የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች የአገር ሰላም እንዲመለስ መስራት እንዳለባቸውና መንግሥትም የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲሉ ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን የሰጡ የኃይማኖት መሪና አባገዳ ተናገሩ። ኅብረተሰቡም ያሉትን ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነና በተረጋጋ ሁኔታ ሊያቀርብ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
ከሰሞኑ በአገራችን የተከሰቱ ጉዳዮችና ወደፊትም መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳባቸውን ያካፈሉት አባገዳ ጎበና ሆላ ‹‹ከሰሞኑ የተደረገው ድርጊት የማይጠበቅ ነው። አገሪቱ ቀደም ሲል ራሷን አስከብራ የኖረች ናት፤ እናም እንዲህ ዓይነቱ አለመግባባት እየሰፋ የሚመጣ ከሆነ መለያየት ያስከትላልና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል» ብለዋል።
አባገዳ ጎበና አያይዘውም ‹‹የምንናገረውንም ሆነ የምናደርገውን ነገር በአግባቡ በመፈተሽ ማድረግ ይጠበቅብናል። ሕዝቡም ‹እከሌ እንዲህ አለ፤ እከሊት እንዲህ አለች› በማለት ነገር መቆፈርን ሊተው ግድ ይላል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነውና ስህተት ቢኖር እንኳ በመነጋገር መፍታትና አንዱ ከሌላው እንዲማር ማድረግ ይጠበቅብናል እንጂ ባላስፈላጊ ነገር የማንም ሕይወት መጥፋት የለበትም›› ሲሉ ገልፀዋል። ‹‹ይህች አገር ፈጣሪ ያላትና ሕዝቡም የሚሰማ ነውና የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችም የአገር ሽማግሌዎች ሰላሟ እንዲመለስ መስራት አለባቸው። ከምንም በላይ ደግሞ መንግሥት የሕዝብን ሰላም ማረጋገጥ ይኖርበታል›› ሲሉ መክረዋል።
«ምንም ዓይነት ጥያቄ ቢኖር በመረጋጋት ማቅረብ ይቻላል፤ አንድ ነገር በጉልበት ማግኘት አይቻልም።
ሰው መግደል፣ ጉዳዩን ወደኃይማኖት መቀየርና ሌላም ሌላም ማድረግ መልካም አይደለም። ሁሉም ሰው መብት አለው። እኔ መብቴን ስጠይቅ የሌላውን በመጣስ መሆን የለበትም» ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት መጋቤ ፃድቁ አብዶ ናቸው።
መጋቤ ፃድቁ አክለውም «እኛ በብሔር ወይም በኃይማኖት የምንጋጭ ከሆነና በተለይ ደግሞ ነገሩ ወደኃይማኖት ከዞረ በጣም አደገኛ ነው የሚሆነው። ማንም ጥያቄ ያለው አካል የሌላውን ሰው መብት ሳይጥስና ሕይወት ማጥፋት፣ መንገድ መዝጋትና ንብረት ማውደም ሳይጠበቅበት ተረጋግቶ መጠየቅ ይችላል» ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ እንደተናገሩት «መንግሥት ማድረግ ያለበት በአራቱም አቅጣጫ ያለው ሕዝብ እንደማይጎዳ ማረጋገጥ መቻል ነው። ሁሉም በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባም መስራት ይጠበቅበታል። የቄሮም ደም ሲፈስ የነበረው ይህን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ነበር። ይህንን ደግሞ መንግሥትም ያውቀዋል።» ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ እንደተናገሩት አባ ገዳዎችን ጨምሮ ሌሎችም ታዋቂ ፖለቲከኞች ወጣቶች ሰሞኑን የተደረገውን የመንገድ መዘጋቱንም ሆነ ሌላውንም ነገር አቁሙ ስላሏቸው ማቆም ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም መማርና መስራት ይገባል። ወደየሥራም መመለስ የግድ ይላል።
ካሉ በኋላ አክለውም፤ «በአጠገባችን ካለው ሕዝብ ጋር በመከባበር መኖር ይጠበቅብናል። የኦሮሞን ሕዝብ ከፋፍለው በመካከል ለመግባት የሚፈልጉ ኃይሎች ስላሉም መከፋፈል የለብንም ዓላማቸውንም ማወቅ ይገባናል» ሲሉ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
አስቴር ኤልያስ