አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ በሂደት ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በማጠናቀቅ እና ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በዘንድሮ ዓመት ብቻ ለ129 ሺ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መዘጋጀቱን አስታወቀ።
በቢሮው የኢንቨስትመንት ድጋፍና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ በላይ ዱፌራ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የሥራ አጥ ችግር ሊፈታ የሚችለው ኢንቨስተሮች ሲበራከቱ ብቻ ነው። በመሆኑም ወደ ክልሉ የሚፈሱ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር ለማበረታታት ደንብና መመሪያዎችን በማሻሻል ጭምር እየተሰራ ነው።
እስካሁን በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት 10ሺ742 መካከል ስድስት ሺ አንድ መቶ አስሩ ወደ ማምረት ሥራ መግባታቸውን የጠቀሱት አቶ በላይ ቀሪዎቹ አራት ሺ 300ዎቹ ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በሂደት ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች በያዝነው ዓመት ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ ሲሆን በዚህም ለ129ሺ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ሲሉ አስረድተዋል።
ደንቡ የተሻሻለበት ዋና ምክንያት ያለ ኢንቨስትመንት እድገት የለም፣ የሥራ አጥ ቁጥርንም መቀነስ አይቻልም ተብሎ በመታሰቡ መሆኑን ገልጸዋል። በማሻሻሉም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በሚያበረታታና የውጭ ባለሀብቶችን ፍሰት በሚያሳድግ መልኩ ቀደም ሲል የነበረውን የኢንቨስትመንት ሕግና ደንብ ተቃኝቷል።
አቶ በላይ እንዳሉት ከዚህ በፊት 141/2004 የሚባል የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ደንብ የነበረ ቢሆንም ሀገሪቱ እያደገች ካለችበት ሁኔታ ጋር በማጣጣም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ወደ ክልሉ እንዲመጣ ለማመቻቸት የክልሉ መንግሥት አዋጅና ደንቡን እንደገና አይቷል።በዚህም በከተማና በገጠር ተከፋፍሎ ሲደራጅና ሲደገፍ የነበረውን ኢንቨስትመንትም ወደ አንድ እንዲመጣ አድርጓል።
ደንብ 141 መመሪያ 1/2004 ከግብርና እና ከማይክሮ ኢንተርፕራይዝ ወደ ኢንቨስትመንት የተዘዋወሩ ባለሀብቶችና በተለያየ አቅጣጫ ንብረት ያፈሩ ሴቶችን በልዩ ሁኔታ የሚያበረታታ እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ አሁን ይህ ደንብ ከዓመት ዓመት ንብረት እያፈሩ ያሉ ገበሬዎችን ወደ ኢንዱስትሪ፣ ማይክሮ ኢንተርፕራይዞችንም ወደ መካከለኛና ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገሩ ያደርጋል።በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ባለሀብት በኢንቨስትመንት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ የውጭ ባለሀብቶችንም ይጋብዛል።
አቶ በላይ እንዳሉት በ2010 ዓ.ም በሀገሪቱ ከነበረው የሰላም ሁኔታ ጋር በተያያዘ ኢንቨስትመንት የቀነሰበት ሁኔታ ነበር።ከ2011 ጀምሮ ግን ወደ ቦታው ተመልሷል።አሁንም ያለው ፍሰትም ጥሩ ነው።በርካታ ባለሀብቶች ለማልማት እየጠየቁ ሲሆን መንግሥትም ድጋፍ እያደረገ እና መሬት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
አልማዝ አያሌው