አዲስ አበባ፡- ላለፉት 28 ዓመታት ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረው የመንግስታዊ ሥርዓት ባህሪ አሃዳዊ እንደነበረ በፌዴራሊዝም ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሰላም ሚኒስቴር ትናንት በዋሽንግተን ሆቴል ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉ ሃሳብ አቅራቢዎች ገለጹ።
በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ልዩ ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዶክተር ደገፋ ቶሎሳ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት 28 ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው መንግስታዊ ሥርዓት ፌዴራላዊ ነው በሚል በመንግስት በኩል ሲቀነቀን ቢኖርም በተግባር ግን የአሃዳዊ አስተዳደር ባህሪ የተላበሰ ነበር፡፡
ዶክተር ደገፋ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች መነሻቸው ረጅም ዓመታት ወደ ኋላ የሚወስድ ቢሆንም ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በሕገመንግስቱ መሰረት ሰጥቻለሁ የሚለው ኢህአዴግም ቢሆን ለዜጎች ጥያቄ መፍትሄ ያመጣ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን እውን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከሀገራዊ ግንባታ ይልቅ በብሔር ማንነት ግንባታ ላይ ብቻ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ኖሯል የሚሉት ዶክተር ደገፋ፤ አሁን በተጨባጭ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ችግሮችም የዚህ ተግባር ተጨባጭ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በበኩላቸው፤ ባለፉት ጊዜያት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው ራስን በራስ የማስተዳደርና በክልልነት የመዋቀር ሂደት በሕገመንግስቱ መሰረት የተዋቀረ ነው ቢባልም ቅሉ በሕገመንግስቱ ላይ የተቀመጡትን ማንነትን መሰረት ያደረገ፣ በሕዝቦች አሰፋፈር ላይ የተመሰረተ፣ በስነልቦና መገናኘትንና መተሳሰርን ያገናዘበ እና በሕዝቦች ፍላጎትና ስምምነት ላይ የተመሰረተ አከላለልን ሙሉ በሙሉ የተከተለ ሳይሆን ማንነትንና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን ብቻ መሰረት ያደረገ እንደነበረ አስረድተዋል፡፡ በተግባር መሬት ላይ ሲውል የሚታየው እውነታ ከፌዴራሊዝም ሥርዓት ባህሪያት ይልቅ የአሃዳዊ ሥርዓት ባህሪው ጎልቶ ይስተዋል ነበርም ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ በክልሎችና በፌዴራል መንግስት መካከል የሚስተዋለው የእርስበርስ ግንኙነት የተሳለጠ አለመሆን፣ ክልሎች ራሳቸውን እንደ ደሴትና እንደሌላ ሀገር እየቆጠሩ መምጣት፣ በፌዴራልና በክልሎች ሕገመንግስት መካከል የሚስተዋለው መጣረስ፣ በክልሎችና በክልሎች መካከል የሚስተዋሉ መልካም ያልሆኑ መስተጋብሮች እና ክልሎች የራሳቸውን የበጀት ምንጭ ፈጥረው ሙሉ በሙሉ የመጠቀም መብት አለመጎናጸፍ እና ሌሎች የሚስተዋሉ በርካታ የአሰራር ሂደቶች ከፌዴራላዊ ሥርዓት ባህሪያት ይልቅ ለአሃዳዊ ሥርዓት የሚቀርቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ስንከተለው የነበረው ራስን በራስ የማስተዳደር ሥርዓት የነበሩበት እጥረቶች አንድ ባንድ ተነቅሰው የተለዩ ከመሆኑም በላይ መደመር ለእነዚህ ጥያቄዎች በተገቢ ሁኔታ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ስዩም፤ መደመር በነበሩት ጥንካሬዎች ላይ ክፍተቶቹን በመሙላት በሀገራዊ አንድነታችን ጥላ ስር ሕብረብሔራዊነታችን ተጣጥሞ ሀገሪቱን የሚያሻግር ስልት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስትከተል የነበረው ሥርዓት ፌዴራላዊም አሃዳዊ አይደለም ይልቁንም የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የፓርቲ ሥርዓት ነው ያሉት ደግሞ የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ናቸው፡፡ አቶ አብርሃ አክለውም ላለፉት 28 ዓመታት በአገሪቱ ሲተገበር የነበረው የፌዴራሊዝም ሥርዓት በብዙ ቸግሮች የተተበተበ ነበር ካሉ በኋላ በማሳያነትም በትግራይ ክልል ሶስት ብሄረሰቦች ቢኖሩም ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት ሰይኖራቸው ተገልለው ኖረዋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
ሙሐመድ ሁሴን