አዲስ አበባ፡- በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ለተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሕንፃ ግንባታ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዟል። በስድስት ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ያሉ 17 ሕንፃዎችም ተጀምረው በግንባታ ላይ ይገኛሉ።
የፌዴራል ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለፃድቅ ተክለአረጋይ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2012 ግንባታቸው እየተከናወኑ ከሚገኙት 17 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ በአራት ፕሮጀክቶች የ7 ሕንፃዎች ግንባታ ይጀመራል። አጠቃላይም በአሥር ፕሮጀክቶች የሚሰራ ይሆናል።
እንደ አቶ ተክለፃድቅ ገለጻ፣ ለተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የተለያዩ ቦታዎች ተመድበው ግንባታዎች እየተካሄዱ ሲሆን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወሎ ሰፈር አካባቢ፣ የፌዴራል ዳኞች አፓርትመንት ቦሌ ክፍለ ከተማ አምቼ አካባቢ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ፣ ለብሔራዊ ቴአትር ሕንፃ ግንባታ ልደታ ክፍለ ከተማ አካባቢ፣ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ቦሌ፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት አራዳ ክፍለ ከተማ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ፣ የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ኤጀንሲ ልደታ ክፍለ ከተማ ዲ አፍሪክ ሆቴል አጠገብ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሲሆኑ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል። ግንባታቸው ያልተጀመሩ ፕሮጀክቶች በቅርቡ እንደሚጀመሩ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የሕንፃዎቹ መገንባትም መንግሥት በየዓመቱ ለመንግሥት መስሪያ ቤቶች ኪራይ የሚያወጣውን 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ እንደሚያስችለው ኃላፊው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
ዋለልኝ አየለ