በየቦታው የሚሰማው ሕገ ወጥነት የዳኛ ያለህ ያስብላል። በከተማ በቢሮ፣ በአስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ፤ ከከተማ ወጣ ሲል ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ያለው የጥፋት አይነት ለሰሚው ያታክታል። በጠረፍ ድንበር ለመተላለቂያችን የሚገባልንን ሕገወጥ የጦር መሳሪያ እንዳልተፀየፍን ያህል የማዕድን ሀብታችን እየተጋዘ መሄዱ ደግሞ ሌላ ጉዳታችን ሆኗል።
ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ከሚገኝባቸው አንዱ ቤንሻንጉል ጉሙዝ በክልሉ እየተመረተ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ፣ ከአመራረቱ እስከ ግብይቱ በችግሮች መተብተቡ የሰሞኑ መረጃችን ነው።
የክልሉ ማዕድን ልማት ኤጀንሲ በ2011 ዓ.ም አንድ ሺ ኪሎ ግራም ወርቅ ለማስገባት አቅዶ 54 ኪሎ ግራም ብቻ ማግኘት መቻሉ የወርቅ ሀብታችን አደጋ ላይ መሆኑን ያመላክታል። ህገ ወጥ ንግድ፣የጸጥታ ችግርና ኋላቀር የአመራረት ዘይቤ ተደምሮበት አፈጻጸሙን ዝቅተኛ እንዳደረገውም ይነገ ራል።
በክልሉ ዱል ሼታሉ ቀበሌ በወርቅ ንግድ የሚተዳደሩት አቶ ዩሱፍ እስማኤልና
አቶ ቡልቻ ዩሱፍ በወርቅ ግብይት በርካታ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ስለሚሳተፉ በተፈለገው መጠን ወርቅ እንደማይገኝና ነጋዴዎቹ ከአምራቾቹ ዋጋ ጨምረው ስለሚገዙ በህጋዊ መንገድ ግዢ በሚፈጽሙት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ያስረዳሉ።
‹‹አምራቾቹ የተመረተውን ወርቅ በተተመነ ዋጋ ለመሸጥ ስለማይፈልጉ በተሻለ ዋጋ ለህገወጥ ነጋዴዎች ያስረክቡታል በዚህም ህገወጥ ነጋዴዎቹ እየከበሩ፣ ህጋዊዎቹ ለኪሳራ ተዳርገናል›› ይላሉ ብሶት ያንገበገባቸው ህጋዊ አምራቾች። እነርሱ ህገ ወጥ ንግዱ እየጎዳቸው እንደሚገኝ ፣ በተገቢው መንገድ ወርቅ ለማግኘት ተጽዕኖ ማሳደሩን፣ መንግሥትም በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለመሆኑ ችግሩ በመባባሱ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን የክልሉ ወርቅ ወደ ሱዳን ብቻ ሳይሆን በመሃል አገር አቋርጦ ወደተለያዩ አገሮች እንደሚሄድም ይናገራሉ። በቅርቡ ከማዕድን ሚኒስቴር ከተወከሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ከወርቅ አዘዋዋሪዎችና አምራቾች ጋር የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን በመግለፅ፤ የወርቅ ሽያጩ ዋጋ ብሄራዊ ባንክ ከሚገዛበትና ከጥቁር ገበያው ጋር ሲነጻጸር በአንድ ግራም ከ300 እስከ 400 ብር ልዩነት ስላለው ለብሄራዊ ባንክ ለመሸጥ እንደማይፈልጉ ይጠቁማሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በጥቁር ገበያ የሚገዙት አጠራቅመው በተለያየ መንገድ ከአገር እንዲወጣ ያደርጋሉ። በወርቅ አምራቾች አካባቢ በዘርፉ የግብይት ማዕከላት ለማመቻቸት ቢሞከርም ወደ ግብይት ማዕከላቱ አይሄዱም። በህጋዊ መንገድ ግዢ የሚፈጽሙ ግለሰቦች በተተመነው ዋጋ ስለሚገዙ አምራቾች ለባለፍቃዶች መሸጥ አይፈልጉም።
‹‹ህገ ወጥ ነጋዴዎች ከአምራቾቹ ጋር በተለያየ መንገድ ግንኙነት ይፈጥራሉ። ወዲያው እንደተመረተ ዋጋውን ከፍ አድርገው ይገዛሉ።አምራቹ የሚፈልገውም ገንዘቡን ስለሆነ ከፍ ያለ ዋጋ ሲያገኝ ይሸጣል እንጂ ህጋዊና ህገ ወጥ የሚለው ብዙም አያሳስበውም ›› የሚሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ለችግሩ እልባት ለማበጀትም የግንዛቤ መፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያመለክታሉ ።
የክልሉ የማዕድን ልማት ኤጀንሲ የፈቃድ ስራዎች ዳይሬክተር አቶ አብዱልባጅ ሙሳ፤ በክልልና በፌዴራል ደረጃ ተደራጅተው በልዩ አነስተኛ ዘርፍ በማህበር በዘመናዊ የወርቅ መፈለጊያ ማሽን የወርቅ ማዕድን ለሚያመርቱ 13 ፤ በባህላዊ መንገድ ለሚያመርቱ ደግሞ 15 ፍቃዶች መሰጠቱን ይገልጻሉ።
የግብይት ሰንሰለቱ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ ጊዜው በሚፈልገውና መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን፣ አብዛኛው የክልሉ ኅብረተሰብ ኑሮውን የሚመራው በዚሁ ሥራ ቢሆንም አመራረቱ ባህላዊ ከመሆኑ አንጻር የህብረተሰቡን ችግር ከመሰረቱ በሚለውጥ መልኩ እንዳልሄደ ያስረዳሉ።
ዳይሬክተሩ 72 የግብይት ፍቃድ የተሰጠ ቢሆንም፤ ወርቅ ከሚመረትበት ቦታ አንስቶ በየቦታውና በዋና ዋና የገበያ ስፍራዎች ግብይት እንደሚካሄድ፣ በአንድ ግራም ወርቅ በጥቁር ገበያ ከሚሸጡበትና ወደ ብሄራዊ ባንክ ከሚያስገቡበት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት ስለሚያገኙ አምራቾች ይህንን ያህል ከስረው ስለማይሸጡም ችግሩን ለማስተካከል ፍቃድ ላላቸው ገዢዎች ብቻ እንዲሸጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራቱን ይናገራሉ።
ክልሉ ከሱዳን ጋር ድንበርተኛ በመሆኑ የማዕድን ሀብቱ በኮንትሮባንድ ስለሚወጣ ግብይቱ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሯል። በአዲስ አበባም ወርቅ በህገወጥ መንገድ ይዘዋወራል። እነዚህን የግብይት መስመሮችን መንግሥት መቆጣጠር ካልቻለ ችግሩ እንደሚባባስ ዳይሬክተሩ ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ኤጀንሲያቸው ግንዛቤ የመፍጠርና መዋቅር የመዘርጋት ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፤ በድንበር በኩል ወደ ሱዳን መውጫዎች ልቅና ለህገወጥ ንግዱ መንስዔ በመሆናቸው ችግሩን ለማስወገድ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ መሰራት ያስፈልጋል። በጉምሩክ በኩልም ቁጥጥሩ ጠንካራ ከሆነ ወደብሄራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን ያድጋል። ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚም መሆን ይቻላል ።
ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የ2011 ዓ.ም መጨረሻ ግብረ ሃይል ቢደራጅም የተጠናከረ ሥራ ለመስራት የመጓጓዣ አቅርቦት ችግር መኖሩ፣ ተሽከርካሪ ባልተመቻቸበት ሁኔታ ግብረ ሃይሉን ማቋቋም ብቻውን ዋጋ እንደሌለው ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ዘላለም ግዛው