መንዝ ላሎ፡- የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ላሎ ምድር ወረዳ ከፍተኛ የምስርና ጤፍ ምርት የሚገኝ ቢሆንም በመንገድ፣ መብራትና የውሃ ችግር የግብርና ምርቱን እሴት ጨምሮ ወደ ገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለ ተገለጸ።
በሰሜን ሸዋ ዞን የመንዝ ላሎ ምድር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገብረህይወት በዛብህ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ አርሶ አደሩ ከፍተኛ የምስር እና ጤፍ ምርት የሚያገኝ ቢሆንም ይህን አቀነባብሮ እና እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ የመብራት መቆራረጥ በዋነኛነት እንቅፋት ሆኖባቸዋል።ከዚህ በተጨማሪ ገበሬው ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ ለማድረስ የሚያስችል ምቹ መንገድ የለም።
‹‹በወረዳው በተለይ ደግሞ በ07 ጦላ አካባቢ ከፍተኛ የጤፍ እና የምስር ሰብል ይመረታል።ታዳጊ ከተማም ነው›› ያሉት የወረዳው ዋናው አስተዳዳሪ የመንገድ ችግርና የመብራት መቆራረጥ ግን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።አስተዳደሩም ሆነ በወረዳው የሚገኘው ማህበረሰብ በተደጋጋሚ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሟላ ጥያቄ እያቀረበ ቢሆንም እስካሁን ግን ምላሽ አላገኘም ብለዋል።
እንደ ወረዳው አስተዳደሪ ገለፃ፤ የውሃ እጥረት ችግር በወረዳው አቅም የሚፈታ ባለመሆኑ የክልል እና የዞን ድጋፍ የሚጠይቅ ነው።ይህ ከተሟላ ማንኛውም ባለሀብት እሴት ጨምሮ ለገበያ የሚያቀርባቸው ምርቶችን ማምረት የሚቻልበት ሰፊ የኢንቨስትመንት ቦታዎች አሉ።አስተዳደሩም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኝ በችግሮቹ ዙሪያ ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት፤ አጠቃላይ ሰሜን ሸዋ በተለይም መንዝ በመሰረተ ልማት ወደኋላ የቀሩ ሆኖም ግን አሁን መንዝ ላሎ፣ መንዝ ማማና መንዝ ጌራ ጨምሮ ስድስቱም የመንዝ ወረዳዎች የአስፋልት መንገድ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፕሮግራም ተይዞ ስራው ተጀምሯል።
‹‹አሁን ያለው ችግር በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ መጓተት እና የጥራት ችግር እንዳለ እናውቃለን›› ያሉት የዞኑ አስተዳደር ይህን እክል ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ማስተካከያ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል።አሁን የተጀመሩ እና በቀጣይ ጨረታ ወጥቶ የሚጀመሩት አዲስ የመንገድ ግንባታዎች ውስጥ ሁለት ወረዳዎች ብቻ በአስፋልት አይተሳሰሩም›› ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ቀሪዎቹ 26 የሚሆኑት ወረዳዎች በአስፋልት ለማስተሳሰር እቅድ ተይዟል ብለዋል።ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችን በመስራትም የአካባቢውን ታሪክ ለመቀየር በመንግስት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
ዳግም ከበደ