፣ ልጅ ምን እንደሆነች የተረዱበት ዘመን በመሆኑ ስለሴት ሙሉ ቀን ማውራት ቢችሉ ከልባቸው እንደሚደርስ አጨዋወቱኝ። ቁምነገሩ የእናቶችን ልፋት፣ ብልሃትና ዘዴ እንዲሁም ውበት በተቻላቸው መጠን ለረጅም ጊዜ አብረዋቸው ካደጉት፣ ጊዜዬን ካሳለፉበት ከአካባቢያቸው፤ ኢትዮጵያውያንን የተረዱበት መንገድና ግንዛቤ ያገኙበት፤ ከጓደኞቻቸውም በትምህርት ቤት የተረዱት ነው። አሁን ዘመን ላይ ያለነው ከድሮ ጋር በማዋሐድ ለሴት ከፍተኛ ክብርና ግምት ስላላቸው፣ በእነርሱ ላይ ብዙ ትኩረት አድርገው በስዕሎቻቸው ላይ ሐሳባቸውን እንደሚያሰፍሩ አጫወቱኝ።
‹‹አንድ ሥራ ስንሠራ የተረዳነውን ነገር ለተመልካችም ለራስም በተገቢው መልክ ማድረስ አለብን› የሚሉት ሰዓሊ ሉልሰገድ ያ እንዲሆን ሆነ ብለው የተጠቀሙባቸው የአሳሳል ዘዴዎች እንዳሉ ይገልፃሉ። በአብዛኛውም ሴቶች መሆናቸውንም ይናገራሉ። ይህ ማለት ግን ወንድ ሥራዎቻቸው ውስጥ አይገባም ማለት እንዳልሆነው ያስረዳሉ። በብዛት በሴቶች ላይ የማተኮራቸው ሌላኛው ምክንያት እሳቸውም በቅጡ እንደማይረዱት በማንሳት፤ አስተዳደጋቸው ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ይገልፃሉ። በተለይ አቀማመጥ፣ እንቅስቃሴና መሰል ሁኔታዎችን የሚረዱበት መንገድ በሴቶች ላይ እንደሚጎላም ያስረዳሉ።
‹‹ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት አገር ናት›› ይላሉ ሰዓሊው። ለአገራቸው ባህል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ቀናኢ ናቸው። ታሪኩ በአበውና በትልልቅ ሰዎች ተጽፎ ተነግሮ ያላለቀ እንደሆነም ነው የሚያምኑት። እንዲያውም በደንብ አልተጻፈም በደንብም አልተነገረም የሚል እምነት አላቸው። ወደፊት አቅምና ጊዜ ሲኖር፤ ወይም ኢትዮጵያዊነት ሁሉም በተገቢው የተረዳ ጊዜ ስለ አገሪቱ ሥነ ጥበብ ዕድገት ከየት ተጀምሮ የት እንደደረሰ መናገር ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት አላቸው። ከዚህ ሲያልፍ ግን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራትም በስዕል ጥበብ የተለየች መሆኗን ይገልፃሉ። ይህንኑ እውነትም በሥራዎቻቸው ላይ ያንፀባርቃሉ።
አንጋፋው ሰዓሊ በቅብና በዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ በተለይ ደግሞ ‹‹ማጂክ ስክሮል›› የመሳሰሉት በሊቃውንት ወይም አዋቂዎች፤ ለፍቅርም ለጥላቻም የሚሠሩ የክታብ ሥራዎች እንዳሉ ይናገራሉ። በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ያሉ ስዕላትም የሚያስረዱት ትውልዱ አንድ ነገር እንዲያስተውል እንዲያገናዝብ ከዚያም ሲያልፍ እንዲማርበት መሆኑን ይገልፃሉ።
እርሳቸውም ይህንኑ መሰረት አድርገው የሰማያዊውን ወደ ምድራዊ ዓለም በተጓዳኝ አምጥተው የኢትዮጵያን ሥነ ጥበብ በትንሹ የተፈነጠቀ የሚመስል አካሔድ እና ፍልስፍና እንዳላቸው ይናገራሉ። ዓለም አቀፍ እውቅና ካለው ትምህርት ቤት የሥነ ጥበብ እውቀት ቀስመው ከመጡ በኋላም ይህንኑ ፍልስፍናቸውን በፍላጎት በሥራ ዓለም በነበሩበት በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ሲያገለግሉ የሠሯቸው ባህላዊና ዘመናዊ ፖስተሮች ነበሩ። ይህም ታስቦበትና ተጨንቆ የተሠራ መሆኑን ከመናገር አልተቆጠቡም። አሁን ላሉበት ዘመን አሻራ የጣለ ሥራ መሆኑን ነው የሚያምኑት።
መክሊትና ዘመናዊ
ትምህርት
አንጋፋው ሰዓሊ ከበርካታ ዓመታት በፊት በውጭ አገር በሙያቸው ዘመናዊ ትምህርት የመቅሰም ዕድሉ አጋጥሟቸው ነበር። ወደ ሶቭየት ሕብረት በ1979 በማቅናት መክሊታቸውን ይበልጥ አነቃቅተውታል። በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ቢያንስ ለአስር ወር ያህል በቅድመ ዝግጅት ኡዝቤኪስታን የሚባል ከተማ ቆይታ አድርገው ነበር። ከዛ ወደ አካዳሚ ለመግባት ፈተና በመኖሩ እሱን አልፈው ቀጥታ ወደ ሌኒንግራድ የሥነ ጥበብ ትምህርት አካዳሚ ለመግባት ቻሉ።
በዚያ ከአንጋፋው ሰዓሊ ታደሰ መስፍን ጋር የመገናኘት አጋጣሚውን አገኙ። ‹እባክህን መስመሬንም ስለምታውቅ የትኛው የትምህርት ክፍል ለእኔ ይሆናል?› ብለው ሲያማክሩትም ‹አንተ ግራፊክ ላይ ብትገባ ጥሩ ነው፤ ቅብ ላይ የምታውቀው ስለሆነ በግራፊክሱ ቀጥል› እንዳሏቸው ገልፀው የሙያ መስመራቸውን በዚህ መንገድ እንዳስተካከሉ ይናገራሉ።
በ1986 ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ኢትዮጵያ ሲመጡ መጀመሪያ ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀሉት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ ነበር። በዛም ኮሜርሻል አርቲስ የሥነ ጥበባት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም ባለሙያ ሆነው 9 ዓመት አገልግለዋል። የውጭ ትምህርት ዕድል ከማግኘታቸው ቀደም ብሎ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ብሔራዊ ቴአትር አገልግለዋል። ከ1996 ጀምሮ እስከአሁን የስቱድዮ አርቲስት ናቸው። በዚህ ሁሉ ጊዜ ብዙ ውጣውረዶች እንዳሳለፉም አይሸሽጉም። አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ እንቅፋቶችን ማለፋቸውን ይናገራሉ። ‹‹ሥራ ላይ ማተኮር ግን አስፈላጊ ነው። ያኔ እግዚአብሔርም ይረዳል›› የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
የሥነ ጥበብ ጎህ ቀዳጅ
ሰዓሊ ሉልሰገድ በግላቸው ልህቀት እና በርካታ ስኬቶችን ቢያገኙም በዚያ ብቻ ረክተው የተቀመጡ አይደሉም። ሥነ ጥበብ የሚገባው ክብር እና ደረጃ ላይ እስኪደርስ ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ሰፊ ትግል የሚያደርጉ ትጉህ ሰው ናቸው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በግል ከሚያቀርቡት አውደ ርዕይ በተጓዳኝ ለሌሎች ዕድል ለመክፈት የሚያስችል ሥራዎችን እየሠሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ወጣቶችን በስፋት በማሳተፍ ከአስር ዓመታት በላይ የዘለቀውና በሸራተን አዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የሚካሄደው ‹‹አርት ኦፍ ኢትዮጵያ›› አውደ ርዕይ ተጠቃሽ ነው።
የተጀመረው በስምንት ሰዓሊያን እ.ኤ.አ 2008 ነበር። የመጀመሪያው መጠሪያም ‹‹መርጅ›› የሚል ነበር። በወቅቱ የሸራተን ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሚስተር ዣንፔር ማኒንጎፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ ህልምና ብዙ ዓላማ እንደነበራቸውና በእርሳቸው እገዛ ሐሳቡ መሳካቱን ሰዓሊ ሉልሰገድ ይናገራሉ። በ2007 አንድ ቦታ ተቀምጠው በመጨዋወት ላይ እያሉ ሐሳቡን እንደጠነሰሱትም ይገልፃሉ። ይህ ሐሳብ ከመጠንሰሱ በፊት እርሳቸው በሸራተን ሥራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር። ከሐሳቡ በኋላ ሰዓሊ ዮሐንስ ገዳሙ፣ ተሾመ በቀለ፣ ጥበበ ተርባ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ እና ሁለት ተጨማሪ ሰዓሊዎች ሆነው ሥራዎቻቸውን አቀረቡ።
አርት ኦፍ ኢትዮጵያ በዚህ መልክ ተጀምሮ በርካታ ሰዓልያን፣ አስተማሪዎቼን፣ ታላላቆቼን፣ ጓደኞቼን፣ ወጣቶችን በሙሉ ማሳተፍ ችሏል። ይህ ታላቅ ራዕይ የእርሳቸው ገፀ በረከት ነው። አሁን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገራት አውደ ርዕይው ሲከፈት በርካታ የጥበብ አድናቂዎች ተሳታፊ ናቸው። ልክ እንደ ቱሪዝም መስህብም መሆኑንም ነው ሰዓሊ ሉልሰገድ የሚናገሩት።
የራስ ምልከታ
በፊት የአብያተ ክህነት ሥራዎችና መልክአ ምድርን የሚገልጽና አገርን የሚወክሉ አንዳንድ ሥራዎች እንደነበሩ የሚገልፁት ሰዓሊ ሉልሰገድ ረታ አሁን ዘመኑ ላይ ያለው ደግሞ እያንዳንዱ በተለይ በዘመነኛው ሥራ ላይ ልንጠቅስ የምንችላቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። ለዚህ እንደማሳያ ሲጠቅሱ ራሳቸውን ጨምረው እንደነ እስክንድር ቦገሳን፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ታደሰ መስፍን፣ መዝገቡ ተሰማ፣ ጌታሁን አሰፋ፣ እሸቱ ጥሩነህና ዘመናዊ አሳሳል ጥበብ እንደገባቸው ይናገራሉ።
‹‹የአሁን ወጣቱ ደግሞ ትንሽ የራሱ አካሔድ አለው›› በማለትም ምን ያህል ጥልቀት ያለው ሥራ እንደሚሠሩ ተመልካች እና እራሳቸው የሥነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ይገነዘቡታል የሚል አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ። እንደእርሳቸው እምነት ግን ትልቁ ቁምነገር አንድ ሰዓሊ ክህሎት ካለው፣ በዛ ላይ ከተማረ የአገሩን ጥበብ ሰፊ የማድረግ አቅም መኖሩ ነው ይላሉ።
ሌላው የማንነት ጉዳይ የሰዓሊው ወሳኝ ነጥብ ነው። ማንኛውም ሙያ ልፋት እንዳለው ያምናሉ። ስለ ኢትዮጵያ ግንዛቤና መረዳት እንዲሁም ማወቅ ያስፈልጋል የሚለው ጠንካራ አመለካከታቸው ነው። ሥራዎቻቸውም ከዚሁ የሚቀዱ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ከመናገር ማዳመጥ ብሎም ለማወቅ መጣር ጠቃሚ ነው የሚል ምክር አላቸው። ወጣቱ ይህን ማዳበር አለበት። አገር በቀል ተረቶቻችንን ማወቅም ጠቃሚ መሆኑን አይሸሽጉም። ወጣቶች ‹‹ብዙ ሊረዱ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ይህ የሚሆነው በልፋት ነው፤ ጥረት ያስፈልጋል›› የሚለው ደግሞ ጠንካራ መልዕክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅም30/2012
ዳግም ከበደ