አዲስ አበባ፡- ከቀርከሃ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግና የባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ብሎም ዘርፉን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የላከው መግለጫ እንደሚያስረዳው በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክ ቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ከዓለም አቀፉ የቀርከሃና የራታን ማህበር ጋር በመሆን በቀርከሃ ምርት ዙሪያ 22 ለሚሆኑና በዘርፉ ለተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ከጥቅምት 14 ቀን ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል። ሥልጠናው ከቀርከሃ የሚገኘውን ጥቅም የበለጠ ለማዘመንና ለማሳደግ የታሰበ ነው።
በባለሥልጣኑ የቀርከሃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙላቱ ተሻለ እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪውን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ማዘመን ስለሚገባና በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ሙያ በማሻሻል፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራትና የቀርከሃን ምርት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ሥልጠናው የላቀ ፋይዳ አለው። ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለመላመድም ዕድል ይሰጣል።
እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ ሥልጠናው የቀርከሃ ምርቶችን ለረጅም ጊዜ ሳይበላሹ መጠቀም በሚቻልበትና የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ የአመራረት መንገዶችን ማሳየትን ጨምሮ የቀርከሃን ምርትን አስመልክቶ አጠቃላይ ጽንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሰፊ የቀርከሃ ሀብት ያላት አገር ብትሆንም በባህላዊ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውል በመሆኑ ተጠቃሚ አልሆነችም።
ባለሥልጣኑ፤ በተለያዩ ወቅቶች ለዩኒቨ ርሲቲ ምሩቃን፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ወደ ዘርፉ መቀላቀል ለሚፈልጉ ሥራ ፈጣሪዎች በልብስ ስፌት፣ በሽመና፣ በብረታብረትና እንጨት ሥራ፣ በቀርከሃ ምርት፣ በሻማ፣ በሳሙና፣ በፕላስቲክና ዘይት ማምረት፣ ሚስማርና አጥር ሽቦ፣ በዳቦና ኩኪስ ዝግጅት በከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጥ ማስዋብ፣ በሶፍትና ናፕኪን ምርት እንዲሁም በቾክ ማምረት ላይ ሙያዊ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር