አዲስ አበባ፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ለሁለት ቀናት በሩስያ ሶቺ ከተማ በተካሄደው የአፍሪካና ሩስያ የኢኮኖሚክ ጉባኤ ላይ በሁሉም መስክ የነበረው ተሳትፎ ውጤታማ እንደነበር ተገለጸ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው የተሳተፉባቸው መድረኮችና ያደረጓቸው ውይይቶች ስኬታማ ነበሩ። በዚህም በሁሉም ዘርፎች የሩስያና የኢትዮጵያ፣ የሩስያና አፍሪካ እንዲሁም ከህዳሴው የውሃ ሙሌት አኳያ የኢትዮጵያና የግብጽ ግንኙነት የተዳሰሱባቸው ውጤታማ መድረኮች ተከናውነዋል።
እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ፤ በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በመልዕክታቸውም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሪፎርም በተለይም ከኢኮኖሚ አኳያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚያግዝ፤ ኢትዮጵያም ለዚህ ከፍተኛ ፍላጎት ኖሯት ወደ ስራ የገባች መሆኑን አብራርተዋል። ይህ መልዕክት ደግሞ የሩስያን ኢንቨስተሮች እንዲሁም ጉባኤውን በተለያየ መልኩ ሲከታተሉ የነበሩ አካላትን ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን እንዲገነዘቡ ያደረገ ሲሆን፤ ኢንቨስትመንቱን ለመሳብም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።
በተመሳሳይ የሩስያ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ምን ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩ ሲሆን፤ በተለይም በአበባና አትክልት፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በማዳበሪያና በስኳር ፋብሪካዎች እና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢሰማሩ ኢትዮጵያም በስፋት የምትሄድባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ከመሆናቸው አኳያ ያለውን እምቅ ሀብት እንዲገነዘቡ አድርገዋል። የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ይህ ጥሩ እድል እንደሆነ፣ ይሄንንም እንደሚያበረታቱ የገለፁ ሲሆን በጋራ ለመስራትም ቃል ገብተዋል።
በተመሳሳይ የሩስያ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ምን ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩ ሲሆን፤ በተለይም በአበባና አትክልት፣ በባቡር፣ በመንገድ፣ በማዳበሪያና በስኳር ፋብሪካዎች እና ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ቢሰማሩ ኢትዮጵያም በስፋት የምትሄድባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ከመሆናቸው አኳያ ያለውን እምቅ ሀብት እንዲገነዘቡ አድርገዋል። የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ይህ ጥሩ እድል እንደሆነ፣ ይሄንንም እንደሚያበረታቱ የገለፁ ሲሆን በጋራ ለመስራትም ቃል ገብተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያና ሩስያ የኒውኩለር ሃይልን በማበልጸግና በመገንባት ለልማትና ለሰላማዊ ተግባራት ለማዋል ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፤ ይሄም በሁለቱ አገራት የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ተፈርሟል። ቀደም ሲል በሩስያ ድጋፍ የተገነባው የመልካ ዋከና የሃይል ማመንጫ ግድብ እድሳትን ሩስያ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ፕሬዚዳንት ፑቲን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የነበረባትን የ163 ነጥብ5 ሚሊዮን ዶላር እዳ ተሰርዞ ወደልማት እንዲውል ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በመሆኑም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የተካሄዱ መድረኮች ስኬታማ እንደነበሩ አቶ ንጉሱ ገልፀዋል።
አቶ ንጉሱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ተወክላ ሌሎች የጎንዮሽ ውይይቶችን ያከናወነች ሲሆን፤ በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብን አስመልክቶ ስኬታማ ውይይት አድርጋለች። በዚህም የግድቡን የውሃ ሙሌት በተመለከተ እንዲሁም ከግብጽ ጋር ባለው ግንኙነት ዙሪያ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ተወያይተዋል። በዚህም ከፖለቲካ አኳያ ማንኛውም ሶስተኛ ወገን አስተያየት ቢሰጥም ሁለቱ አገራት ጉዳዩን በስምምነት ይዘው እንዲጨርሱት ፍላጎት ከማሳየትና ድጋፍ ከማድረግ አኳያ መታየት እንደሚገባው አንስተዋል። የተቋረጡት የውይይት መድረኮችም በተጠናከረ መልኩ እንደገና እንዲጀምሩ እና ኢትዮጵያም የግድቡን ሙሌት ባስቀመጠችው መልኩ እንዲጠናቀቅና ይህ ሲሆን ግን የግብጽን ስጋት በመጋራት የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ግብጽን በመጉዳት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን ግንዛቤ እንዲጨበጥበት ማድረግ ተችሏል። በጥቅሉ በውይይቱ ሁለቱም መሪዎች በጥሩ መግባባት ውይይታቸውን አጠናቅቀዋል።
ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የተናጠል ፎረሞች ተደርገዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ፣ የአፍሪካና ሩስያ ግንኙነትን ለማሳለጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን መሆን አለበት የሚለው ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የአፍሪካ ሚዲያዎችና የሩስያ ሚዲያዎች ይሄን ግንኙነት በማሳካት ረገድ ያላቸውን ሁነኛ አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተመላክቷል። በአጠቃላይ የጉባኤው ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ የሩስያና የኢትዮጵያ፣ የሩስያና አፍሪካ እንዲሁም ከህዳሴው የውሃ ሙሌት አኳያ የኢትዮጵያና ግብጽ ግንኙነት የተዳሰሱበት ስለነበር መድረኩ ስኬታማ እንደነበር አቶ ንጉሱ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
ወንድወሰን ሽመልስ