አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያን ጨምሮ ከመላው አፍሪካ የተመረጡ 200 ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች በመዲናዋ እየተሳተፉበት የሚገኘው የአፍሪካ የፈጠራ ሳምንት አካታች የሆነ ዘላቂ ልማትን በአፍሪካ ለማምጣት እንደሚያግዝ ተገለጸ።
የአፍሪካ የፈጠራ ሳምንት ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት በተወካያቸው አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ የፈጠራ ሳምንቱ አፍሪካውያን የፈጠራ ባለሙያዎችን ከኢንቨስተሮች ጋር ማገናኘትን ዋና ዓላማው አድርጓል፤ መድረኩ የአፍሪካዊያንን የፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን፣ የግል ዘርፍ ባለሃብቶች እና ዓለም አቀፍ ተዋንያንን አንድ ላይ የሚያገናኝ ከመሆኑም በላይ ፈጠራን የሚያሳድግና አካታች ዘላቂ ልማትን በአፍሪካ ለማምጣት የሚያግዝ ነው።
ዝግጅቱ ከህብረቱ አጀንዳ 2063 ፕሮጀክት ጋር ተጣጥሞ እንደሚሄድ ሊቀመንበሩ ጠቁመው፤ የፈጠራ ሳምንቱ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ እድልን የያዘ፣ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን የሚከፍት እና ተጨማሪ ባለሃብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።በመድረኩ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ትኩረታቸውን በሴቶች እና ሥራ ፈጠራ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በመስተንግዶ እንዲሁም በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ ያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የአይ ቢ ኤ ኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ እና የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በመድረኩ በላኩት የምስል መልዕክት እንደገለጹት፤ ይህ መድረክ መዘጋጀቱ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን እና ውጤታማ ባለሃብቶችን በአንድ መድረክ በማገናኘት በሚፈጠሩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ስራዎች አማካኝነት አህጉሪቱን በዘርፉ ከተቀረው ዓለም ጋር እንድትራመድ ያግዛታል ብለዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤ መሰል የፈጠራ ስራዎች አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት በተለይ በአገልግሎት እና ማምረቻ ዘርፎች ላይ ወጣቶች የፈጠራ ስራዎችን እንዲሰሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የአፍሪካ የፈጠራ ሳምንት አጋር በመሆን በቅርቡ የተቀላቀለው የቮዳፎን የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምስራቅና የኤዠያ ፓሲፊክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቪቬክ ባድሪናት<<የፈጠራ ሳምንቱን የምንደግፈው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሁሉም የሚያስገኘውን ጥቅም ስለሚያሳይ ነው>> ብለዋል።
<<ኢትዮጵያ ያላትን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፣ በመድረኩ በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ ተገቢ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የፈጠራ ሳምንቱ የተዘጋጀው አይ ቢ ኤ ኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ኢኖቬሽን ከኢፌዴሪ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ከኦስሎ ኢንተርናሽናል ሃብ ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ሶሎሞን በየነ