አዲስአበባ፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የመንግሥትን ድርሻ በመቀነስና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ መበላለጥ ሳይሆን መደጋገፍን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍና ማህበራት ምክር ቤት፣ ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ባለድርሻ አካላት ጋር አገር በቀል የማሻሻያ እቅዱን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ይዘት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትር የፊሲካል ፖሊሲ አማካሪው አቶ ፋንታሁን በለው እንደገለፁት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት እጅና ኢንቨስትመንት የበዛ በመሆኑ የማሻሻያው አንዱ አቅጣጫም የመንግሥትን እጅ መቀነስና የግሉን ዘርፍ በዋናነት በኢኮኖሚ ውስጥ ማሳተፍ፣መበላለጥ ሳይሆን መደጋገፍን መፍጠር፣ያለፈውን ማረምና ሳንካዎችን ማስወገ ድን ያለመ ነው።
ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በተለይ መዋቅራዊ ለውጥን ከማምጣት አንፃር እምብዛም ስኬታማ እንዳልነበረ፣ የገቢ ዕድገቱ በዋናነት የመነጨው በሀብት ክምችት በመሆኑ አነስተኛ ምርታማነት መከሰቱን፣ኢኮኖሚው በበርካታ መዋቅራዊና የዘርፍ ማነቆዎች የተተበተበ በመሆኑም የተገኘውን ዕድገት ዘላቂ አድርጎ ማስቀጠል የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን አቶ ፋንታሁን አመላክተዋል።
‹‹የማሻሻያ የመጨረሻ ግብም ከፍተኛ የሥራ እድል በመፍጠር ሁሉን አካታች ልማትና ድህነት ቅነሳ ነው፣የግሉን ዘርፍ በመዘንጋት የሚገኝ እድገት አይታሰብም፣ የግሉ ዘርፍም በማሳተፍ ፈጣን ድሎችን ለማስመዝገብም መንግሥት የፖሊሲ የሕግና ሌሎችም ማእቀፎች ተግባራዊ ያደርጋል ›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍና ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንደተናገሩት በፖሊሲም ሆነ በማስፈፀም አቅም ውስንነት የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገቱ በእዳ ጫና፣በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣በዋጋ ግሽበትና በከፍተኛ የኑሮ ውድነት መዘፈቅ ግድ ሆኖበታል።
ይሕ በሆነበት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ መደረጉም እነዚህን ፈተናዎችን ለመሻገርና የግሉ ዘርፍ የተሳትፎ እድገት ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ፣‹‹ከሁሉ በላይ በማሻሻያው የመንግሥትን ተሳትፎ መጠን በመቀነስ የግሉን ዘርፍ የሚያጎለብት መሆኑ በሁሉም መስክ የሚኖረንን ተሳትፎ ያሳድገዋል››ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ታምራት ተስፋዬ