«ምግብ ሳይመገቡ መማር ይከብዳል፤ መምህሩ የሚለውን በደንብ አንከታተለውም» ይላል የአስራ ሁለት መቱ ታዳጊ ዮሐንስ ሙለታ። ታዳጊው በኮከበ ጽባህ አጸደ ህጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የቤተሰቦቹ የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ቁርስና ምሳውን ይመገብ የነበረው በትምህርት ቤቱ ነበር። ዘንድሮ ግን እሱ ምክንያቱን ባያውቀውም በጣም ለባሰባቸው የደሃ ልጆች ብቻ የምግብ አገልግሎት ስለሚሰጥ እሱ ከሳምንቱ አብዛኛውን ቀን በባዶ ሆዱ ለማሳለፍ መገደዱን ይናገራል። እሱ ባይናገርም ነጭ ሆነው የደረቁት ከንፈሮቹ የሆዱን ባዶነት ያሳብቁበታል።
በተመሳሳይ በወጣቶች ገነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው የአስራ ሁለት ዓመቷ አበባ «ምሳ ይዤ አልመጣም፤ ብዙ ጊዜ የምበላው ከጓደኞቼ ጋር ነው፤ አንዳንድ ጓደኞቻችን ብዙ ቀን ጾማቸውን ይውላሉ፤ የሚያፍሩት ደግሞ ባዶ ምሳ እቃ ይዘው መጥተው ይመለሳሉ።» የምትለው ተማሪ ሀና ትምህርት ሲጀመር ምገባው በጥቅምት ይጀመራል ቢባልም እስካሁን ግን ምንም ነገር የለም። መምህራኖቻችንን ስንጠይቃቸው በቅርቡ ይጀመራል ይሉናል ትላላች።
የትምህርት ቤቱ የአደረጃጀት ምክትል ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ዘነበ ወርቁ ከዚህ ቀደም በእናት ወግ በጎ አድራጎት 107 እንዲሁም በፍቅር ወንድማማቾች የጤና ስፖርት ማህበር 18 ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደነበሩ በማስታወስ ዘንድሮ ፍቅር ወንድማማቾች የስፖርት ማህበር ብቻ 3 ሺ ብር በመመደብ 25 ተማሪዎችን እየመገበ መሆኑን ይናገራሉ። በትምህርት ቤቱ አብዛኛው ተማሪ ከደሀ ቤተሰብ የመጡ፣ ዘመድ ጋር ተጠግተው የሚኖሩና በትርፍ ሰዓታቸው ሥራ እየሠሩ ራሳቸውን የሚደጉሙ ናቸው። ከልዩ ፍላጎትና ከአጸደ ህጻናት ውጪ ካሉት 1ሺ200 ተማሪዎች አራት መቶ የሚደርሱት የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ተለይተው እንዲቀርቡለት በጠየቀው መሰረት ከፍተኛ ችግር ያለባቸው 270 ተለይተው የተላኩ ቢሆንም እስካሁን በቅርቡ ይጀመራል ከሚል ምላሽ ውጪ ጠብ ያለ ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።
የወጣቶች ገነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ታገል መንግስቱ በበኩላቸው የምገባ ፕሮግራሙ መጀመሪያ ቀን እነሱንም እንደናፈቃቸው ይገልጻሉ። ባለፈው ዓመት የእናት ወግ በጎ አድራጎት 85 ተማሪዎችን ይዞልን ነበር ዘንድሮ ከመቶ በላይ ምገባ የሚያስፈልጋቸውን ለይተናል። አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን ባለፈው ሳምንት ጠይቀን ይጀመራል ብንባልም የመጣ ነገር የለም። በመሆኑም ብዙ ተማሪዎች በችግር ውስጥ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በጣም የባሰባቸውን እስካሁንም ሲደግፍልን የነበረው ሙላት የበጎ አድራጎት ድርጅት ለ27 ተማሪዎች የምሳና ቅዳሜ ደግሞ የጥናትና የምሳ ድጋፍ እያደረግልን ይገኛል።ብዙ ቤተሰብ እንደ አምናው የምገባ ፕሮግራሙ ይኖራል ብሎ ስላልተዘጋጀ ቅሬታ ፈጥሮበታል ይላሉ።
«ምገባው በጥቂት ቀናቶች ውስጥ ይጀመራል» የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የህጻናት ጤናና ምገባ ቢሮ አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሪት ሜቲ ታምራት ናቸው። ወይዘሪት ሜቲ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ እስካሁን ሲካሄድ የነበረው በተለያዩ አካላት ድጋፍ ነበር። በዋናነትም የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር እስከ ባለፈው ዓመት 22 ሺ ተማሪዎችን በአስሩም ክፍለ ከተማ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲመግብ ነበር። ሌሎች የተለያዩ ተቋማት፣ መምህራን፣ ማህበረሰቡና ባለሀብቶች ደግሞ ወጥነት ባይኖረውም አስር ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች አገልግሎት ሲሰጡ ነበር። የእናት ወግ የበጀት እጥረት ስለገጠመው በዚህ ዓመት እየመገበ ያለው ዘጠኝ ሺ ብቻ ሲሆን፣ እነዚህም በተለይ ችግሩ በሰፋባቸው አራዳ፣ ቂርቆስና ጉለሌ እንዲሆም በሌሎቹ ክፍለ ከተሞች በተወሰኑ ትምህርች ቤቶች ብቻ ነው።
ፕሮግራሙ ውጤታማና አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ከተማ አስተዳደሩ ለመደገፍና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተደራሽ ለማድረግ መስራት ጀምሯል። በዚህም በ2011 ከተማ መስተዳድሩ በፈቀደው በጀት ፕሮግራሙ 51 ሺ የሚደርሱ ተማሪዎችን የቁርስና ምሳ ተጠቃሚ ለማድረግ ወስኗል። ለዚህም የመጀመሪያ ዙር 66ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የተፈቀደ ቢሆንም ፋይናንስና ኢኮኖሚ ብሩን ለክፍለ ከተሞች የለቀቀው ታህሳስ አምስት ዘግይቶ ነው።ሆኖም በአሁኑ ወቅት ወደ የትምህርት ቤቱ አካውንት እንዲገባ ተደርጓል። በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ በኩልም ምግብ የሚያዘጋጁት እናቶች እንዲደራጁ ተደርገው ወደ ስራ እየገቡ ነው። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በፍጥነት ጀምረዋል በቅርብ ጊዜ ደግሞ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚጀምሩ ይሆናል ።
ፕሮግራሙ የሚካሄደው ተማሪዎችን ለመርዳት ሳይሆን ህጻናቱ በቂ ምግብ የማግኘት መብት ስላላቸው ነው የሚሉት ወይዘሪት ሜቲ ከዚህ ቀደም ትምህርት የሚያቋርጡ ክፍል ውስጥ የሚወድቁ እንደነበሩ በማስታወስ ልጆቹ ተምረው ቢጨርሱም ውጤታማ፣ ጤናማ ብቁ ዜጋም እንደማይሆኑ ይናገራሉ። በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ የማይቆራረጥ በመሆኑ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው የሚሉት ወይዘሪት ሜቲ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ዘንድሮ በከተማዋ ሰባ ሺ የሚደርሱ ተማሪዎች ድጋፉ እንደሚያስፈልጋቸው ተረጋግጧል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ