ላለፉት 18 ዓመታት ያህል የኮንጎ ዴሞክራ ሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በመሆን በስልጣን ላይ የቆዩት ጆሴፍ ካቢላ ቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከተከናወነ በኋላ ስልጣናቸውን ለተተኪው ተመራጭ ያስረክባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ቢሆንም ምርጫው ጦርነት መለያዋ ሆኖ በዘለቀው አገር በተደጋጋሚ እየተራዘመ ዜጎችም ተስፋ እንዲቆርጡ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የሦስት ልጆች አባት የሆነው የ35 ዓመቱ ካምባዪ ኢብራሂም ምርጫው መራዘሙ ይፋ ከሆነ በኋላ ለአልጀዚራ በሰጠው አስተያየት፣ በምርጫው የአገሪቱ ዜጎች የወደፊቱን እጣ ፈንታቸውን የሚወስንላቸውን እጩ ለመምረጥ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ግን ምርጫውን በማራዘም ፕሬዚዳንት ካቢላ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ የ59 ዓመቱ ጆናስ ሙታላ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ድምፃቸውን ለጆሴፍ ካቢላ መስጠታቸውንና በድርጊታቸውም እንደሚፀፀቱ ቁጭት ባዘለ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ለምርጫ የተዘጋጁት የምርጫ ቁሳቁሶች በመቃጠላቸው ምርጫው እንደተራዘመ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ተቃዋሚ ኃይሎች በበኩላቸው ኮሚሽኑ ይህን የሚያደርገው ፕሬዚዳንት ካቢላን በስልጣን ላይ ለማቆየት ነው በማለት የኮሚሽኑን ድርጊት ክፉኛ ያወግዛሉ፡፡
የ47 ዓመቱ ጆሴፍ ካቢላ እ.አ.አ ከ1997 እስከ 2001 ድረስ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አባታቸው ሎረን ካቢላ እ.አ.አ በ2001 በጠባቂዎቻቸው ከተገደሉ በኋላ ወደ ፕሬዚዳንታዊ መንበሩ በመምጣት እስካሁን ድረስ በማዕድን ሀብት የበለፀገችው ሰፊ አገር ፕሬዚዳንት ሆነው ቆይተዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ያበቃው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ካቢላ መንግሥታቸው በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ አለው በማለት ከስልጣናቸው ሳይነሱ ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳ ካቢላ ከቀናት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ በተያዘለት ምርጫ ባይወዳደሩም 18 ዓመታትን ባስቆጠረው የስልጣን ዘመናቸው እርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች ላለችው አገር ምን ሰሩላት የሚለው ጉዳይ ደጋፊዎቻቸውንና ተቃዋሚዎቻቸውን እያወዛገበ ነው፡፡
ካቢላ እ.አ.አ በ2001 ወደ ስልጣን ሲመጡ ደካማ በሆነው የአገሪቱ ጦር ውስጥ ወሳኝ ስፍራ እንደነበራቸው የሚታወስ ነው፡፡ ከአውሮፓዊቷ ፈረንሳይ አምስት እጥፍ የበለጠ ስፋት ባላት በዚያች አገር ውስጥ ብረት አንስተው ሲዋጉ የነበሩ ከ25 የሚበልጡ ታጣቂ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሙከራ እንዳደረጉ ይነገርላቸዋል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ዜጎችን ለሞትና ከዚህ የበለጡትን ደግሞ ለስደት የዳረገውና ‹‹የአፍሪካው የዓለም ጦርነት (Africa’s World War)›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የእርስ በእርስ ጦርነት እ.አ.አ በ2003 ፍፃሜ እንዲያገኝ የካቢላ ሚና ትልቅ ነበር ይባላል፡፡ በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተፈረመ የሰላም ስምምነት ካቢላ ከአማፂያኑ መሪዎች ጋር ስልጣን ለመጋራት መስማማ ታቸው ለጦርነቱ ማብቃት ወሳኝ ሚና የተጫወተ እርምጃ እንደነበር ይገለፃል፡፡
በተለይ ደጋፊዎቻቸውና የአስተዳደራቸው ባለስልጣናት እንደሚናገሩላቸው ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱን ፀጥታ ሁኔታ አሻሽለውታል፡፡ የአገሪቱ ጦር ምክትል አዛዥ ዣን ፔር ካምቢላ ካክዌንዴ ‹‹ፕሬዚዳንት ካቢላ ወደ ስልጣን ሲመጡ አገሪቱ ለአራት ተከፋፍላ ነበር፡፡ በርካታ ታጣቂ ቡድኖችም ነበሩ፡፡ አሁን ግጭት ያለው በአንድ አካባቢ ብቻ ነው፡፡ ካቢላ በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ያከናወኑትን ተግባር እውቅና አለመስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ ጥያቄ ውስጥ የነበረው የአገሪቱ ሕልውና አሁን አስተማመኝ ደረጃ ላይ ይገኛል›› ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ በሰሜናዊ ኪቩ፣ ኢቱሪና ካሳይ ግዛቶች ያለው ግጭት በአካባቢዎቹ ያሉትን የአገሪቱን ዜጎች ሕይወት ለአስከፊ አደጋ የዳረገ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ የኖርወይ የስደተኞች ካውንስል ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው እ.አ.አ በ2018 ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ፍልሰት ተቆጣጠሪ ማዕከል (Internal Displacement Monitoring Center) መረጃ እንደሚሳየው ደግሞ በአገሪቱ በየቀኑ ከአምስት ሺ 500 የሚበልጡ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ይፈናቀላሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ካቢላ እንደአብዛኞቹ አፍሪካ መሪዎች ከሙስና ጋር በተያያዘ ስማቸው በክፉ ይነሳል፡፡ 80 ሚሊዮን ከሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ መካከል ከ63 በመቶ የሚበልጠው በቀን ከሁለት ዶላር ያነሰ ገቢ እንዳለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ የመብት ተሟጋች ድርጅቶችና የካቢላ ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንት በማዕድን የበለጸገችውን ሰፊ አገር ሀብት እየመዘበሩት ነው ሲሉ ተደጋጋሚ ክስ ያቀርቡባቸዋል፡፡ ካቢላና ቤተሶቻቸው በኮንጎና በሌሎች አገራት የሚገኙ ከ80 በላይ የሚሆኑ የንግድ ኩባንያዎችን በባለቤትነት እንደያዙ በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የኮንጎ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሪፖርት ያሳያል፡፡ ጃይኔት ካቢላ የተባሉት የፕሬዚዳንት እህትና የአገሪቱ ፓርላማ አባል ‹‹ቮዳኮም (Vodacom)›› በተባለው የአገሪቱ ትልቁ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ድርሻ እንዳላቸው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ ዞ ካቢላ የተባሉት የፕሬዚዳንት ወንድምና የፓርላማው አባል ደግሞ በዓለማችን በአዋጭነ ታቸው ተወዳዳሪ የላቸውም የተባለላቸውን የማዕድን ቁፋሮ ፕሮጀክቶችን የሚያከናውኑ ኩባንያዎች ባለቤት ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ‹‹ግሎባል ዊትነስ (Global Witness)›› የተባለው ዓለም አቀፍ የጸረ-ሙስና ተቋም አገሪቱ ለውጭ ገበያ አቅርባ ከምታገኘው የማዕድን ሽያጭ ገቢ ወደ ዓመታዊ በጀቷ የሚደርሰው ከስድስት በመቶ እንደማይበልጥ ባለፈው ዓመት ገልፆ ነበር፡፡ እ.አ.አ ከ2013 እስከ 2015 ባሉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ከማዕድናት ሽያጭ የተገኘ ገንዘብ ወደ አገሪቱ ካዝና ሳይገባ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ ተቋሙ እንደሚለው ይህ ገንዘብ አገሪቱ ለትምህርትና ለጤና ከምትመድበው ዓመታዊ በጀት በእጥፍ የበለጠ ነው፡፡
‹‹ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል (Transpa rency International)›› የተባለው የአገራትን የሙስናና መልካም አስተዳደር ደረጃ የሚገመግም (የሚለካ) ዓለም አቀፍ ተቋም እ.አ.አ በ2017 ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን በሙስናና በመልካም አስተዳደር ይዞታዋ ከ180 አገራት መካከል 161ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡
ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የዓለማችን ትልቋ የመዳብ አምራች ከመሆኗ ባሻገር 60 በመቶ የሚሆነው የዓለም የኮባልት ማዕድን መገኛም ናት፡፡ 80 በመቶ የሚሆነውን የወጪ ንግድ ገቢዋን የምታገኘውም ከሁለቱ ማዕድናት ሽያጭ እንደሆነ የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡
ይሁን እንጂ ኪንሻሳ ውንጀላው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመድፈርና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመዝረፍ በመጋረጃነት የሚቀርብ ክስ እንደሆነ በመግለፅ ከላይ የተጠቀሱትን ተቋማት መረጃ አትቀበልም፡፡ ዣን ፔር ካምቢላ ካክዌንዴ ‹‹ጦርነቱ ሉዓላዊነታችንን አስከብረን ሀብታችንን በሚገባ ለመጠቀም በሚፈልጉና ያንን በማይፈልጉ አካላት መካከል እንደሆነ ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል›› በማለት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚስተዋሉ ግጭቶችና በመንግሥት ላይ ከሚሰነዘሩ ተቃውሞዎች ጀርባ የሌሎች አካላት እጅ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
አል ኪቴንጌ የተባሉ የፖለቲካ ተንታኝ በበኩላቸው ሰራተኛ ከሆነው የአገሪቱ ሕዝብ መካከል ግብር የሚከፍለው ከአምስት በመቶ በታች እንደሆነ በመግለፅ፣ ግብር አለመክፈል ሙስናን እንደሚያ ስፋፋና የአገሪቱ ዜጎች ይህንን ማስተካከል እንደሚገባቸው ያስረዳሉ፡፡
ከምጣኔ ሀብት እድገት አንፃር የካቢላ የሥልጣን ዓመታት በበጎ የሚጠቀሱ ውጤቶች እንደታዩባቸው ይነገራል፡፡ ለአብነት ያህል የአፍሪካ ልማት ባንክ (Africa Development Bank) የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እ.አ.አ ከ2010 እስከ 2015 ድረስ ባሉት ዓመታት በአማካይ የሰባት ነጥብ ሰባት በመቶ እድገት እንዳሳየ ይፋ አድርጓል፡፡
የእርስ በእርስ ጦርነቱ የአገሪቱን የትምህርት ዘርፍ በእጅጉ እንደጎዳው ይገለፃል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋም (USAID) መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚበልጡ የአገሪቱ ሕፃናት ወደትምህርት ቤት ሳይሄዱ ቀርተዋል፡፡ የካቢላ መንግሥትም ይህን ለማሻሻል ለትምህርት የሚመድበውን በጀት በየዓመቱ ሲያሳድግ ቆይቷል፡፡
የፕሬዚዳንት ካቢላ መንግሥት ጨቋኝና የዜጎችን መብት አፋኝ ነው ተብሎም ይወቀሳል፡፡ ማርቲን ፋዩሉ የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት አመራር ‹‹የካቢላ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ያስራል፤ ያሰቃያል፡፡ ምርጫ በማጭበርበር በስልጣን ላይ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር ነው›› ይላሉ፡፡ የካቢላ ደጋፊዎች በዚህ አይስማሙም፡፡ እንዲያውም በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር አለመፈለጋቸው ሊያስመሰግናቸው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
ያም አለ ይህ ምርጫው ድጋሚ ካልተራዘመና ድንገተኛ ነገር ካልተፈጠረ በቀር 20 ዓመታትን ሊደፍኑ ሁለት ዓመታት ብቻ የቀሯቸው የፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ የስልጣን ጊዜያት ከሁለት ቀናት በኋላ ይደረጋል ተብሎ ቀን በተቆረጠለት ምርጫ የሚደመደም ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
አንተነህ ቸሬ