አዲስ አበባ፡- ኢህአዴግ አንድ ውህድ ፓርቲ ከሆነ አሃዳዊ ሥርዓትን ይፈጥራል፤ ብዝሀነትን ያጠፋዋል የሚለው ሀሳብ ቦታ የሌለውና ትርጉም የማይሰጥ መሆኑን ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ብዙ የፌዴራል አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንድ ፓርቲ በምርጫ ተፎካክሮ ካሸነፈ በፌዴራል ሥርዓት ስር ያሉ የክልል መንግስታትንም ያስተዳድራል። የኢህአዴግ ውህደት አሃዳዊ ሥርዓትን ያመጣል፤ ብዝሀነትን ይጨፈልቃል የሚለው ስጋት ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር አብሮ የሚሄድ አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም። ኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ ሲሆን በየክልል መንግስታት ውስጥ ቅርጫፎች ይኖሩታል። ውህደቱ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን ያሰፋል እንጂ አሃዳዊ ሥርዓት የሚያመጣ አይደለም ብለዋል።
ኢህአዴጎች ከ20 ዓመታት በላይ ግንባር እያሉ ሳይዋሀዱ የቆዩት ባይተማመኑ ነው የሚል ሀሳብ ነበረን የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ በዚህ ምክንያት ኢህአዴግ ለሌሎች ፓርቲዎች ጥሩ አርአያ እንዳልሆነም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ኢህአዴግ አምስቱ አጋር የሚላቸውን ፓርቲዎች በምንም ሚዛንና ምክንያት ያልተወያዩባቸውን ፖሊሲዎች እንዲፈጸሙ ግዴታ እንደሚጥልባቸው ገልጸው ይህ አካሄድ ኢህአዴግ አግላይ ድርጅት እንደሆነ ያሳያል ብለዋል። በዚህም የተነሳ አጋር ፓርቲዎችን በአገሪቱ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ለማድረግ በውህደቱ እንዲካተቱ ማድረግ አስፈላጊና ተገቢም ነው ብለዋል።
ከፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለምልልስ ከታች ባለው ሊንክ ያገኙታል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
ጌትነት ምህረቴ