የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባካሄደው መዋቅራዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ ተደራድሮና አሳምኖ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ሚናውን የሚወጣ ጠንካራ ዲፕሎማት ለመፍጠር በችሎታቸውና በትምህርት ዝግጅታቸው ጠንካራ ናቸው ለተባሉ ዲፕሎማቶች ሹመት ሰጥቷል፡፡
በጅቡቲ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉሥልጣን አምባሳደር ሆነው ለሁለት ዓመት ከአስር ወር አገልግለው ከአዲሱ ማሻሻያ በኋላ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ተመልሰው የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የሥራ ዘመኑን ጨርሶ ከተመደበበት ሀገር የተመለሰ ዲፕሎማት አንድ ወርና ከዚያ በላይ የዕረፍት ጊዜ እንደነበረውና በአዲሱ አደረጃጀት ግን ይህ መቅረቱን ገልፀዋል፡፡ ለውጡ ከዚህ መጀመሩንም በማመላከት፡፡
‹‹አንድ ዲፕሎማት አበባ ቀስማ ማር በምትሠራ ንብ ይመሰላል፡፡ ንብ ውጤቷ ማር እንደሆነው ሁሉ ዲፕሎማትም ከሚጠበቅበት ውጤታማ ተግባርም አንዱ በኢኮኖሚው ዘርፍ ስኬታማ ሥራ መሥራት ነው፡፡ እንደ ውትድርና ሙያ የዲፕሎማቱ ሥራም በውጤት መለካት አለበት። በአዲሱ አደረጃጀት የተወጠነው የመቶ ቀናት ዕቅድም መሳካት ይኖርበታል›› በማለት የዲፕሎማቱን ተግባር ከውትድርና ሙያ ጋር በማያያዝ አምባሳደር ሻሜቦ ይገልፃሉ፡፡
እንደ አምባሳደር ሻሜቦ ማብራሪያ፣ እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ወዲህ ዓለም ትኩረቱን በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ አድርጓል፡፡ የሁለትዮሽና የአጋርነት ግንኙነት የጠበቀ ቢሆንም፣ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በሀገር ውስጥ የሚደረግ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መደገፍ ይገባል፡፡ ዲፕሎማሲ ሀገርን በኢኮኖሚ የማሳደግ መርህ የተከተለ ነውና፡፡
አምባሳደር ሻሜቦ እንደገለፁት፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በአጋርነት የሚሠሩት እንደ ንግድ ሚኒስቴር ያሉ አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ባለቤት ሆነው ለመሥራት የሚያስችላቸው ተመሳሳይ የአሠራር ማሻሻያ ካላደረጉ ዲፕሎማቱ ብቻውን ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አጋር ተቋማቱ ወጪ ቆጣቢ በሆነ አሠራር ከወደብ ዕቃ በፍጥነት የማንሳትና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡
ማሻሻያው የሰው ሀብት ልማቱ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ዲፕሎማቱ ኃላፊነቱን ለመወጣት እንዲያስችለው የተሟላ ግብዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የግብዓት አለመሟላት፣ ሞራል አለመጠበቅ፣ መብት አለማክበርና የዲፕሎማቱን ቤተሰብ የጉዞ ሰነድ አለማቀላጠፍ እንዲሁም የሰው ኃይል ለሚያስፈልጋቸው ዘርፎች ትኩረት ያለመስጠት ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ይሁንና አሁን አንዳንዶቹ በማሻሻያው መፈታት ጀምረዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሉቲ ዲንና የቢዝነስ መምህር ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ የማሻሻያውን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ትወልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በሚያስችል መልኩ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን ለሀገራቸው እንዲያውሉና ለሀገራቸውም አምባሳደር ሆነው ሥራዎቻቸውን እንዲያግዟቸው ማድረግ ባለመቻላቸው ዲፕሎማቶቹ በተቃራኒው ከትውልደ ኢትዮጵያኑ ተቃውሞ ሲቀርቡባቸው ነበር፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ እንቅስቃሴም ምዕራቡን ያገለለና በውስን አገሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች አዲሱ ማሻሻያ ሊፈታ ይገባል፡፡
በሀገር ውስጥም ሠላምን ለማረጋጋጥና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች አብረው ካልተጠናከሩ የዲፕሎማቱ ጥረት ብቻውን ውጤት ያመጣል ተብሎ መታሰብ እንደሌለበት የሚናገሩት ዶክተር ቀነኒሳ፣ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲና ተያያዥ የሆነ ሥራ የሚሠሩ ሌሎች አካላትን አሠራር አብሮ ማቀላጠፍ ከተቻለ ማሻሻያው ሀገሪቷ እያከናወነች ላለው የድህነት ቅነሳና የኢኮኖሚ ዕድገት ውጤታማነትን ከግብ መድረስ ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ዶክተር አጥላው ዓለሙ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተሻለ ለውጥ መነሳሳቱን በበጎነት ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ማሻሻያ በአብዛኛው ከድክመት የሚነሳ በመሆኑ ከአስፈፃሚ ብቃት ማነስ ወይንም ከአደረጃጀት ነው ብሎ ለይቶ ለተሻለ ውጤት መነሳት ይደገፋል፡፡ ይሁንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለለውጥ ስምንት ዓመት ድረስ መዘግየት አልነበረበትም ሲሉም ይተቻሉ፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያቶች ባከናወነቻቸው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተግባራት የተሳካ ሥራ ሠርታለች ለማለት እንደማያስደፍርና የዲፕሎማት ሹመት ፖለቲካ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበረ ይገልፃሉ፡፡ የዲፕሎማቶቹን ውጤታማነት በየጊዜው እየገመገሙና ክፍተቶችን ለይቶ ችግሮችን እየፈቱ አለመሄድም የጎላ ስኬት ላለመመዝገቡ ከሚጠቀሱ ምክንያቶቹ መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችልም ይናገራሉ፡፡
ፉክክር በበዛበት ዓለም ኢትዮጵያ ተነጥላ ልትቀር አትችልም ያሉት ዶክተር አጥላው፣ በውድድሩ ተፎካካሪ ለመሆን ጠንካራ ዲፕሎማት እንደሚያስፈልጋትና ሌላው ዓለም የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ፣ የንግድ ክህሎትና ለዕድገታቸው የተጠቀሙበትን ዘዴ ወደ ሀገሩ የሚመጣበትን ዘዴ በማመቻቸት እንዲሁም የሌላውን ዓለም አሠራር የማየት አጋጣሚውን ለማያገኘውና የገንዘብ አቅም ለሌለው የሀገር ውስጥ ነጋዴ የዓለምን ሁኔታ እንዲገነዘብ በማድረግ በኩል የዲፕሎማቱ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
ዶክተር አጥላው፣ በዲፕሎማሲ ሥራ አንቱ ለመባል የበቁትን የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ጃፓንን፣ ቻይናን፣ ኮሪያን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት አገራቱ በቴክሎጂና በንግድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት የሌሎችን አገሮች ልምድና ተሞክሮ በመቅሰምና አሠራራቸውን በመቅዳት እንጂ በራሳቸው ፈልስፈው አይደለም፡፡ ዶክተር ቀነኒሳ እንዳሉት በማሻሻያው የተመደቡት ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ስለሚወክሉ መሄድ ያለባቸው ኢትዮጵያን ሆነው ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንለውጣለን ብለውም ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁሉም ቦታ መድረስ ስለማይችሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ይዘው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡
በማሻሻያው መሰረት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ካልተሳካ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ይቀጥላል፣ ሥራ አጥነቱ ይባባሳል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ታጣለች፡፡ ኢንቨስትመንትም ይዳከማል፡፡ ይህ ደግሞ የበለፀገች አገር ለመገንባት የተወጠነው ውጥን እንዲጨነግፍ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
በለምለም መንግሥቱ