አዲስ አበባ፤ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞንን የኢንቨስትመንት እና የልማት ሥራዎች በማሳደግ የልማት ቀጣና ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል አስታወቀ።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ በአርሶአደሮች በኩታ ገጠም መሬት የለማ 819 ሔክታር ሰብልን የፌዴራል እና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ሰሞኑን በጎበኙበት ወቅት፤ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ/ ምክትል ሊቀመንበር እና የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እንደገለጹት፤ በዞኑ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር እና ኅብረተሰቡ ባደረገው ጥቂት ጥረት በርካታ ኢንቨስተሮችን የመሳብ ትልቅ ልምድ ታይቷል።
‹‹የተሟላ መልካም አስተዳደር ባይሰፍንም በተደረጉ ጥረቶች ግን አመራሩ ከሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ አገራት ጭምር ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል።››ያሉት አቶ ዮሀንስ፣ ክልሉም የዞኑን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
‹‹አካባቢው ከክልሉ አልፎ ለሌሎችም የሚተርፍ ሃብት ይዟል፤ይህንን በአግባቡ ባለመጠቀም ችግር ውስጥ የምንገባባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው።››ያሉት አቶ ዮሀንስ፣ አሁን በሰሜን ሸዋ በኢንቨስትመንቱ ብቻ ሳይሆን በግብርና ምርታማነት እየታየ ያለውን ለውጥ እንደተስፋ በመቁጠር ለተሻለ ስኬት ጠንክረን መታገል ይኖርብናል››ብለዋል።በተለይ አርሶአደሩን ከተደገፈ እና የተሻለ ትምህርት ከተሰጠው በግብርና ምርቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሞጃና ወደራ ወረዳ አርሶ አደር ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል።‹‹በዚህ ሳንኩራራ የአርሶአደሩን የምርት ተሞክሮ ልምድ በማስፋፋት ሥራችንን እንቀጥላለን›› ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድማገኘሁ እንደገለጹት፤ በኢንቨስትመንቱ መስክ ዞኑ ለበርካታ ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን የሚገኝበት ነው። የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት ምቹነት በመመልከት በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ፍቃድ እየወሰዱ ነው። በተለይም በዞኑ የሚገኙ ማዕድናትን የሚያለሙ ኢንቨስትሮች ኦፓል፣ ብረት እና የተለያዩ ማዕድናትን ለማውጣት ግንባታ ጀምረዋል።
‹‹ለኢንዱስትሪው መስክ የተመቸ ሰላማዊ ሁኔታ አለ›› ያሉት አቶ አቶ ተፈራ፣ ከመካከለኛ እስከ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች በግንባታ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ይህንን የኢንቨስትመንት እድል በመጠቀም አርሶአደሮች ምርታቸውን ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
ጌትነት ተስፋማርያም