በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ይከናወናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ታላላቅ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሐገራዊ ምርጫ ነው። ከሐገራዊ ምርጫው በተጨማሪም የሲዳማ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ በቀጣዩ ወር ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል። የአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማዕከል ሕዝበ ውሳኔው ሰላማዊ እንዲሆን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለተውጣጡ የሐይማኖት አባቶች ሰጥቷል።
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፓስተር ተሰማ ታደሰ እንደሚሉት፣ የኃይማኖት ተቋማት ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ግጭቶችን አስቀድሞ በመከላከልና ግጭቶች ሲፈጠሩ ችግሩን በመቆጣጠር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም ሕዝቡ መብቱን ተጠቅሞ ሕዝበ ውሳኔውን እንዲያካሂድና ውጤቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲቀበል የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
‹‹ሕዝበ ውሳኔው የሚካሄድበት የራሱ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አለው። ምርጫ ቦርድም ሕጉን ተከትሎ ታማኝ፣ ገለልተኛና ግልፅ ሆኖ ሕዝበ ውሳኔውን ማስፈፀም አለበት። የሐይማኖት አባቶችም ግጭቶች እንዳይፈጠሩና ከተፈጠሩም እንዴት መቆጣጠር እንደሚገባ በአቅም ግንባታና በልምድ ልውውጥ መድረኮች በኩል ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን›› ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም፣ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የሕዝቡን ሰላምና የአገርን አንድነት የሚያናጉ ድርጊቶች በመሆናቸው ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ተስተውለው የነበሩት መሰል ድርጊቶች እንዳይደገሙ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ይገልፃሉ።
‹‹ግጭት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ግጭት እንዳይከሰትና ከተከሰተም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እንሰራለን›› የሚሉት ፓስተር ተሰማ፣ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔው ባለፉት ጊዜያት ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችንም በማረጋጋት ረገድ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱንና ይህ ስራ ከጉባዔው መደበኛ ተግባራት መካከል አንዱ ስለሆነ ቀጣይነት እንደሚኖረው ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት ያለው አንፃራዊ ሰላም ሊገኝ የቻለውም የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከሕዝቡ፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራ ቅንጅታዊ ስራ እንደሆነም ይናገራሉ።
በሐዋሳ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትን የሚመሩት ወላንሳ ኢንጋሞ በበኩላቸው ሕዝቡ ምርጫውንና ሕዝበ ውሳኔውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያከናውን የሐይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ይገልፃሉ።
‹‹በመወያየትና በሰላም እንጂ በግጭት የሚሆን ነገር የለም። ሕዝበ ውሳኔው ማንንም ሳይጎዳ እንዲከናወንና ሰላማዊና አሳታፊ እንዲሆን ግንዛቤ እያስጨበጥን ነው›› ይላሉ።
ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሲዳማ ሕዝብ ከሁሉም ሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ የሚጠናከርበት እንዲሆንና ችግር እንዳይፈጠር ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
ባለፉት ጊዜያት በክልሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት ማፅናናታቸውንና መርዳታቸውን ፤በሃይማኖት ተቋማት ላይ ሲደርስ የነበረውን ጥቃት ለማስቆም ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ፤ ወደፊትም መሰል ተግባራት እንዳይፈጸሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ያስረዳሉ።
ከምርጫ ጋር ተያይዘው ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ለመከላከልና ለመፍታት የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አስፈላጊነታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመሰከረ መሆኑን የሚያስረዱት ደግሞ ስልጠናውን ባዘጋጀው በአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማዕከል ከፍተኛ የምርጫ ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት ፍራንክ ባልም ናቸው።
እንደባለሙያው ገለፃ፣ ግጭቶችን በማስወገድና መረጋጋትን በመፍጠር ረገድ የሐይማኖት አባቶች አስተዋፅኦ የላቀ በመሆኑ ይህን ጥረትና ሚና በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ማገዝ ምርጫውም ሆነ ሕዝበ ውሳኔው ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል።
ስለሆነም ሐገራዊ ምርጫውና ሕዝበ ውሳኔው ሰላማዊ ሆነው እንዲካሄዱ የአውሮፓ የምርጫ ድጋፍ ማዕከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
አንተነህ ቸሬ