የአባይ ወንዝ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ የቤተሰብ ያህል ቅርብ ነው፡፡ በአሉታም ይሁን በአዎንታ፣ በዘፈን ይሁን በለቅሶ የአባይን ሥም በአንደበቱ ያላወደሰ ወይም ያልኮነነ ማግኘት ይቸግራል፡፡ ከትናንት ዛሬ ያለው ልዩነት በስስት የሚያዩት ኢትዮጵያውያን ዓይኖች መበራከትና ከመነሻው ኢትዮጵያ በላይ የእኛነት ስሜት የሚሰማቸውም አካላት ጭንቀት ነው፡፡
በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራው የህዳሴ ግድቡን የግንባታ ደረጃ ለማሳወቅ ሐሙስ ታኅሳስ አራት ቀን 2011 ዓ.ም. ከወትሮው በተለየና ባማረ ቅንጅት መድረክ ተፈጥሯል፡፡ ውይይቱን የመሩት የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሥለሺ በቀለ እና የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ ነበሩ፡፡
በወርሃ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በይፋ ግንባታው የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 80 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት በአምስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር፡፡ ‹‹የፋይናንስ ምንጮቹም የኢትዮጵያ መንግስትና ኢትዮጵያውያን፣ ግንበኛና መሀንዲሶቹም እኛው›› በሚል ሲታወጅ አንዳች የሥሜት ኃይል ከትከሻው ዘልቆ ውርር… ር… ር…ር ያላደረገውና ‹‹እናደርገዋለን!›› ያላለ የሀገሪቱ ዜጋ አልነበረም፡፡ በመድረኩ በተባለው ጊዜ ሳይጠናቀቅ ከመዘግየቱም በተጨማሪ ከተመደበለት አልፎ ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ መፍጀቱ ተነግሯል፡፡
ጉዳዩ የሚገርም ቢሆንም በአገሪቱ የብዙ ፕሮጀክቶች መጓተትና የገንዘብ ምዝበራ ድራማዎች ለንጽጽር ቅርብ ሥለነበሩ ‹‹አጃኢብ›› አልተባለለትም። ይልቁንስ የግደቡ ግንባታ መቼ ይጠናቀቃል? የሚሉ ድምጾች ከየአቅጣጫው ይሰሙ ነበር፡፡ በአወያዮቹ በኩል በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ቢገለጽም፣ ለማጠናቀቅ የሚጠይቀው ተጨማሪ ወጪ ግን ይፋ አልተደረገም፡፡
ዶክተር ኢንጂነር ሥለሺ እንደገለጹት፤ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ አሁን 65 በመቶ አፈጻጸም ላይ ይገኛል፡፡ ከመነሻው 5,250 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ የተጀመረው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በሒደት ወደ 6,450 ሜጋ ዋት ቢያድግም፤ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሥራውን መፈጸም ባለመቻሉ ፍጻሜው እውን መሆን አልቻለም፡፡ አጠቃላይ የግድቡ ሥራዎች በአራት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ የሚሉት ዶክተር ኢንጂነር ሥለሺ፤ የመጀመሪያው የሲቪል ሥራ በዋናነትም የኮንክሪት ሙሊት ሥራ ነው፤ 82 በመቶ ተጠናቋል። ሥራው በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተሰርቷል። ሁለተኛው የብረት፣ ሦስተኛው የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የመጨረሻው የመነጨው ኃይል ወደ ሚፈለገው ክፍል እንዲደርስ የሚደረግበት ሥራ ነው።
ሜቴክ እንዲገነባ የተደረገው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ 25 በመቶ ተጠናቋል። የኃይድሮሊክ የብረት ሥራዎች፤ ማለትም የውኃ ማቀበያ አሸንዳዎች፣ መቆጣጠሪያ በሮች፣ የግድብ ውኃ ማስተንፈሻ በሮች እና ከብረታብረት ጋር የተገናኙ ሌሎች ስራዎች ናቸው። ሥራዎቹ ቢዘገዩም የጥራት መጓደል መኖር አለመኖሩን ማጣራት ያስፈልጋል ሲሉ የግድቡ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል፡፡
መድረኩን የመሩት ኃላፊዎች፤ የግድቡን የቴክኒካዊ ይዘት፣ የሕዝብ ተሳትፎ፣ ኢንቨስት የተደረገበት ገንዘብ መጠን፣ በግድቡ ላይ ከግብፅ ወገን የሚነሱና ሌሎች ውጫዊ ጉዳዮችንም አንስተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱን፣ ‹‹በድፍረት የተገባበት ሥራ ነው›› ብለዋል፡፡ በተለይም በኃይድሮ ስቲል ስትራክቸር መስክና በኤሌክትሮ ሜካኒካል መስክ ተገቢው ልምድና ዕውቀት በሌለው ሜቴክ አማካይነት እንዲሠራ የተላለፈው ውሳኔ ስህተት እንደነበር፣ እርሳቸውም ሆኑ የተቀሩት ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአገር ውስጥ አቅም እንዲሠራ የተላለፈው ውሳኔ በቂ ጥናትና ትንተና አልተደረገበትም›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ 14 ኃይል አመንጪ ተርባይኖችን የማምረቱ ሥራ በዲዛይን ደረጃ ብቻ ተወስኖ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ማብራሪያ ከሆነም፣ ከግድብ ሥራው ጋር የተያያዙ የግድብ ውኃ ማስተንፈሻ ሥራዎች የጥራት ችግሮች አጋጥሟል፡፡ ውኃ ከማስረግ፣ ከቁመት፣ ከወርድና ከዝርመት ጋር የተያያዙ የቅርፅ ወይም የዳይሜንሽን ችግሮችም መሠረታዊ ከሚባሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በብረት መዋቅር ሥራው ወቅት ከብየዳ ጋር የተገናኙ ችግሮች በመኖራቸው በርካታ ፍተሻዎችን ማካሄድ አስፈልጓል፡፡ የተበየዱት መዋቅሮች ያሉባቸውን ችግሮች በላቦራቶሪ ለማስመርመር ናሙናቸው ወደ ውጭ የተላኩ እንዳሉም አብራርተዋል፡፡
አንዱ የህዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጫ ተርባይን 400 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል፡፡ ሁለቱ ተርባይን እስካሁን የውኃ ማቀባበያ አሸንዳ እንደተሠራላቸው ተጠቅሷል፡፡ የአሥራ አራቱ ተርባይኖች ግን ከዲዛይን የዘለለ ሥራ አልተሰራም ተብሏል፡፡ ይሁንና በሜቴክ ሥር ልዩ ልዩ ሥራዎችንና ግንባታዎች በመውሰድ ሲሳተፉ የነበሩ የውል ውል ተቀባዮች ወይም ንዑስ ተቋራጮችን በድርድር በማስገባት እንዲሠሩ እየተደረገ ነው። ከዚህ ቀደም በሜቴክና በሥሩ በነበሩ ኩባንያዎች ሲካሄዱ የነበሩ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲዛወሩ ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሮ ሜካኒካልና በተርባይን አቅርቦት ሥራው ላይ የፈረንሣይ አልስቶም ኩባንያን ጨምሮ የጀርመን ተርባይንና ጄኔሬተር አምራች ቮይት ኩባንያ፣ እንዲሁም የአሜሪካው ጄኔራል ኤሌክትሪክ በህዳሴው ግድብ ሥራ ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡ በተለይም አልስቶም ከአቅርቦት ባሻገር በገጠማ ሥራውም እንዲሳተፍ መወሰኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ከታኅሳስ ወር በኋላ ወደ ግድቡ የግንባታ ቦታ በመሄድ ሥራ እንደሚጀምር አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በማማከርም ጭምር እየተሳተፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ ከሜቴክ ጋር ውል ያላቸውና ድርድር ላይ የነበሩ ኩባንያዎች በዚያው መሠረት እንዲቀጥሉ የተደረገው፣ በአገር ውስጥ የተከናወኑት ሥራዎች ያስከተሉት የጥራት ችግር ብሎም የብረት መዋቅሮቹ ላይ የታየው የስታንዳርድ አለመጠበቅ ጉዳይ ፈታኝ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ብየዳውን ያካሄዱት በሥራው ፈቃድና ዕውቅና ያላቸው አለመሆናቸውም ችግሩን በማባባሱ፣ በርካታ ሥራዎች እንደገና እንዲሠሩ አስገድዷዋል ብለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ በሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች መዘግየቱን ሲያብራሩም፣ አንደኛው ሳሊኒ ከመነሻ እስከ መጨረሻ ያለውን ሥራ አጠናቆ እንዲያስረክብ የተገባው ውል ተሻሽሎ ሜቴክ እንዲገባ በተደረገበት ወቅት፣ ለአንድ ዓመት ያህል ግንባታው ዘግይቷል ብለዋል፡፡ በሲቪል ምህንድስና ሥራው ወቅትም ያልታሰበ ጥልቅ ዋሻ በማጋጠሙ፣ ሥራውን ለሦስት ዓመታት ያለ ክፍያ ለማራዘም እንዳስገደደ ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ባሉበት ሜቴክ በተባለው ጊዜና ጥራት የተሰጡትን ሥራዎች ለማስረከብ አለመቻሉ ተጨማሪ ወጪና ኪሳራ እንዳስከተለ ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም እስካሁን ሳሊኒ ላከናወነው የ82 በመቶ አፈጻጸም 82 በመቶ ክፍያው እንደተፈጸመለት ሲገለጽ፣ ሜቴክ ግን ቅድመ ክፍያን ጨምሮ ለ25 በመቶ ሥራው የ65 በመቶ ክፍያ ተፈጽሞለታል። ይህም የፋይናንስ ሚዛኑን የሚያዛባ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተቋራጮች በተጓተተው ሥራ ምክንያት ላጋጠማቸው ኪሳራ የሚጠይቁት ማካካሻና የግድቡ መዘግየት ያስከተለው ተጨማሪ ወጪ ሁሉ በሒደት እንደሚታይ ተብራርቷል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የህዳሴ ግድቡ በተቀመጠለት ጊዜ አለመጠናቀቁ አገሪቱን ያሳጣት ገቢ በትንሹ አንድ ኪሎ ዋት ኃይል በሰዓት በ0.5 የአሜሪካ ሳንቲም ተሰልቶ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይገመታል፡፡
እንዲህ ያሉ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ቀርቦ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ለመቀዛቀዙ የውጭ ግፊት ነበረበት ወይ? በቀጣይስ በትክክል ሥለመሰራቱ ህዝቡ እንዴት ያምናል? የሚሉትን ጨምሮ ግድቡ በትክክል መቼ ተገንብቶ ሊያልቅ እንደሚችል ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
የግድቡን ግንባታ በሚመለከት ምንም ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነትም ሆነ ተፅዕኖ የለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይልቁንም ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሦስትዮሽ ድርድር ሲካሄድ ቆይቶ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ግድቡ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ በውኃ ይሞላል የሚለው ላይ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት በሚወስድ ጊዜ ውስጥ ግድቡ ውኃ የሚሞላባቸው ዓመታት እንዲሆኑ፣ ይህም ሲደረግ በሦስት መነሻዎች ላይ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የድርቅ ዓመት በሚሆን ጊዜ፣ ጎርፍ በሚኖርበት ዓመትና እንዲሁም መካከለኛ ፍሰት በሚኖር ጊዜ ውኃው በምን ያህል መጠን መለቀቅ እንዳለበት ድርድር መካሄዱን አስረድተዋል፡፡
የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳብራሩት፣ ግድቡ በአራት ዓመታት ውስጥ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2022 ሙሉ በሙሉ ያልቃል፡፡ ከዚህ በፊት በሁለት ዓመታት ውስጥ በቅድመ ማመንጨት የምዕራፍ አንድ ግንባታ 750 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሁለት ተርባይኖች ተተክለው ሥራ ይጀምራሉ ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ለግድቡ ግንባታ ከሕዝብ የተዋጣው ገንዘብ ከ12.3 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን የገለጹት የሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ ሮማን፣ በ2011 ዓ.ም ብቻ እንኳ 347 ሚሊዮን ብር እንደተዋጣም አውስተዋል፡፡ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብም 45.5 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱና እስካሁንም ከሚጠበቀው የ20 በመቶ መዋጮ ውስጥ 15 በመቶ መሰብሰቡን ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ከቀድሞው የግደቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢኒጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሕልፈት፣ እንዲሁም ከሰሞኑ የሜቴክ ሙስና ጉዳይ ጋር በተያያዘ አብዛኛው ሕዝብ ለግድቡ የተዋጣው ገንዘብ ተበልቷል የሚል ሥጋት ውስጥ መግባቱና ተነሳሽነቱ እየቀነሰ መምጣቱም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡
በሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በኩል በተሰበሰበ አስተያየት መሠረት 45 በመቶ የሚሆኑት አሁንም ለግድቡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ፣ 47 በመቶ የሚሆኑት ከእንግዲህ ድጋፍ እንደማይሰጡ፣ ስምንት በመቶ ያህሉም ለጥናቱ ምላሽ ሳይሰጡ መቅረታቸውን ወይዘሮ ሮማን አስታውሰዋል፡፡ ሕዝቡ ተስፋ ቆርጦና ተቆጥቶ እንጂ ፕሮጀክቱን ሳይፈልገው ቀርቶ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሮማን፣ የታዩት ችግሮች ሲፈቱ የሕዝቡ ተነሳሽነት እንደሚመጣና የመዋጮው ሥራም እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ያም ሆነ ይህ ግድቡ የብስራተ ነጋሪቱ ከተጎሰመበት እለት ጀምሮ ዜጎች አቅማቸው በፈቀደው ልክ የላባቸውን ጠብታ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፤አሁን በማበርከት ላይም ናቸው። ግድቡ የዚህ ትውልድ አሻራ የታተመበት የትውልድ ሀብት ነውና የታሪኩ አካል ሆኖ ማለፍ ቀላል ገድል ስላልሆነ አባይ ይጠናቀቃል፤ በጥፋት የተሳተፉ አባያዎችም ይጠየቃሉ የሚለው ሁሉንም ዜጋ ያግባባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
ሙሐመድ ሁሴን