አዲስ አበባ፣ የሰው ልጆች ተግባራትን በተቀላጠፈና በተሻለ የጥራት ደረጃ በመፈጸም ውጤታማ የዕድገት መንገድ ለሆነው ‹‹አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ›› ትግባራ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው በአገሪቱ የመጀመሪያው የ‹‹አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ››ጉባኤ ትላንት በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዳራሽ በተጀመረበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለፁት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጆችን ተግባራት በተቀላጠፈ፣በፈጠነና በተሻለ የጥራት ደረጃ በመፈጸም ውጤታማ የዕድገት መንገድ ወይም የሳይንስ ዕመርታ ነው።
ቴክኖሎጂው በጤና፣ በግብርና፣በደህንነት፣በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ምርት ሂደትና ተደራሽነት ላይ መተግበር ይችላል። ቴክኖሎጂውን ለዕድገታቸው ማሳለጫ በማድረግ ትሩፋቱን የሚቀደሱ አገራት እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቅሰው፣ኢትዮጵያም ከዓለም ጋር ለመጓዝ ቴክኖሎጂውን መቀላቀል ግድ እንደሚላት ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።
የቴክኖሎጂው ትግበራ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት ማሟላት እንደሚፈልግ ተናግረው፣ በዚህ በኩል መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ከአገሪቱ ስመጥር የምርምር ተቋማት አንዱ ሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂው ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል።በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትምህርት ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች እንዲሰጥ ተደርጓል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ምርምር ኔትወርክ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም አሰፋ በበኩላቸው እንዳሉት፤አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም ረገድ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ቀርታለች።እንደሌሎች አገራት ቴክኖሎጂውን ለሁለንተናዊ ዕድገት ግብዓት ለማድረግ ከትምህርት ተቋማት ጀምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
ታምራት ተስፋዬ