አዲስ አበባ፡- የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት መስራት እንደሚገባቸው ተገለጸ።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትናትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በአገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር “በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላምን መገንባት” በሚል ርዕስ ውይይት አካሂዷል። በዕለቱ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሰለሞን እንዳሉት በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየው ሁከት የአመራሮች ችግር ነው። ማንኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መሪ የአመራርነት ሚናውን ለመወጣት መጀመሪያ ከራሱ ጋር ሊታረቅ ይገባዋል።
እራሱን ያወቀ መሪና ለራሱ ሰላም ያለው መሪ ለሚመራው ተቋም ሰላም ለመፍጠር አይቸግረውም።በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ያሉ ተማሪዎች እየሰጡን ያሉት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ለተማሪዎቻችን የሰጠናቸውን ነው ።ስዚህም ከራሳችን ጋር እንታረቅ ብለዋል።ራሱን ያወቀ መሪ ለምን እንደተሾመ እና ምን ለመስራት እንደተቀመጠ ከአወቀ ለተቋሙ እሴቶች በመስራት ይጠመዳል። ችግር ቢያጋጥመው እንኳን ለማለፍ በራስ መተማመኑ ከፍ ያለ ይሆናል ብለዋል።
ሌላኛው የጥናት አቅራቢ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው በየተቋሙ ተማሪዎች አንደኛው የሌላውን ባህል እና ሀሳብ ማክበር እንዳለበት ገልጸዋል።ህብረብሔራዊነት የእውቀት ምንጭ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ እያንዳንዱ ግለሰብ እንደመጣበት አካባቢ የራሱ የሆነ ልዩ ባህል እና ልምድ አለው። ይህን በመቻቻል እና ልምድ በመለዋወጥ ለአገር ሰላም እንዲሆን የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ ለተግባራዊነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።በየተቋማቱ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች፣ መምህራንና የተማሪዎች ህብረትን በህብረብሔራዊነትን፣ በመቻቻል ላይ ተማሪዎች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማስተማርና ማወያየት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩበት ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም አቀፍ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወይዘሮ ሂሩት በፍቃዱ እንዳሉት ሰላምን ለማምጣት በመጀመሪያ ሰላምን የሚፈጥሩ እሴቶችን ማጎልበት ያስፈልጋል። የሰላም ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በአገር ውስጥ ሰላምን መፍጠር ይቻላል።በመግባባት እና በንግግር የማይፈቱ ነገሮች እንደሌሉም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
አብርሃም ተወልደ