አምቦ ፡- የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የወጣውን የስነምግባር መመሪያ መሰረት በማድረግ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሂደቱን መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት ዩኒቨርሲቲው መመሪያውን ለተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ ያስተዋወቀ ሲሆን በዚሁ መሰረት ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን የስነምግባር ደንብ አሟልተው ገብተዋል።
ተማሪዎቹ ለመመሪያው ተገዥ በመሆን ጸጉራቸውንና አለባበሳቸውን አስተካክለው ወደ ዩኒቨርሲቲው መምጣታቸውን የጠቆሙት ዶክተር ታደሰ ይሁን እንጂ በተማሪ፣ መምህርና ሰራተኛው ውስጥ አንዳንድ የዲስፕሊን ግድፈቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ እነዚህን ችግሮች በሂደት ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
አብዛኛውን ማህበረሰብ ይዞ ችግር ያለባቸውን ደግሞ እየነገሩ፣ እያስተካከሉና እያስተማሩ በመሄድ በሂደትም መሻሻሎችን ለማስመዝገብ ተስፋ መኖሩን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ምዝገባ አጠናቀው ትምህርት እየጀመሩ በመሆኑ እስካሁን ድረስ መመሪያውን ስራ ላይ ለማዋል በተደረገው ጥረት ምንም ችግር አለመግጠሙንና ቀሪውን በሂደት ለማስተካከል እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ለአዳዲስ ተማሪዎች እንጂ ለነባር ተማሪዎች አጠቃላይ ገለጻ አይሰጥም ነበር ያሉት ዶክተር ታደሰ ዘንድሮ ግን ለሁሉም ተማሪዎች ገለጻና ማብራሪያ መሰጠቱንም ጠቅሰዋል። ከሰራተኛው እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋርም ምክክር መደረጉን የተናገሩት ዶክተር ታደሰ አስቀድመን ከሰራናቸው ስራዎች እና ካደረግናቸው ጥረቶች አንፃር የትምህርት ዘመኑ በተሻለ መልኩ በሰላም ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለ ብለዋል።
ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የሚሰጡ አዳዲስ ኮርሶችን በሚመለከት የመምህራን ቅጥር፤ የክፍል ዝግጅት እና የመጽሀፍት ግዢ በመፈጸም በቂ የሚባል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
ከማህበረሰብ አገልግሎት እና ምርምር ጋር ተያይዞ ስራዎችን በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ታደሰ ብዙ ፕሮጀክቶች ተሰርተው ህብረተሰቡ ጋር መድረሳቸውን አስታውሰዋል። በተለይ በግብርና አርሶ አደሩን የሚረዱ አነስተኛ መካናይዜሽንና ሌሎችም በየዘርፉ የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት በ15 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክቶች መካሄዳቸውንና ከዓመት ዓመት የሚሸጋገሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸው የምርምር ወርክሾፖች እውቀት በሚሸጋገርበት ዘርፍ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር