የሰው አይነት ይታያል።ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ታዳጊው፣ጎልማሳው ወዲህ ወዲያ ይላል። በአማርኛ፣በኦሮምኛ፣በእንግሊዝኛ የሚነጋገሩ በርካታ ናቸው። ቻይናውያን፣ አውሮፓውያን እንዲሁም አፍሪካውያንም በብዛት በየአቅጣጫው ይታያሉ።
በቡድን፣በተናጥል እንዲሁም በጥንድ በጥንድ ሆነው ነው በአንድነት ፓርክ ቅጥር ግቢ ውስጥ ጉብኝቱን የሚያደርጉት።
ፎቶ ይነሳሉ፤ታሪካዊ እና ባህላዊ መስህ ቦችን የሚገልጹ መረጃዎችን ጠጋ ብለው ያነባሉ፤ ይመለከታሉ፤ያዳምጣሉ። በታላቁ ቤተመንግስት ግቢ ውስጥ ተገንብቶ በቅርቡ ተመርቆ ጎብኚዎችን እያስተናገደ የሚገኘው ይህ ፓርክ ወደ ስድስት የሚደርሱ የመስህብ ስፍራዎች አሉት።
የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ቤተመንግሥት፣ግብር ቤትና የተለያዩ ታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎች የተካተቱበት ይህ ፓርክ፣የጥቁር አንበሳ ስፍራ፣የክልል እልፍኞች፣የእንስሳት ስፍራ፣ የእጽዋት ስፍራ፣ የህጻናት መጫወቻ እና የአረንጓዴ ስፍራ የፓርኩ ሌሎች ውበቶች ናቸው።
ጥላ ስር አረፍ ብለው ወደተቀመጡት አዛውንቶች እና ጎልማሶች ተጠጋሁ፤ የፓርኩን የተለያዩ ክፍሎች ከጎበኙ በኋላ ከመውጣታቸው በፊት አረፍ ለማለት ፈልገው እንደተቀመጡ ገመትኩ፤አረፍ ባሉበት ቦታ ሆነውም መጎብኘታቸውን አልተውም።ወደተለያዩ የፓርኩ አቅጣጫዎች እያመለከቱ ይወያያሉ።
የኮተቤ አካባቢ ነዋሪው አቶ ተድላ መኮንን ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ናቸው።አቶ ተድላ ቀድሞ ፓሊስ ጋራዥ በሚባለው በቤተመንግሥቱ አጎራባች መንደር ኖረዋልና አንድነት ፓርክ የተገነባበትን የቤተመንግሥቱን አካባቢ በወጣትነታቸው በሚገባ ያውቁታል።
በንጉሡ ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤታቸውንም እንደ ዘመኑ ተማሪዎች ግብር ቤት በመገኘት ለንጉሡ እጅ ነስተዋል።በደርግ ዘመን ደግሞ በቀይሽብር ታፍሰው በዚሁ ግቢ ለቀናት ታስረዋል።
በጨለማ ወደ ግቢው እንደተወሰዱ የሚናገሩት አቶ ተድላ፣ ግቢው ጫካ እና በጣም አስፈሪ እንደነበር ይናገራሉ።በቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ መታሰራቸውንና የቤቷ ግድግዳ በደም የተለወሰ እንደነበር አስታውሰው፤በኋላም ወደ ማእከላዊ ተወስደው ለአመታት በእስር ቆይተዋል።
‹‹ዛሬ እግዚአብሄር ይመስገን ቤተመንግሥቱን ገብተን በነጻነት ተዘዋውረን አየነው››ይላሉ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርኩን ለመገንባት ያሳዩትን ድፍረት በማድነቅም በጣም የሚያምር ሥራ ጨክነው መስራታቸውን ተናግረዋል።የፓርኩን ግንባታ ፍጥነት በጣም በማድነቅም፣ሲመረቅ ህልም እንደመሰላቸውም ነው የገለጹት።‹‹ከእንቅልፍ ሲነቃ የታየ ያህል ነው››ሲሉ የግንባታውን ፍጥነት ገልጸውታል።
አቶ ተድላ ከዚህም በላይ ይጠብቃሉ፤ ከተጀማመረው ሁሉ አብዛኛው ጥሩ መሆኑን በመጥቀስም፣ትንንሽ ነገሮች ይጠፋሉ፤ እኛም የሚሰራን ሰው ማገዝ አለብን፤ቢያንስ ባንሰራ እንኳ እንቅፋት መሆን የለብንም››ይላሉ።
‹‹ፓርኩ በእርግጥም የአንድነት ተምሳሌት ነው›› የሚሉት አቶ ተድላ፣ለእዚህ ደግሞ ‹‹ይሄው ኢትዮጵያ ቁጭ ብላ አይደል፤ፍቅር ከስር ይታያል፤ሌሎቹ እኮ ቅርንጫፎች ናቸው።›› ሲሉ በአረንጓዴው ስፍራ የሚታየውን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ታፔላ አመለከቱን።ኑሮውን በአውስትራሊያ ካደረገ ከ15 ዓመታት በላይ የሆነው አቶ ደረጀ ገብረማርያም፣ በመገናኛ ብዙኃን ስለፓርኩ የተከታተለው ከጎበኘው ጋር በጭራሽ አልተገናኘለትም።በጉብኝቱ ፓርኩን በጣም ውብ ሆኖ አግኝቶታል።‹‹በህይወቴ እንደዚህ ተደስቼ አላውቅም፤ኢትዮጵያውያን ይህን አይነት ውብ ስፍራ በማግኘታችን ኮርቻለሁ።››ሲል ይገልጻል።
አቶ ደረጀ ፓርኩን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነጸብራቅ አርጎ ተመልክቶታል፤‹‹የምናደርጋቸው የትኞቹም ነገሮች የእኛነታችን መገለጫ ናቸው፤ይህ ሥራም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ብሩህ አእምሮ ያመለክታል።››ብሏል።‹‹በጉብኝቴ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገለጫዎችን አይቻለሁ፤ጎብኚዎችንም ስመለከት ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተውጣጡ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ።››ሲል ይገልጻል።
ኢትዮጵያን በቅጡ እንደማያውቃት ጠቅሶ፤አሁን ግን በፓርኩ ውስጥ እንዳያት ተናግሯል።ፓርኩም እንደ ስሙ አንድነት መሆኑን ጠቅሷል።
‹‹ኢትዮጵያ እንድታብብ እንደምንፈልጋት እንድትሆን ከፈለግን ሁሉም ሰው አመለካከቱን መቀየር ይኖርበታል››ያለው አቶ ደረጀ፣ለውጥ የሚመ ጣው አእምሮ እና አመለካከት ሲቀየር መሆኑን ያብራራል።የክልሎችን ሳሎኖች ስትጎብኝ ያገኘኋት ወጣት የትናየት ታደለ፣የቄራ አካባቢ ነዋሪ ናት።
በጉብኝቷ የተመለከተችው ከሰማችውም በላይ ሆኖባታል፤ሳሎኖቹ በጣም የሚያምሩ ሆነው አግኝታቸዋለች።‹‹ፓርኩ የሁሉንም ክልሎች መገለጫዎችን አካቶ ማቅረቡም በእርግጥም አንድነት ፓርክ እንዲሰኝ አርጎታል።››ትላለች።
ወጣት የትናየት ከሰማቸው በመነሳት በቤተመንግሥቱ አካባቢ ስታልፍ ከፍራቻዋ የተነሳ ግቢውን በሙሉ በአይኗ አይታ አታውቅም ነበር።‹‹የቤተ መንግሥቱን ግቢ አተኩሬ ካየሁ የሚተኩስብኝ ያህል አርጌም አስብ ነበር።››ትላለች።
ሀገሪቱ አሁን በጣም ተመስገን በሚያሰኝ ሁኔታ እንደምትገኝ ገልጻ፤ወደ ፓርኩ ስትገባም ያለችውም ይህንኑ አንደነበር ትናገራለች።‹‹ሥ ራው በጣም ፈጣን ነው፤እንደሚሰራ ተነገረ፤ አለቀ፤በጣም ደስ ይለኛል።››ብላ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርኩ እውን እንዲሆን የወሰዱትን ተነሳሽነት ታደንቃለች።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል