አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ማህበር የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) 1494ኛ የልደት በዓል (መውሊድ) በዓልን አስመልክቶ በትናንትናው እለት በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ማህበሩ ለአገር አንድነት፣ ሰላምና ወንድማማችነት እንደሚሰራ ገለፀ።
የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የዝግጅቱ አስተባባሪ ወጣት መሀመድ ዘይኑ እንደገለፀው ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በተከሰተው አስከፊና አሰቃቂ፣ ኢትዮጵያዊነትን በፍፁም የማይገልፅ ተግባር አዝኗል፤ ድርጊቱንም ይቃወማልም። ወጣት መሀመድ እንደሚናገረው ማህበሩ አገር በቀል ሲሆን አላማውም በሃይማኖትና በአገር ልማትና እድገት ላይ እየሰራ ይገኛል።
ይህ ዝግጅት ሰሞኑን በአገራችን በተፈጠረው አስከፊ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ሊስተጓጎል ነበር፤ ይሁን እንጂ በፖሊስና የፀጥታ ሀይሉ ከፍተኛ ትብብርና ድጋፍ ሊካሄድ ችሏል የሚለው የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ የፀጥታ መደፍረሱ ጉዳይ በፍፁም መከሰትና መሆን የሌለበት ድርጊት ነው። ይህ በእኛ አገር ሊሆን ቀርቶ ሊታሰብ የሚገባ ጉዳይ አልነበረም ሲልም ይገልፃል።
የዚህ ዝግጅት አቢይ አላማ ዘንድሮ የሚከበረውን የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) 1494ኛ የልደት በዓል አከባበርን አስመልክቶ ከወዲሁ የደስታ ስሜት መፍጠርና ልደታቸውን ከታሪካቸው ጋር አያይዞ ለማስታወስ እንደሆነ የሚገልፀው ወጣት መሀመድ በዚህ ስሜት ውስጥ እያለ እንዲህ አይነት ነገር በአገራችን መፈጠሩ በግሉም ሆነ ማህበሩ ሃዘን እንደተሰማቸውና ወጣቱ በእንደዚህ አይነት ድርጊት ውስጥ መሳተፍ እንዳልነበረበት ይናገራል።
የአዲስ አበባ ሙስሊም ወጣቶች ማህበር እንዲህ አይነቱን አስከፊ ተግባር ሁል ጊዜ ያወግዛል ያለው ወጣት መሀመድ የማህበሩ ዋና ዓላማ ወጣቱ ሁል ጊዜ ለሀገሩ ልማት መስራት፣ ለሰላም እንዲጥር፣ እንዲሰራ ማስተማር፣ ማበረታታትና ማገዝ ነው ብሏል።
የመሻይኮቻችንም መንገድ የሚያስተምረን ይህንኑ መሆኑንና ቁርአንም ሆነ ሀዲስ የሚያስተላልፉትና የያዙት መልእክት ይህንኑ መተሳሰብን፣ መተዛዘንን፣ በፍቅር አብሮ መኖርን፣ መስራትንና ማደግን ነው እንጂ እንዲህ አይነቱን ተግባር አላስተማሩንም ሲል ይገልፃል። በመሆኑም ማህበራችንም ከዚህ ውጪ አይደለም። የሚያስተምረውም ሆነ የሚያስተላልፈው መልእክት ከዚህ ውጪ አይደለም ሲልም ሃሳቡን ገልጿል።
እንደ ወጣት መሀመድ ገለፃ በአሁኑ ሰአት አገራችን ላይ እየታየ ያለው ነገር ፍፁም የማይጠበቅ፣ አስቀያሚና አሳዛኝ ነው። በመሆኑም ወጣቱ ፊቱን ወደ ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ሳይሆን ወደ ሃይማኖቱ፣ ባህሉና ወላጆቹ ወደሚሉት መመለስ አለበት። ከእንደዚህ አይነቱ ተግባር ፍፁም መራቅ ነው የሚገባው። ማህበራችንም የሚለው እና የሚደግፈው ይህንን ብቻ ነው። ወጣቱ ሰላም ከሌለ ምንም ነገር እንደሌለ ሊገነዘብ ይገባል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ፕሬዚዳንት ሀጂ ኡመር ሙፍቲ በበኩላቸው እየተፈፀመ ያለው ተግባር ከማሳዘንም አልፎ እንዳስለቀሳቸው የጠቀሱ ሲሆን “ሁላችንም አንድ እንሁን፣ ሰላም እናስፍን፣ ከእንደዚህ አይነቱና አላህ ከማይወደው ተግባር እንራቅ፣ እስላም ክርስቲያኑ ሁሉ በአንድ ሆነን አገራችንን እናልማ፣ ሰላም እንፍጠር፣ ከመተላለቅ እንዳን። እባካችሁ ሁላችንም ለአላህ ብለን ከዚህ ተግባር እንቆጠብ” ብለዋል።
ሃጂ ኡመር ሙፍቲ ሰላማችን የጠነከረ፣ አንድነታችን የጎለበተ፣ እድገታችን የተፋጠነ እንዲሆን እንድንጥር አላህን እለምናለሁ ብለዋል። “ሰላም ማጣታችን ያሳዝናል። ፍቅር ማጣታችን ያሳዝናል። ኡለማዎችንን ማስለቀሳችን ያሳዝናል። አንድነት ማጣታችን ያሳዝናል። አሁን አንድ ሆነን ቆራጥ ሆነን ልንነሳ ይገባል። አንድ እንሁን፤ የከተማውም የገጠሩም እስላም እና ክርስቲያኑም አንድ እንሁን። አንድ ሆነን ቆራጥ ሆነን እንነሳ። እውነቱም ይታወቃል፤ ውሸቱም ይታወቃል። ለእውነት እንድትሰሩ አሳስባለሁ። አደራም እላለሁ። አሚን።” በማለት መልእክታቸውን ለመላው የእስልምና ተከታይ ማህበረሰብና የኢትዮጵያ ህዝብ አስተላፈዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
ግርማ መንግስቴ