አዲስ አበባ፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን ለማፋጠን ጠንካራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁ ህዳሴ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤቱ 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ትናንት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደበት ወቅት እንዳስታወቁት ፤የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ሊዘገይ የቻለው በገንዘብ እጥረት አልያም በህዝብ ተሳትፎ ማነስ አይደለም።
‹‹የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ሲጀመር አገራዊ አቅምን ለመገንባት ታስቦ ቢሆንም እንዲህ አይነቱን ውስብስብ ፕሮጀክት በታሰበው ልክ መዝለቅ ይቻላል ብሎና ችግሮች ሲታዩም ቶሎ ብሎ በማስተካከል ስራው ተሟልቶ እንዲሄድ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ወሳኝ በሆነ የሜጋ ፕሮጀክቱ ቦታ ላይ የተፈጠረ ችግር ለፕሮጀክቱ መዘግየት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል›› ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በ2011 ዓ.ም የግንባታውን ማነቆ ፈቶ የግድ ወደሚለው መፍትሄ መግባት መቻሉ በጥንካሬ የሚታይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የግንባታ ፕሮጀክቱ እየዘገየ በሄደ ቁጥር ሌሎች ጣጣዎችን እያመጣና ክፍተቶች እየታዩበት ሊሄድ እንደሚችል አስገንዝበው፣ፕሮጀክቱን ለማፋጠን ጠንካራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ ያሉ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ተጠሪዎችና አመራሮችም አምባሳደር በመሆን የግንባታ ፕሮጀክቱን የበለጠ የማስተዋወቅና በየጊዜው የሚቀያየሩ ሁኔታዎችን የማወቅ ኃላፊነት አለባቸው።
በግንባታ ፕሮጀክቱ ዙሪያ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለህብረተሰቡና ለተለያዩ ተቋማት እንዲታወቁ እየተደረገና ሥራው በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም የሚታዩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በሃገር ውስጥ ላሉ አምባሳደሮችና የሲቪክ ማህበራት በሚዲያ አማካኝነት ማሳወቅ እንደሚገባው አመልክተዋል።ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም ጭምር የሁልጊዜ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
በጉባኤው ላይ በግድቡ ግንባታ ወቅታዊ ሁኔታና ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያለው የሦስትዮሽ ውይይትና ግንኙነት ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፃ ተደርጓል።የምክር ቤቱ የ2011 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፅም ቀርቧል፤ በ2012 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት ተካሂዶ አቅዱ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
አስናቀ ፀጋዬ