አዲስ አበባ፡- የአየርላንድ መንግሥት የምግብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ወገኖች የሚውል የ325 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአየርላንድ መንግሥት ትናንት በገንዘብ ሚኒስትር የ325 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ በተፈራረሙበ ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንደገለጹት፤ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የምግብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ወገኖች ማቋቋሚያ የሚውል ነው። በተለይም በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ያሉ ወገኖች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ይደረግበታል።
ከ1990ዎቹ ጀምሮ ከተለያዩ ለጋሽ አገራት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረው የሴፍቲኔት ፕሮግራም በአራት ክልሎች ሲሰራበት የቆየ ሲሆን አሁን የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2020 ድረስ የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል። ፕሮግራሙ በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ተግባራዊ የሚሆን ነው።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ በተያዘው ዓመት በ382 የተለዩ ወረዳዎች ሰባት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ለመደገፍ ታቅዷል። የተለዩት ወረዳዎች በአፋር፣ አማራ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ ሶማሌ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 15/2012
ዋለልኝ አየለ