አዲስ አበባ፦ በግብዓት ችግር የማምረት አቅሙ ቀንሶ የነበረው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ 1000 ሜትሪክ ቶን ግብዓት ማስገባቱን አስታወቀ።
የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጋሻው ይመር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ግብዓቱ አንድ ሚሊዮን ዶላር ወይም 30 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውና እስከ ዘጠኝ ወር ማምረት የሚያስችሉ ለስኳር ማያዣ ከረጢቶች፣ ለቤትና ለውሃ ቧንቧ፣ ለልዩ ልዩ እቃ ማሸጊያዎች፣ ለውሃ መጠጫ ኮዳ፣ ለወንበርና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ገዝቷል።
አቶ ጋሻው የኢንደስትሪው ችግር የጥሬ እቃ እጥረት እንደነበር፣ ችግሩን ለማቃለል በተያዘው በጀት ዓመት ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት ጨረታ እንደሚወጣና ምርቱንም በቋሚነት እንደሚያቀርብ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የማምረቻ መሳሪያዎች ተጠግነው ወደ ምርት ለመግባት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ከሙስናና ዕዳ ጋር በተያያዘ አብዛኞቹ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምርቶች ላይ መቀዝቀዝ ታይቶ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ወደ ምርት እየገቡ ናቸው። ከኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ፕላስቲክ ፋብሪካ ዕዳ ያለበት ቢሆንም፤ ከሌሎቹ አንፃር ዕዳው ዝቅተኛ ነው። ዕዳውን እየሰራ ለመክፈልም ጥረት እያደረገ ነው።
የተለያዩ አይነት ምርቶችን የሚያመርቱ ስድስት ፋብሪካዎችና 650 ሠራተኞች ያሉት ኢንዱስትሪው በ2012 በጀት ዓመት 100 ሚሊዮን ብር ሽያጭ በማከናወን ስምንት ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ሲሆን፤ ከኢትዮ-ቴሌኮም፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከመድሃኒት ፋብሪካዎች፣ ከአዲስ አበባ ቤቶች፣ ከግል ተቋራጮች፣ ከመከላከያ ፋውንዴሽንና ከሌሎች ተቋማት ጋር አብሮ ይሠራል። በቅርቡም ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ባለ መቶና ባለ ሃምሳ ኪሎ ግራም የስኳር ማያዣ ከረጢቶችን ለማምረት ስምምነት ተፈራርሟል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
አጎናፍር ገዛኽኝ