– ለምገባው ብቻ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል
አዲስ አበባ፦ በተያዘው የትምህርት ዘመን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በተጀመረው የምገባ ፕሮግራም ከ10 ሺ በላይ እናቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ክትትል ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ዓቢይ ተፈራ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ በምገባ ፕሮግራሙ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የተካተቱ ሲሆን፣ለአንድ ተማሪ በቀን ቁርስና ምሳን ጨምሮ 14 ብር በአማካይ በጀት ተመድቧል።በዚህም 300 ሺ የሚደርሱ ተማሪዎች ተጠቃሚዎች ናቸው።
በምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎችን በመመገብና የተማሪ ወላጆችን ደግሞ ለመደጎም እየተሠራ መሆኑንም የቡድን መሪው ጠቅሰው፣በፕሮግራሙ ከ10ሺ በላይ እናቶች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።
እንደ አቶ ዓቢይ ገለፃ፣በምገባው መርሐ ግብሩ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወላጆች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሲሆኑ፣ አብዛኞቹም ተማሪ ልጆቻቸው በሚማሩበት ትምህርት ቤት እንዲሠሩ ተደርጓል።ይህም ልጆቻቸውን እየመገቡ መሆኑ እንዲሰማቸውና ለምግቡ ጥራትና ጥንቃቄም እንዲያደርጉ ታስቦ የተደረገ ነው።
የምገባ መርሐ ግብሩ ተማሪዎችን በመመገብና የተማሪ ወላጆችን ደግሞ በመደጎም ሁለት ግቦችን ማሳካቱን ያስረዱት አቶ ዓብይ፣የምግቡን ጥራት ለመጠበቅ ጤና ቢሮ፣ንግድ ቢሮ፣ሴቶችና ህፃናት ቢሮ፣የፋይናንስ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች መሆናቸውን ተናግ ረዋል።ለአቅራቢዎቹ በሚከፍለው አገልግሎት ልክ ተመጣጣኝና ታሳቢ የተደረጉ የምግብ ዝርዝሮች መኖራቸውንም ገልፀዋል።
አቶ ዓቢይ እንደተናገሩት፣በትምህርት ቤት የምግብ ተረፈ ምርቶች ለተማሪዎቹ ጠንቅ እንዳይሆኑ የከተማዋ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥራውን በኃላፊነት ይሰራል።ምግቦች ጤናማ ለመሆናቸውና ለተማሪዎቹ ችግር እንዳይፈጥሩ ደግሞ ጤና ቢሮ እንዲሁም የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር የሚሠሩ ሲሆን፣ምግብ አቅራቢዎቹ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ከሸማች ማኅበራት፣መንግሥታዊ ተቋም ሆነው በቅናሽ ከሚያቀርቡ አካላት ግንኙነት እንዲኖራቸው ንግድ ቢሮ ደግሞ ሚናውን ይወጣል።
ሴቶችና ህጻናት ደግሞ ዋነኛ ሥራው ለሴቶቹ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ማብቃትና ንቃተ ኅሊናቸውን ከፍ ማድረግ እንዲሁም ህፃናትን መንከባከብ እንደመሆኑ ሁለቱን አስተሳስሮ ሥራውን ያከናውናል።
እንደ አቶ ዓቢይ ገለፃ፣ገንዘቡ አነሰ የሚሉ አካላት ቢኖሩም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች ምግብና መኝታ ተካቶበት በቀን ለአንድ ተማሪ 15 ብር ወጪ የሚደረግ በመሆኑ ተቀራራቢ እንደሆነ ጠቁመው፣ለምገባው ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚሆንም አያይዘው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ