አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ሰሜኑ አካባቢ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመቆጣጠር ሥራ ለሁለት ሳምንት ተጠናክሮ ከቀጠለ በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሶላቶ በተለየ ለአዲሰ ዘመን እንደገለፁት፤ወደ ኢትዮጵያ እየተዛመተ ያለው ያደገ የበረሃ አንበጣ በሰኔ አጋማሽ ላይ ከየመንና ከሶማሌ ላንድ የመጣ ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላም በአፋር ክልል በስፋት እንቁላል የተጣለ ሲሆን፣ መስከረም መጀመሪያ ላይ ይህ እንቁላል ተፈልፍሎ ወደ ትግራይና አማራ አካባቢ በመውጣት ላይ ይገኛል።በድሬዳዋ ዙሪያ እና ምስራቅ ኦሮሚያ የቀርሳ እና ጎሮጉቱ ወረዳዎችን ጫፍ እየነካካ ይገኛል።
የአንበጣ መንጋው ወደተጠቀሱት ክልሎች መዛመት ከጀመረ አንስቶ ባለሙያዎች በቦታው በመገኘትና ህብረተሰቡንም በማስተባበር ለመቆ ጣጠር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፣ለሦስት ተከታታይ ቀናት የአውሮፕላን ርጭት መካሄዱንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
እየተደረገ ባለው የቁጥጥር ሥራ የአንበጣ መንጋው በቁጥር እየቀነሰ መሆኑን አስታውቀዋል።ቁጥጥሩም በሰው ሀይል ጭምር እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ይህ የመቆጣጠር ሥራ ለሁለት ሳምንት ያህል ተጠናክሮ ከቀጠለ የአንበጣ መንጋውን መቆጣጠር እንደሚቻልም አመልክተዋል።
አቶ ዘብዲዎስ እንደተናገሩት፤በአሁኑ ሰዓት ያለው መንጋ ተራ የሚባለው ነው።አንበጣ በባህሪው ምቹ የአየር ፀባይ ሲያገኝ በመገናኘት ትልቅ መንጋ የመፍጠር አቅም አለው።ከመከላከል የተረፈው አዳጊው አንበጣ የተበጣጠሰና አነስተኛ በመሆኑ ተፈላልጎ በመገናኘት ትልቅ መንጋ ለመሆን ጥረት እያረገ ነው።
የአንበጣ መንጋ እድገቱን ጨርሶ ወደጉልምስና ስለሚቀየር እንቁላል በመጣል የሚያልፍ ስለሆነ እንደ አገር ሰፊ የመከላከል ሥራ በመካሄድ ላይ ነው።
አንበጣውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ተጠናክሮ መረጃ መስጠት እንደሚኖርበት ጠቅሰው፣የባለሙያዎችን ምክር መቀበል አለበት ብለዋል።
መንግሥታዊና መንግ ሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉ አካባቢያቸው ባሉ የግብርና ፅህፈት ቤቶች አሊያም በአርብቶ አደር ፅህፈት ቤቶች አማካይነት የተቀናጀ የጋራ ሥራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።የመከላከሉ ሥራ በዚህ መሰረት አንድ አቅጣጫ የሚያዝ ከሆነ በቀላሉ መከላል ይቻላል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፤‹‹በእስካኑ ሂደት ያን ያህል ጉዳት አስከትሏል ተብሎ የተመዘገበ ነገር የለም።ወደፊትም ደግሞ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ተጠናክረን እንቀጥላለን።››በማለት አስረድተዋል።ለዚህም ደግሞ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
አስቴር ኤልያስ