አዲስ አበባ፡- ‹‹በብልሹ አሰራር ጎዳና የወደቁት ኢንቨስተር›› በሚል ርዕስ ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተስተናገደው የሸሲ ቡና ተክል አምራች ገበሬዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ በሕገወጥ የጥቅም ትስስር የተፈፀሙ እኩይ ድርጊቶች እንዲታረሙ የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት አዘዘ።
ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለጉዳዩ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ አቅጣጫ መሰጠቱን ገልፀው፤ የክልሉ ፕሬዚዳንት በ20/07/2011 ዓ.ም ለማጃንግ ብሔረሰብ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል።በመዝገብ ቁጥር መ2/3859/መ1/10 ወጪ በተደረገው በዚሁ ደብዳቤ፤ ማህበሩ ላይ የተፈፀሙ ሕገወጥ ድርጊቶችን ፕሬዚዳንቱ አውግዘዋል።
ማህበሩ በማጃንግ ብሔረሰብ ዞን መንገሺ ወረዳ የሪ ቀበሌ ውስጥ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የቡና ልማት ሲያካሂድ ቢቆይም በ2004 ዓ.ም ግን በተወሰኑ ግለሰቦች በቀረበው ሕገወጥ ጥያቄ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር በደብዳቤው ሰፍሯል።ሥራ አስኪያጁ በማረሚያ ቤት ከቆዩ በኋላ ጉዳዩን የያዘው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከወንጀል ነጻና የንብረቱ ባለመብት መሆናቸውን ወስኖ ከእስር ቢያሰናብታቸውም ፤ በ2007 ዓ.ም በጥቅም የተሳሰሩ አካላት ልማቱን ዳግም ማስቆማቸውን ፕሬዚዳንቱ በጽሑፋቸው እንዳብራሩ ከደብዳቤ ግልባጭ ለመረዳት ተችሏል።
ሥራ አስኪያጁ በኪራይ ሰብሳቢዎች ድጋፍ የተፈፀመውን ሕገወጥ ድርጊት በሁሉም የአስተዳደር እርከን ለሚገኙ የመንግሥት አካላት ቢያሳውቁም ድርጊቱን ያስተካከለ አካል ባለመኖሩ ጉዳዩ ከክልሉ አልፎ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማትና ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መድረሱን ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤው አብራርተዋል።በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሳታፊ በመሆን ለክልሉና ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ልማታዊ ባለሀብቶችንና ማህበራትን ድጋፍ መስጠትና ማበረታታት እንደሚገባም ደብዳቤው አስቀምጧል።
በሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በእንጭጩ መፍታት እንደሚያስ ፈልግ ተገቢነቱ ባያጠያይቅም፤ ማህበሩ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ አለመሰጠቱ ግን ወረዳውና ዞኑ ፍትሕን ከማስፈን አንፃር የነበረባቸውን ከፍተኛ ችግር አጉልቶ ያሳየ እንደሆነም ተችቷል።
የተፈፀመው ሕገወጥ ድርጊት አገሪቱ የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ የሚፃረር በመሆኑ ተጠያቂነት እንደሚያ ስከትልም በደብዳቤው ተገልጿል።ማህበሩ የጀመረውን ልማት እንዲቀጥልም በይዞታው ላይ የገባ ሌላ ድርጅት ካለ በአስቸኳይ እንዲለቅ፤ የተሠራ የይዞታ ማረጋገጫ የባለቤትነት ካርታ ካለም በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤው አዝዘዋል።በዚህም ማህበሩ በመታገዱ ምክንያት ያልከፈለውን የመንግሥት ግብር እንዲከፍልና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸው እንዲታደስ ድጋፍ ተደርጎ በአጭር ጊዜ ወደ ልማት እንዲገባ መታዘዙን ከደብዳቤው ግልባጭ ተመልክተናል።
ይህን መነሻ በማድረግ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ግልጽ መመሪያ መሰጠቱን ገልፀው ለዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ደብዳቤ ጽፏል።በዚህም በማህበሩ ጣልቃ የገባ አካል ወጥቶ የተሠራ ካርታ ካለም ተሰርዞ ማህበሩ በአጭር ጊዜ ወደ ሕጋዊ የልማት ሥራው እንዲመለስ እንዲደርግ ማሳሰባቸው ሰፍሯል።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አደመ ገብረጻዲቅ፤ ውሳኔውን ለማስፈፀም አዲስ አበባ መጥተው ዳግም በተቋማችን ተገኝተው በሰጡን ቃለምልልስ ሁለት መቶ ሔክታር የቡና ማሳቸው ባልታወቀ መልኩ ለሌሎች ግለሰቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሠርቶ መሰጠቱን አስታውሰዋል።ምንም እንኳ ጉዳዩን የመረመሩ አካላት ሕጋዊ መሆናቸውንና በንብረቱ ላይም ሕጋዊ ባለመብት እንደሆኑ ቢያረጋግጡም፤ በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ውስጥ የሚሠሩ አካላት ግን ሥልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም በደል እንዳደረሱባቸው ተናግረ ዋል።
የደረሰባቸው በደልም ከልማታቸው ለመልቀቅና ሚስትና ሦስት ልጆቻቸውን በትነው ለጎዳና እንደዳረጋቸው አስረድተዋል።በዚህ የተቀነባበረ ድርጊት ረጅም ቀጠሮ እየተጠየቀ ባልፈፀሙት ወንጀል በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸውንና ሕጋዊ ቢሆኑም ትከሻቸውን የሰበረ የበዛ ቁጥር ያለው ማስረጃቸው ዘብጥያ ከመወርወር እንዳላዳናቸው አስታውሰዋል።
ከማረሚያ ቤት ወጥተው በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳና ወድቀው ይኖሩ እንደነበርም በመግለጽ፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን፣ የሰነድ ማስረጃዎቻቸውንና የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር በማነጋገር በሠራው ዘገባ ዳግም የተስፋ ብርሃን እንደበራላቸው ፤ ያለአግባብ በግለሰቦች እጅ የሚገኘው ንብረታቸውም እንዲመለስ መወሰኑን ተናግረዋል።የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በድብቅ የተሠራው ካርታ መክኖ ንብረታቸው ተመላሽ እንዲደረግላቸውና ወደ ሥራ እንዲገቡ ለዞኑ አስታውቋል።የዞኑ ርዕሰ መስተዳድር ከዚህ በፊት ጉዳዩን አስመልክቶ ሦስት ጊዜ የፃፈውን ደብዳቤ ተፈፃሚ ያላደረገውን የዞኑን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ተጠያቂ ሳያደርግ ትዕዛዙን ብቻ አስተላልፏል።
ችግሩን የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ ባለመደረጋቸውና ወደ ሥራ እንዲገቡም ምንም ዓይነት የሕግ ዋስትና ያልተሰጣቸው በመሆኑ የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ትዕዛዙን ሊያስፈጽም ፈቃደኛ እንዳይሆን እንዳደረገው ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።በዚህም ‹‹አሁንም እንደ ቀድሞው ያለአግባብ ለእስር እዳረግ ይሆን?›› በሚል ያደረባቸውን ስጋት ተናግረዋል።በአሁኑ ወቅት ክልሉ የወሰነውን የውሳኔ ግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውን በመግለጽ፤ የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ፍዮሪ ተወልደ