አዲስ አበባ፡- ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ሕዝብንና ዕቃዎችን የሚያመላለሱ ባቡሮች በቀጣዩ ዓመት ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ሹፌሮች የሚሽከረከሩ መሆኑን የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰርካ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ባቡሮቹ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል በኢትዮጵያውያን ረዳትነት በቻይናውያን ሲሽከረከሩ ቆይተዋል። ይሁንና በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያውያን ባቡሮቹን ከቻይናውያን ሙሉ በሙሉ በመረከብ ያሽከረክራሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ስልሳ አምስት ኢትዮጵያውያን የባቡር አሽከርካሪዎች በሀገር ውስጥ የሚሰጣቸውን ሥልጠና ያጠናቀቁ ሲሆን በሁለት ዙር ለተጨማሪ ሥልጠና በቅርቡ ወደቻይና ይላካሉ። በቻይና በሚኖራቸው ቆይታም የቻይና የባቡር ቢሮ በምን መልኩ ሥራውን እያከናወነ እንደሆነና ከባቡር ማሽከርከር ሞያ ጋር የተያያዙ ትምህርቶችን ቀስመው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚሁ የባቡር ሹፍርና ሰልጣኞች ባቡር የማሽከርከር ልምዳቸውን በማካበት ከአንድ ዓመት በኋላ ባቡሩን ከቻይናውያን ሙሉ በሙሉ ተረክበው ያሽከረክራሉ ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ሥልጠናውን በቻይና እንዲወስዱ የተፈለገበት ዋነኛ አላማ በቅርቡ በባቡሩ ላይ ከደረሰው አደጋ አኳያ አሽከርካሪዎቹ የበለጠ እውቀት እንዲይዙና የባቡር ጉዞ ደህንነትን ለማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም የባቡር አሽከርካሪዎቹ ሥልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀጣይ የጥገና ባለሞያዎችና የኤሌክትሪክ ጣቢያ ተቆጣጣሪዎች ተመሳሳይ ሥልጠናዎች ተሰጥቷቸው በእወቀት ከበቁ በኋላ ቻይናውያን ባቡሩን የማስተዳደር ሥራ ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያውያንና ጂቡቲያውያን እንደሚያስረክቡም አመልክተዋል።
ለዚህም በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ ያሉ ሞያዎች ተለይተውና ፕሮግራም ወጥቶላቸው ሠራተኞች እንዲሰለጥኑ ዝግጅት መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርትን የቻይናዎቹ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እና የባቡር ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በጥምረት እያስተዳደሩት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያውያንና ጅቡቲያውያን ባቡሩን ሙሉ በሙሉ ከቻይናውያን ተረክበው ያንቀሳቅሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
አስናቀ ፀጋዬ