አዲስ አበባ፡- የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ መዘግየት የተነሳ የመማሪያ እና የቢሮ እጥረት እንዳጋጠማቸውና የሚፈለገውን ያህል ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር እንዳልቻሉ የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገለጹ። የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ግንባታው የዘገየው በበጀት እጥረት እንደሆነ አስታውቋል።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት የዩኒቨርሲቲው የመሰረተ ልማትና የህንጻዎች ግንባታ በዕቅዱ መሰረት ባለመጠናቀቁ በመማር ማስተማሩ ስራ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል። የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ሂደቱ ሶስት ምዕራፎች አሉት የሚሉት ዶክተር ገናናው ሁሉንም ምዕራፎች በ2012ዓ.ም ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝም የተጠናቀቁት ውስን የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ገናናው ገለጻ በግንባታው መዘግየት ምክንያት በየዓመቱ መቀበል የሚገባቸውን ተማሪ ልክ መቀበል አልቻሉም፤ የቢሮና የመማሪያ ክፍሎች እጥረትም አጋጥሟቸዋል። የኤሌክትሪክ ዝርጋታና የውሃ አገልግሎቶቹ ከፕሮጀክቶች ጋር ተያይዘው የሚሰሩ ቢሆንም ኤሌክትሪክ ለማስገባት ክፍያ ከተፈጸመ ሁለት ዓመት አልፏል። ውሃን በተመለከተም በጊዜያዊነት ከከተማ አስተዳደሩ በተቋራረጠ መንገድ የውሃ አገልግሎት ቢያገኝም በፕሮጀክቱ አካል የሆነው የውሃ መስመር ዝርጋታ ሊጠናቀቅ አልቻለም።
የዛሬ ሁለት ዓመት ይደርሳል ተብሎ የታሰበው የመማሪያ ክፍሎች ህንጻ ግንባታ በስራ ተቋራጩ አቅም ችግር ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ አለመጠናቀቁን የሚያነሱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የግንባታ መጓተቶችም በተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየፈጠሩና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እክል እየሆኑ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጄዎ ደማሙ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው የህንጻ ግንባታ በመጓተቱ በዘንድሮ ዓመት የተማሪዎችን ቁጥር ሰባት ሺ ለማድረስ የተያዘው እቅድ አልተሳካም። በዚህ የተነሳ አሁን መቀበል የተቻለው ከአራት ሺ 500 አይበልጥም።
በተለይ እንደ ውሃ፣ የኤሌክትሪክና መንገድ ያሉ መሰረተ ልማት ግንባታዎች 50 በመቶ እንኳ ሊደርሱ አለመቻላቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ያለው የመማሪያ ህንጻ አንድ ሲሆን ሌላው በግንባታ ላይ ይገኛል ብለዋል። የቢሮ እጥረትም እንዳጋጠማቸው ፣ የውስጥ ለውስጥ መገዶቹም ግንባታ መዘግየቱንና የአስፓልት መንገዱ ገና አለመጀመሩ ለግንባታው መጓተት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አቋቁሞ በ 2008 ዓ.ም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ መጀመሩን የሚገልጹት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ዶክተር ከተማ መስቀላ የ11ዱ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያው ምዕራፍ በሙሉ አቅም በቂ በጀት ተመድቦ ተጠናቆ ከሁለት ዓመት በፊት ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር መጀመራቸውን አውስተዋል።
በየዓመቱ ቢያንስ አንድ ሺ 500 ተማሪዎችን መቀበል በሚያስችል መልኩ የተወሰኑ ህንጻዎች፣ መኝታ ክፍሎችን (ዶርሚተሪዎችን) ፣ መማሪያ ክፍሎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ አተኩረን እየሰራን ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ የህንጻና የመሰረተ ልማት ግንባታውን በ2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ዕቅድ ቢያዝም በበጀት እጥረት ምክንያት ማጠናቀቅ አልተቻለም ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ዩኒቨርሲቲዎቹ እያንዳንዳቸው ሰባት ሺ ተማሪ እንዲያስተናግዱ ቢታቀድም የዘንድሮን ጨምሮ ከአራት ሺ እስከ አራት ሺ 500 ተማሪዎችን ብቻ ነው የሚያስተናግዱት ብለዋል።
እንደ ዶክተር ከተማ ገለጻ አቅምን አማጦ ግንባታውን ማጠናቀቅ ባይቻልም ዩኒቨርሲቲዎቹ ሙሉ አቅም ላይ እስኪደርሱ ድረስ በየዓመቱ በተወሰነ በጀትም ቢሆን ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል።
በ2011 በጀት ዓመት ለአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች መሰረተ ልማትና ህንጻ ግንባታ ሶስት ቢሊዮን ብር ያህል ተመድቦ እንደነበር አውስተው ዘንድሮ አራት ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን አብራርተዋል። ብሩ ለህንጻዎችና ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች ብቻ ሳይሆን ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ ቁሳቁሶችንና የቤተ ሙከራ ዕቃዎች፣ የቢሮ ዕቃዎች፣ የመመገቢያ ዕቃዎች፣ የተማሪዎች አልጋዎችና መቀመጫ ወንበሮች ለማሟላት ጭምር የሚውል መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይ አንድና ሁለት ዓመታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ ገልጸው የበጀቱ እጥረቱ ሲፈታ ቀሪ የግንባታ ምዕራፎች ማጠናቀቅ ይቻላል እንጂ የማጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ይከብዳል ብለዋል። በመሰረተ ልማት በመንገድ፣ በፍሳሽ ማስወገጃና በኤሌክትሪክ ዝርጋታና በውሃ አገልግሎት ጅንካ፣ እንጅባራ፣ ራያ ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ አፈጻጸም ሲኖራቸው በህንጻ ግንባታ ግን ከደምቢዶሎና ቀብሪደህር በስተቀር አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በአንጻራዊነት እኩል ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በካሳ ምክንያት የተጓተተው የኦዳ ቡልቱ ዩኒቨርሲቲ በ 2011 ዓ.ም የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ለዩኒቨርሲቲዎቹ የሚመደብላቸው በጀት ተመሳሳይ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ከተማ የተወሰኑት ስራ ተቋራጮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማጠናቀቃቸውንና የዘገዩትን የስራ ተቋራጮች ግን ውል በማቋረጥ ለሌላ ስራ ተቋራጭ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል። በመጀመሪያው ምዕራፍ የዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ 150 ተቋራጮች መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
ጌትነት ምህረቴ