የአሜሪካ ሴኔት ውጭ ግንኙነት ኮሚቴን የሚመሩት የሪፐብሊካንና የዲሞክራቲክ መሪዎች በሳኡዲው ጋዜጠኛ ካሾጊ ግድያ ላይ ሁለተኛ ዙር ምርመራ እንዲደረግ በመጠየቅ ደብዳቤ መላካቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሳኡዲው ጋዜጠኛ ካሾጊ በቱርክ የሳኡዲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ግቢ ውስጥ ከመገደሉ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁኔታ አለም አቀፍ ውግዘት እየደረሰባቸውም የአሜሪካንንና የሳኡዲ አረቢያን ግንኙነት ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ ካሾጊ በኦክቶበር 2 ቀን 2018 ቱርክ በሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ ነው የተገደለው፡፡ በመጀመሪያ ላይ ለሚያገባት ቱርካዊት ሚስቱ የጋብቻ ሰነዱን ለመጨረስ ነበር ከግቢው ውጭ እንድትጠብቀው አድርጎ ወደ ቆንስላ ጽህፈት ሕንጻ የዘለቀው፡፡ የጋብቻ ሰነዱን ለማስጨረስ ግቢ ከገባ በኋለ የቆንስላ ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ ለቆ ወጥቷል በሚል የክህደት ቃል ዓለምን ሲያምታቱ የነበሩት በቱርክ የሳኡዲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ባለስልጣናት ከሳኡዲ አረቢያ በመነሳት የጽህፈት ቤት ግቢ መሽጎ የሚጠባበቅ 18 ክንደ ፈርጣማ አባላት ያሉት ብርቱ የነፍሰ ገዳይ ቡድን አስቀምጠው ነበር የሚጠብቁት፡፡
ካሾጊ አሁን በአልጋ ወራሽነት ስልጣን ይዞ ሳኡዲ አረቢያን እንዳሻው እየዘወራት ያለውን ልኡል መሀመድ ሳልማን በግንባር ቀደምትነት በሰላ ትችት ከሚያጥረገርጉት ውስጥ ቀዳሚው ነበር፡፡ ይሄንን አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ነው የሚለውን ትችት መስማት የማይፈልገው የሳኡዲው ልኡል በካሾጊ ላይ ቂም አርግዞ ጥርስ ነክሶ ለመበቀል ሲያደባ ቆይቷል፡፡
ካሾጊ የጋብቻ ሰነዱን እንደ ዜጋ ከቱርክ ሳኡዲ አረቢያ ኤምባሲ ለመውሰድ ቀጠሮ መያዙን የኤምባሲው መረጃ ክፍል ጄዳ በመደወል ለልኡል ሳልማን መረጃ ካቀበለ በኋላ ግድያው በልኡሉ ትእዛዝ መቀናበሩን ዓለም አቀፍ የደህንነት ተቋማት ዘግበዋል፡፡
ከልኡሉ ፈላጭ ቆራጭ ስልጣን ውጪ ማንም ሰው በአሁኑ ሰአት በሳኡዲ አረቢያ መሬት ትእዛዝ መስጠት የሚችል የለም፡፡ለዚህ ዋቢ ማስረጃው በሀገሪቱ ሪፎርም አካሂዳለሁ በሚል ለስልጣኔ ይቀናቀኑኛል ያላቸውን የሳኡዲ ቢሊየነሮችና የቅርብ ዘመዶቹ የሆኑትን ሼሆች በሙሉ ሰብስቦ እስርቤት ማጎሩ ነው፡፡
ጉዳዩ ሙስና ሳይሆን የፖለቲካ ሴራና ውንጀላ መሆኑ ዛሬ ቀድሞ ከነበረው ጥርጣሬ በላይ ገሀድ እውነት መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ሳኡዲ አረቢያ በድንገተኛ አፈሳ ከታሰሩት ቢሊየነሮች ውስጥ የእኛውም ሼህ መሀመድ አላሙዲን ይገኛሉ፡፡ በታሰሩበት እስርቤት ግርፊያ ድብደባ በልኡሉ ትእዛዝ እንደሚፈጸም ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ልኡል ሳልማን መረን በለቀቀ አምባገነንነት የመፈንጨቱን ጉዳይ በተጨባጭ የሚያረጋግጠው በሴራ ፖለቲካ ውስጥ ተሸፍኖ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ነው ሲሉ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
ይቃወሙኛል በሚላቸው ላይ ከእስር እስከ ግድያ ትእዛዝ እንደሚሰጥ ይህም በኢም ፓየሪቱ ውስጥ ተፈሪ በመሆን ጸጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ያለውን እቅድ አመላካች ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡የካሾጊም ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡የምእራቡ ዓለም የመረጃ ስለላና የደህንነት ተቋማት የዓለማችን እውቅ ስለላ ድርጅቶች የካሾጊ ግድያ በማንና ለምን መቼና የት እንደተካሄደ አነፍንፈው ደርሰውበታል፡፡
የካሾጊን የግድያ ኦፕሬሽን በቅርብ እየተከታተለ የመራው ያስፈጸመው ገዳዮችን ያሰማራው ሂደቱን ሲቆጣጠር የነበረው አንድና አንድ ሰው ብቻ እንደሆነ ከመደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፡፡ ልኡሉና ልኡሉ ብቻ ነው፡፡መሀመድ ቢን ሳልማን ፡፡ትራምፕም የልኡሉ ሚና ምን እንደነበረ ይገለጽልኝ ነው ያሉት፡፡
አሁን አሜሪካን ከሳኡዲ ጋር ያላትን ጥቅም ላለማጣት እያካሄደችው ያለው እሹሩሩ በትራምፕ የሚመራውን የአሜሪካ መንግስት ታላቅ ውርደትና ሀፍረት ላይ እንደሚጥለው ይጠበቃል፡፡ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በካሾጊ ግድያ ሁለተኛ ዙር ምርመራና ማጣራት እንዲደረግ በጽሁፍ ጠይቋል፡፡ይህ አካሄድ ትራምፕ ፈጥነው በሳኡዲ አረቢያ ላይ እርምጃ ካልወሰዱ ውሎ አድሮ ትራምፕን በምክር ቤቱ በሕግ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ ለታላቁ ዓለም አቀፍ የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤና፤ኤፍ.ቢ.አይ ይህ ጉዳይ ተሰውሮ አይደለም፡፡ ለዚህም ይመስላል ትራምፕ ፈራ ተባ እያሉ በካሾጊ ግድያ የልኡል ሳልማን ሚና ተወስኖ እንዲነገራቸው የጠየቁት፡፡ትራምፕ በቢቢሲ ዘገባ መሰረት አድርጎት ይሆናል፣ ላይሆንም ይችላል ባይ ናቸው፡፡
ሳኡዲ አረቢያ በካሾጊ ግድያ ታላቅ ዓለም አቀፍ ውግዘትና ተቃውሞ ደርሶባታል፡፡ በዚህም አያበቃም፡፡ ኢኮኖሚዋን የሚያንኮታኩት ድባቅ የሚመታ እቀባም ያሰጋታል፡፡ዓለም በካሾጊ ግድያ ከልኡሉና ከንጉሳዊ ቤተሰቡ አልወረደም፡፡ ጀርመን የበኩሏን እርምጃ ወስዳለች፡፡ሌላውም ይቀጥላል፡፡
በርካታ ሀገራት ከነፍሰ ገዳይ መሪዎች ጋር አንተባበርም በሚል መርህ ከሳኡዲ አረቢያ ጋር የነበራቸውን ዲፕሎማቲክና የንግድ ግንኙነት ሊያቋርጡ ይችላሉ፡፡እነዚህን ሁሉ እርምጃዎች ለመውሰድ ተጠንተው በጠረጴዛ ላይ ተሰድረው የተቀመጡ ናቸው፡፡አስፈላጊ በሆነ ሰአት ይመዘዛሉ፡፡
ሳኡዲ አረቢያ በግድያው ላይ የልኡሉን ሚና ይፋ ካላደረገች በታሪኳ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ፈተና ውስጥ ትወድቃለች፡፡ የማታውቀውን ኪሳራና ቀውስ ታስተናግዳለች፡፡
ሳኡዲ አረቢያ ሌላም ክስ አለባት፤ ለአሸባሪዎች ከኋላ ሆና የምታሸክማቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠር የእርዳታ ገንዘብ መሳሪያ እንዲገዙ እንዲታጠቁ እንዲዘምቱ የሚያሰማሩት ሁሉ የሳኡዲ ቱጃሮችና የሌሎችም አረብ ሀገራት ቱጃሮች ናቸው፡፡ የአሜሪካም ሆነ የእንግሊዝ የስለላ ተቋማት ይሄን ጉድ በዝርዝር ያውቁታል፡፡ እንዲያውም ቢቢሲ በአንድ ወቅት ሰፊ ዶክመንተሪ ሰርቶበት ነበር፡፡
የዓለም ሰላም የስጋት ምንጭ ለሆነው አሸባሪነት ደጋፊዎቹ ረዳቶቹ አጉራሾቹ እነሱና ሌሎችም ናቸው፡፡ አረመኔዎቹ የሳኡዲ አራጆች ካሾጊን በአንድ ክፍል ውስጥ እንደ ከብት አርደው በልተውታል፡፡ቆራርጠው ከታትፈው በግቢው ውስጥ በሚገኝ የአትክልት ስፍራ ቀብረውታል የሚሉ መረጃዎችም ወጥተው ነበር፡፡ በቅርቡ በወጣው የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት ካሾጊን ከገደሉት በኋላ ቆራርጠው አካሉን በቦርሳ ውስጥ በማድረግ የማይፈተሸውን የዲፕሎማቲክ መብታቸውን ተጠቅመው በአውሮፕላን ተሳፍረው ከቱርክ ወጥተዋል፡፡ የተለያዩ መላምቶች ይሰማሉ፡፡ ፈጭተው ዘይት አድርገውታል ከሚለው ጀምሮ ባሕር ጥለውታል፤ አቃጥለውታል፤ በረሀ ላይ ወርውረው ታል የሚሉ የተለያየ ግምቶች ይደመጣሉ፡፡ ከውጭ ሆና ካሾጊ ጉዳዩን ጨርሶ እስኪወጣ ትጠብቀው የነበረችው እጮኛው በዛው የውሃ ሽታ ሆኖ ሲቀር ደመ ነፍስዋ እንደገደሉት ጠርጥሯል፡፡
የቱርክ ደህንነት የመረጃ ክትትል ሰራተኞች በውስጥ ወኪላቸውና በስለላ ካሜራዎቻቸው የካሾጊን በቆንስላ ጽህፈት ቤት ግቢ ውስጥ መገደል ወዲያው ነው የደረሱበት፡፡ ሳኡዲ ብትክድም ሳትወድ በግድ እውነቱን በግፍና በአረመኔነት መገደሉን አምናለች፡፡በገዳይነት የተጠረጠሩ ያለቻቸውን 11 ሰዎች ስታስር በአምስቱ ላይ የሞት ፍርድ በይናለች፡፡የሳኡዲ ንጉሳዊ ቤተሰብ በካሾጊ ግድያ ውስጥ የለበትም ብላለች-ሳኡዲ አረቢያ፡፡ዓለም ደግሞ የገደላችሁት ያስገደላችሁት እናንተ ናችሁ ከእናንት ራስ አንወርድም እያለ ነው፡፡ለዚህም ከበቂ በላይ ማስረጃ አለው፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማክሰኞ እለት በሰጡት መግለጫ፤ የሳኡዲው ልኡል በካሾጊ ላይ ስለተካሄደው ዘግናኝ ግድያ በሚገባ እንደሚያውቁ አምነዋል፡፡በማከልም አድርጎታል ወይንም አላደረገውም ሊሆን ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በኋላ ላይ ሲ.አይ.ኤ ሙሉ በሙሉ 100 ፐርሰንት ግድያውን አልወሰነም ብለዋል፡፡ለሁሉም የካሾጊ የግድያ ሁኔታ የአካሉ መሰወር ዛሬም የዓለማችን አቢይ የመነጋገሪያ ርዕስ በመሆን ቀጥሏል፡፡
የፕሬዚዳንቱን አስተያየት ተከትሎ የሪፐብሊካኑ ሴኔተር ቦብ ኮርከር የዲሞክራቱ ሴኔተር ቦብ ሜንዴዝ በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ስም መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በዚህም መግለጫ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተለይም በልኡሉ ላይ ሁለተኛ ዙር ምርመራ እንዲደረግ በዚህም የውጭ ተወላጅ የሆነ ሰው ለግድያው፣ለግርፊያና ድብደባው፣ ግዙፍ ለሆኑ ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ኃላፊነቱን ይወስድ እንደሆነም ለመወሰን የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወንድወሰን መኮንን