– በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር 100 ለማድረስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፡- እስካሁን ለተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ 1ነጥብ1 ቢሊዮን ዶላር በሼባ ቦንድ እና በብድር መልክ የተገኘ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ። በ2011 በጀት ዓመት ከፓርኮቹ ምርቶች ወደ ውጭ ተልኮ የተገኘውን 110 ሚሊዮን ዶላር 50 በመቶ የማሳደግ ውጥን መኖሩም ተገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስግዶም በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፤ እስካሁን ለተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዓለም ባንክ 400 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተገኝቷል።
በሼባ ቦንድ መልክ ደግሞ ከአውሮፓ ኅብረት 750 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል። ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ የባህርዳር፣ ቦሌ ለሚ እና ጅማ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መንግሥትም በራሱ በጀት ማስገንባቱን ጠቁመዋል። በቀጣይም ከአውሮፓ እና የእንግሊዝ አገር የፋይናንስ ምንጮች ብሎም የቻይና ባንኮች በተገኘ ገንዘብም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገነቡ ይሆናሉ።
እንደ አቶ አማረ ገለፃ፤ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 100 እንደሚደርሱ የሚጠበቁ ሲሆን በሂደት ደግሞ ከዚህም ሊልቁ ይችላሉ። ለዚህም መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው።
ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት በዘለለም ጎን ለጎን ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል። ለአብነትም በእያንዳንዱ ፓርኮች ከ20ሺ እስከ 50ሺ የሚደርሱ አገር በቀል ዛፎች እንዲተከሉ እየተደረገ ነው።
በተጨማሪም ፓርኮቹ የተጠቀሙትን ውሃ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ፣ ተረፈ ምርቶቻቸው ለሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ለቆዳ ፋብሪካዎችና ለሌላ ተግባር እንዲገለገሉበትና ብክለትን ለመቀነስ ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ሠራተኞችም እንዳይቸገሩ የቤት ግንባታ ሥራዎች አብረው እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከተጀመረ ጥቂት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ለአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኙ መሆኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም በ2011 በጀት ዓመት 110 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ ይህን አሃዝ 50 በመቶ የማሳደግ እቅድ መኖሩን አስገንዝበዋል።
እንደ ወ/ሮ ሌሊሴ ገለፃ፤ እስካሁን የተገነቡት ፓርኮች ከአገራዊ ፋይዳቸው አኳያ በጥናት ላይ ተመስርተው ሲሆን በተለይም ወደ ውጭ መላክን ማዕከል አድርገው የሚገነቡ በመሆኑ ለጅቡቲ ኮርደር የቀረቡ መሆናቸው ታሳቢ ይደረጋል።
በሌላ ጎኑ ደግሞ ኢትዮጵያ እየተወዳደረች ያለው ከአፍሪካና ከዓለም ጋር በመሆኑ ከአዋጭነትና ጠቀሜታው አኳያ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር