አዲስ አበባ፡- አዲሱ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 ሴቶችን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገለጸ። አዋጁ በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ያለው ግንኙነት ህግን የተከተለ እንዲሆንና ለድርጅታቸውና ለሃገራቸው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተባብረው እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ ነውም ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በትናንትናው ዕለት በአዲሱ የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ላይ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሃይ ጳውሎስ እንዳሉት በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ ኢንዱስትሪ እንዲኖር በአሰሪና ሠራተኛ መካከል ከመግባባት ባለፈ ዘመናዊ የሆነ የሥራ ባህል እንዲኖር ያግዛል።
የኢንዱስትሪ ሰላም ለከተማዋም ሆነ ለሀገሪቱ ሰላምና ብልፅግና ወሳኝ በመሆኑ የሥራ ሁኔታዎች በአሰሪውና በሠራተኛው መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች በንግግር ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊዋ፤ “አዋጁ በተለይም ሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን የሚቀርፍና የሚያበረታታ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ ነው” ብለዋል። በሌላ በኩልም ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ ቁጥር 377/96 ማነቆ የነበሩ ችግሮች እንዲፈታ መደረጉን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው አዲሱ አዋጅ የአሰሪና የሠራተኞችን መብትና ግዴታ በግልፅ ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ ለሴቶች ትኩረት ያደረገ፣ ከምንጊዜውም በላይ ለማበረታታትና ለማብቃት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በአዋጁ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳ ስዩም በበኩላቸው የአዋጁ ዋና አላማ አሰሪና ሠራተኛው ተባብረው በመስራት ወሳኝ ድርሻ እንዲወጡ ማድረግ ነው ብለዋል።
የአሰሪና ሠራተኛ ሰላማዊ ግንኙነት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ ነው ያሉት የሥራ ሂደት መሪው አዲሱ አዋጅ ግንኙነታቸው ህግ ባስቀመጠው መሰረት እንዲመራ በማድረግ ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ድርጅታቸውንና ሃገራቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።
አዋጁ የአሰሪና ሠራተኛ መብትና ግዴታ፣ ክልከላ የተደረገባቸውንና ለቅጣት የሚዳረጉ ጉዳዮችን በስፋት ያካተተ ሲሆን ክልከላ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል በብሔር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኤች አይቪ /ኤድስ፣ በአካል ጉዳት እና በሌላም ሁኔታ በሠራተኞች መካከል አድሎ መፈፀምን ይመለከታል።
በቀድሞው አዋጅ ቁጥር 377/96 የሠራተኛ የሙከራ ጊዜ ቅጥር 45 ቀናት የነበረው ወደ 60 ቀናት ከፍ እንዲል አድርጓል ፤ አዋጁ ከነሀሴ 30 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ተፈፃሚ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ይበል ካሳ