አዲስ አበባ፦ የኤሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ በዘንድሮው በጀት ዓመት አንድ ሚሊዮን 198 ሺ 718 ኩነቶችን ለመመዝገብ እየሰራ ሲሆን፤ የባለፈው ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙ 53 በመቶ መሆኑን አስታወቀ።
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ተሬሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ2012 በጀት ዓመት ፍቺ 25 ሺ 98 ፣ ልደት 694 ሺ 660 ፣ ሞት 309 ሺ 18 ፣ ጉዲፈቻ 479 እና ጋብቻ 169 ሺ 443 በድምሩ አንድ ሚሊዮን 198 ሺ 718 ኩነቶችን ለመመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ለኩነቶች ምዝገባ ያለው ግንዛቤና ልምድ አናሳ መሆን፤ ያሉት የክብር መዝገብ ሹሞችም የመዋቅሩ አካል አለመሆናቸው ፣ የጸጥታ ችግር መኖሩ ፣ ለስራው እንቅፋት መሆናቸውን አመልክተው፤ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ባለፈው ዓመት አንድ ሚሊዮን 309 ሺ 153 ኩነቶችን ለመመዝገብ ቢታቀድም ማሳካት የተቻለው 693 ሺ 881 ወይም የእቅዱን 53 በመቶ ብቻ መሆኑን፣ ከ2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀርም ዝቅተኛ አፈጻጸም መሆኑን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለመጨመር በተለያዩ መንገዶች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊመዘገብ የሚችለውን ኩነት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ዕቅዱን በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም በ 16 ሺ ቀበሌዎች ይካሄድ የነበረውን ምዝገባ ወደ 19 ሺ ቀበሌዎች ከፍ እንዲል መደረጉን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ