-ገንዘቡ የኢትዮጵያን ብድር በአንድ ቀን መክፈል ያስችላል
ኢህአዴግ ወደሥልጣን ከመጣ ጀምሮ 30 ቢሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ መሸሹን እና ገንዘቡንም ለማስመለስ መንግሥት ከባድ ሥራ ከፊቱ እንደሚጠብቀው ምሁራን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በበኩላቸው ከሀገር የሸሸውን ገንዘብ ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢጠይቅም መንግሥት ጉዳዩን እንደሚከታተለው ቢያሳ ውቁም ምንም ተግባራዊ ነገር እንዳልታየ ምሁራኑ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ እንደገለጹት፤ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ከኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገራት በሙስና እና ማጭበርበር የሸሸው ገንዘብ 30 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ በጥናት ተረጋግጧል። ገንዘቡ በወቅቱ የኢትዮጵያን የስድስት ዓመት ተኩል በጀት መሸፈን የሚችል ወይም አሁን ያለውን የውጭ አገር የመንግሥት ብድር በአንድ ቀን ከፍሎ መጨረስ የሚያስችል ነው።
ጥናቱ ሲሰራ በሀሰት ደረሰኝ የወጪ ንግዱ ላይ በማጭበርበር፣ ከእርዳታ የተገኘውን እና ጥቅም ላይ የዋለውን ልዩነት በመመርመር እንዲሁም በቀጥታ በሙስና የወጡ ገንዘቦችን ተመርኩዞ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር አለማየሁ፣ በተለይ በእርዳታ የሚገባው ብር እና ተግባር ላይ የሚውለው ብር ከፍተኛ ልዩነት እንደነበረውና ለሌብነት የተጋለጠ እንደነበር አስረድተዋል።
የሸሸው ገንዘብም በግለሰቦች አካውንት እና በባለሥልጣናት የባንክ አድራሻ ነው ወደውጭ የወጣው የሚሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ደግሞ የግለሰቦችን አካውንት የመመርመር ሥልጣን ስለሌለ የማስመለሱ ጉዳይ ከባድ ቢሆንም በመርህ ደረጃ መብት ባይኖርም በፖለቲካ ጥያቄ ግን ተጽእኖ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ፕሮፌሰር አለማየሁ ከሆነ፤ ሕጉ ባይፈቅድም አሜሪካ፣ አረብ አገራት እና አውሮፓውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በጥሩ መልኩ ስለሚቀበሉ የመንግሥትን የመርምሩልኝ ጥያቄ ሊቀበሉ ይችላሉ። በመሆኑም ጉዳዩ የፖለቲካ ጥያቄ ነው የሚሆነው። አሜሪካን እና የተለያዩ ሀገራትን ስለሸሸው ገንዘብ መገኛ እና መረጃ አጣሩልኝ በማለት ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሸሸው ገንዘብ የማስመለስ ጥረት ይደረጋል ቢሉም እስከአሁን ግን ተጨባጭ እና ተግባራዊ ጉዳይ አልታየም ሲሉ ፕሮፌሰሩ ሀሳባቸውን ይቀጥላሉ። በሌላ በኩል ግን አሁንም በርካታ ገንዘብ ከሀገር እየሸሸ በመሆኑ በእጅ ያለውንም መቆጣጠር ያስፈ ልጋል።
የፋይናንስ አሠራር ቁጥጥር እና ምርመራን በማጠናከር በማጭበርበርም ሆነ በሙስና ግለሰቦች አካውንት እንዳይገባ ካልተሰራ ትርፉ ድካም ነው የሚሆነው።
በፋይናንስ እና ታክስ ጉዳዮች ለ50 ዓመታት የሰሩት ፕሮፌሰር ፍሰሐጽዮን መንግሥቱ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በአፍሪካ በየዓመቱ ካደጉ አገራት ከሚደርሰው እርዳታ ይልቅ በየዓመቱ ከአህጉሪቷ በሕገወጥ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ በቢሊዮኖች ዶላር ብልጫ አለው። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው።
ሀገር ወዳድነት በመቀነሱ እና በታማኝነት የሚያገለግሉ ባለሥልጣናት ጥቂት በመሆናቸው በርካታ ገንዘብ ከሀገር ሸሽቷል፤ አሁንም እየሸሸ ነው። በመሆኑም ገንዘቡ እንዳይወጣ ከፍተኛ ቁጥጥር ከማድረግ በተጨማሪ የእስካሁኑ የት ደረሰ፣ በማን ስም እና እንዴት ወጣ የሚለው በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሰነድ ያስፈልገዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ፍሰሐጽዮን ከሆነ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገንዘቡን የማስመለስ ጥረት እንደሚደረግ ቢገልጹም የታየ ግልጽ ነገር ግን የለም። በሌላ በኩል የውጭ ባንኮች ገንዘቡ ከየትም ይምጣ ከየትም ተቀብለው ለብድር እና ለተለያዩ ሥራዎች እየተጠቀሙበት ነው። የባንኮች የሕግ፣ አሠራር እና መብት የማንንም ገንዘብ ማንኛውም መንግሥታት እንዲወስድ አይፈ ቅድም።
በመሆኑም ገንዘቡን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ቀላል አይሆንም። ይሁንና በቅድሚያ ጠንካራ የፋይናንስ ደህንነት ተቋማትን በማጠናከር እና ሀገር ወዳድነቱን በጎን በማሳደግ ገንዘቡ እንዳይወጣ ከወጣም አካሄዱን በመረጃ ብቻ ሳይሆን በማስረጃ ጭምር አስደግፎ መከታተል ያስፈልጋል። መንግሥት የወጣ ውን ብር ለማስመለስ ከመሞከር ባሻገር ማን፣ ምን ያህል፣ መቼ እን እንዴት ባለ መንገድ ገንዘብ ከሀገር አሸሸ የሚለውን በዝርዝር አጥንቶ ለቀጣዩ እርምጃ መዘጋጀት አለበት።
የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ በበኩላቸው በጉዳዩ ዙሪያ እንደሚያብራሩት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ግሩፕ (ኤግሞንት) አባል ከሆነች ሦስት ወራት በመቆጠሩ በአሁኑ ወቅት በየሀገራቱ ከሚገኙ 164 የፋይናንስ ደህንነት ተቋማት ያለምንም ክልከላ መረጃ የማግኘት መብት ይኖራታል።
በመሆኑም በአገር ደረጃ የሸሹ ገንዘቦችን መገኛ እና ተጨባጭ መረጃ የሚያሰባብስ ጥናት ተጀምሯል። ከሀገር የሸሸ ተብሎ በየሚዲያው የሚገለጸው የተለያየ ቢሆንም ማጣራቱ ሲደረግ መጠኑን በተጨባጭ ማወቅ ይቻላል። በጉዳዩ ተጠርጥረው መረጃ እየተሰበሰበባቸው የሚገኙ ሰዎችንም በተመለከተ ምርመራ እየተካሄደ በመሆኑ ጊዜው ሲደርስ ይፋ ይደረጋል ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።
እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ ተጨባጭ ምንጭ እና መረጃ ላይ ሲደረስ የትኛውንም ሀገር ስለሸሸው ገንዘብ መገኛ እና በማን ስም እንዳለ ያለከልካይ መረጃ ማግኘት ይቻላል። የግል ዓለም አቀፍ ባንኮች ውስጥ ገንዘቡ ቢኖር እንኳን በዚያው አገር ያለው የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል መረጃ የመስጠት ግዴታ ስላለበት መተባበሩ አይቀርም። በጉዳዩ ላይም በመንግሥት ደረጃ የሰላም ሚኒስቴር የሚሳተፍበት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
ጌትነት ተስፋማርያም