የገጠር መሬት የተጋረጡበት ችግሮች ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን እንዲያገኝ ስላላደረጉት ችግሮቹን በመፍታት የማስተካካያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ የፌዴራል የፍትህ፣ የህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት አመለከተ።
በኢንስቲትዩቱ ጥናት ካደረጉት ተመራማሪዎች አንዷ ወይዘሪት ሃና ብርሃኑ እንደተናገረችው፤ ጥናቱ የገጠር መሬት ይዞታን በተመለከተ ከህግ ተግባራዊነትና እስከ አፈጻጸም በርካታ ችግሮች በመታየታቸው የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።
እንደ ተመራማሪዋ ማብራሪያ፤ በህገ መንግሥቱ ላይ መሬት የብሄር በሄረሰቦች እንደሆነ ቢቀመጥም፤ ይህን በሚጥስ መልኩ አርሶ አደሮች በተለያየ መንገድ ሽያጭ ስለሚያከናውኑ፣ በስጦታም ከመስፈርቱ ውጭ መሬት ስለሚያስተላልፉ፣ ከህግ ውጭ የውል መሬቶች ላይ ወረራ ስለሚያካሂዱና ሌሎችም የተለያዩ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ስለሚፈጽሙ በህግ የተቀመጠውን ድንጋጌ ጥሰው ይታያሉ።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚያያቸው ጉዳዮች 70 በመቶ የሚሆኑት ከመሬት ጋር የተያያዙ ፤ በተለይም ከዳር የአገሪቱ ክፍል እስከ መሀል አገር ለፍርድ ቤት ፍትህ ይሰጠን ሲሉ በር የሚያንኳኩት ከመሬት ጋር የተያያዙ የፍትህ ጥያቄዎች እንደሆኑ ተመራማሪዋ ያስረዳሉ።
ተመራማሪዋ በመሬት ፍትህ ጥያቄ አብዝቶ የሚጠየቀው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የችግሮቹ መንስዔ ምን እንደሆነ የፌዴራል የፍትህ፣ የህግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት እንዲያጠና ጥያቄ በማቅረቡ፤ ኢንስቲትዩቱም የገጠር መሬት ይዞታን አስመልክቶ የአንድ ዓመት ጥናት አካሂዶ ከህግ እስከ አፈጻጸሙ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።
መንግሥት መሬትን በፍትሃዊነት ለአርሶ አደሮች አይደለድልም፤መሬት ለሚገባው ሰው ይከለክላል፤ ለማይገባውም ይሰጣል፤ መሬትን ቋሚ በሆነና በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ በፍትሃዊነት የማስተዳደርም ችግር አለ፤ ክትትልና ቁጥጥርም አይደረግም፤ ጥፋተኞችንም ተከታትሎ ተጠያቂ አያደርግም፤ በዚህም የተነሳ መሬት ውጤታማ ጠቀሜታ እንዳይኖረው፤ ዜጎችም በፍትህ ደጅ እንዲንከራተቱ መንስዔ መሆኑን ፤ ወደ ፍትህ መድረክ ሲደረስም የተደራጀ መረጃና አሰራር ባለመኖሩ ዜጎች በሚፈለገው ደረጃ ፍትህን ለማግኘት እንደሚቸገሩ በጥናቱ መታየቱን ተመራማሪዋ ታስረዳለች።
የፍትሐብሔር ህጎች ዳይሬክተርና የጥናቱ መሪ አቶ ገብረመስቀል ገብረመድህን ‹‹የገጠር መሬት ውስን ነው፤ በአንፃሩ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ እየሄደ ነው፤ በዚህ የተነሳ የእርሻ መሬት ፍላጎት እየጨመረ ይገኛል፤ መሬትን በፍትሃዊነት፤ ሳይንሳዊና በስርዓት መጠቀም ካልተቻለ ዜጎች ለመገፋፋትና የማያስፈልግ ግብግብ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ይሆናል›› ይላሉ።
አቶ ገብረመስቀል ስለጥናቱ ሲያብራሩም ተግባራዊ እንዲደረጉ የሚወጡ ህጎች ችግር እንዳለባቸው፤ በፌዴራልና በክልሎች የሚወጡ አንዳንድ ህጎችም እንደማይጣጠሙ፤ የመረጃዎችና የተቋማት አለመደራጀት፣ የመልካም አስተዳደርና መረጃ ያለመያዝ ችግሮች ይታያሉ፣ ክልሎች መሬት የብሄር ብሄረሰቦች ነው ሲባል በክልሉ የሚኖሩ ዋነኛ በሄረሰቦች ብቻ አድርገው በማሰብ ደንቦችንና መመሪያዎችን በመሸርሸር፤ ተዘዋውሮ የመስራትን መብት እስከመገደብ እንደሚደርሱ በጥናቱ ተለይቷል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢንስቲትዩቱ የምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ እንደሚያብራሩት በህገ መንግሥቱ መሬት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ የማይሸጥ የማይለወጥ የጋራ ሀብት መሆኑ ተደንግጓል። ነገር ግን በተደረገው ጥናት መሬት ለሽያጭ ይቀርባል፤ ከተሸጠም በኋላ ህገ ወጥ ነው ብሎ በመንጠቅ ባለቤቱ አላግባብ ይጠቀምበታል።
በፌዴራልና በክልሎች የሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች መካከል ልዩነትና ከፍተቶች መኖራቸውንና በህግ መንግሥቱ ላይ ከተቀመጠው ውጭ መሬት የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ አድርጎ የማስብ ሀኔታ መታየቱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይኸው ጉዳይ በቅርቡ ለነበረው ግጭት ምክንያት እንደሆነ ፤ በተለያዩ ክልሎች የተለያየ ገጽታ ቢኖርም የዜጎችን መብት አላግባብ የሚነጥቁበትና በዜጎች የኢኮኖሚና የማህበራዊ መብቶቻቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ጥናቱ እንዳመላከተ ይናገራሉ።
የገጠር መሬትን ውስብስብ ችግር ለመፍታት የገጠር መሬት ተቋማትን መገንባት። ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት በመዘርጋት ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት። በስርዓቱ ውስጥ ያሉ አካላት ሲያጠፉ ተጠያቂ ማደረግ። የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ማውጣት። በመሬት የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ስርዓት መዘርጋት።
መሬት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸውን ግንዛቤ መፍጠር። በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያሉትን ህጎች ማጣጣም። በአሰራር ያሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ በጥናቱ በመፍትሄነት መቀመጡን የጥናቱ ተሳታፊዎችና ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ