በባሌ ሮቤና ዲንሾ ከተሞች ከሰሞኑ ተከስቶ የነበረውን ሁከት መቆጣጠርና ከተሞቹም መረጋጋት መጀመራቸውን የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ አደም ኢድሪስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባሳለፍነው ሳምንት በዞኑ ባሉ 20 ወረዳዎች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን ዋና አስተዳዳሪው አስታውሰው፤ በሰልፉ የተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ አስተላልፈው ሁሉም በሰላም ወደየቤታቸው የተመለሱ ሲሆን፤ በሮቤና ዲንሾ በተባሉ ወረዳዎች ላይ ችግር መከሰቱን ተናግረዋል።
በዲንሾ ተከስቶ የነበረውን ግጭት የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በባህላዊ መንገድ ለማብረድ መቻሉን፤ በሮቤ የነበረው ሁኔታ ጠንከር ያለ ስለነበር በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
እንደዋና አስተዳዳሪው ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብት መልካም ነገር ሆኖ ሳለ ወደ ግጭት መግባት፣ ሃይማኖታዊ ቅርጽ እንዲይዝ በማድረግ ህይወት ማጥፋትና ንብረት ማውደም በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው።
በዚህ ግጭት ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ በዚህም በጣም አዝነናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህ አካሄድ የኦሮሞ ህዝብ ያገኘነውን ለውጥ ከእጁ ለማውጣት የሚፈልጉ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል።
‹‹ የኦሮሞ ህዝብ ይህን አካሄድ ተገንዝቦ በመካከሉ የሃሳብ ልዩነት ቢኖር እንኳን በመወያየት መፍትሄ መፈለግ ይገባዋል እንጂ ሃሳብን በሃይል ለማስፈጸም መሞከር የኦሮሞ ህዝብ ያገኘውን ድል ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት መሯሯጥ ነው፤ ይህ ደግሞ አሳፋሪ ድርጊት ነው›. ብለዋል።
‹‹ ከዚህ አይነቱ ተግባር ወጣቱ መውጣት ይገባዋል›› ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ‹‹በቀጣይም ችግር አይገጥመንም ብሎ መናገር አይቻልም፣ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል፤ ይሁንና ችግርን ተቀምጦ በመወያየትና በመነጋገር ማስተካከል ይገባል እንጂ በእንዲህ ያለ አካሄድ መፍትሄ መፈለግ አግባብ አይደለም›› በማለት አሳስበዋል።
እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ፤ ኦሮሞ ችግርን የመፍታት የራሱ የሆነ የዳበረ ባህልና ወግ አለው ህዝብ በመሆኑ ችግሮችን ቁጭ ብሎ በመመካከር መፍትሄ መፈለግ ይገባል እንጂ እንደዚህ አይነት ነገር መፈጸም በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም።
ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ ሃያ ወረዳዎች ያሉ መሆኑን ገልጸው ግጭት የተከስቶ የነበረው በሁለቱ ወረዳዎች ከዚያም አልፎ ደግሞ ሁኔታው ጠንከር ያለው በአንድ ከተማ ብቻ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ሚዲያዎች ግጭቱ በአጠቃላይ በባሌ እንደሆነ አስመስለው የሚያቀርቡት ዘገባ ስህተት መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
በቸርነት ሁንዴሳ