በአማራ ክልል አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት ሲገኝ ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታሩ በመስኖ መልማት የሚችል ነው። ይሁን እንጂ፤ እስካሁን የለማው ሁለት መቶ ሺህ አስራ ዘጠኝ ሄክታር ብቻ ነው። ይህም በመሆኑ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል መሬት ጾም እያደረ ነው። ባለፉት ዓመታት በክልሉ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት የተሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም ከመሬት አቅርቦትና ተያያዠ የግብዓት ችግሮች ጋር በተገናኘ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ሳይቻል ቆይቷል። በመሆኑም በዘንድሮው ዓመት ክልሉ የነበሩትን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ከ82 ሺህ በላይ ዜጎችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ወደተግባር እየገባ ይገኛል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድሙ እንደሚያብራሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመስኖ በማልማት የፍራፍሬና የቡና ችግኝ በማዘጋጀት ሥራ በማሳተፍ 59 ሺህ 759 ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ነበር። ነገር ግን፤ ማከናወን የተቻለው የእቅዱን ሰላሳ በመቶ አስራ ሶስት ሺ841 ወጣቶችን ብቻ ነው። አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሆነበት ቀዳሚው ምክንያት ደግሞ የመሬት አቅርቦትና የገንዘብ እጥረት በመግጠሙ ነበር።
በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ከ82 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ያሉት ዳይሬክተሩ በመሬት አቅርቦትና በገንዘብ በኩል የሚገጥሙትን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሰሩ ያሉትን ሥራዎች እንደሚከተለው ገልጸዋል። በመስኖ የሚለማውን መሬት እጥረት ለመቅረፍ ከክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ ጋር በተደረገ ውይይት ለመስኖ የሚስማማ በቂ መሬት ለማቅረብ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ የመለየት ሥራም ተሰርቷል። በገንዘብ አቅርቦት በኩል ያለውንም ክፍተት ለመሙላት ዘንድሮ አዲስ አሰራር ተዘርግቷል።
ከዚህ ቀደም በነበረው የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት አምራቾቹ ችግኝ ሲሸጡ ብሩ ወደ መንግሥት ካዝና ይገባ ስለነበር እያዟዟሩ በመጠቀም ከሚያገኙት ትርፍ ውጭ ጥሪት ለማፍራት የሚችሉበት እድል አልነበራቸውም። ዘንድሮ ግን በዓመቱ መጨረሻ የተሰጣቸው ገንዘብ ተመላሽ መሆኑ ባይቀርም በጀት እንዳያጥራቸው ራሳቸው እያዘዋወሩ እንዲጠቀሙበት ይፈቀድላቸዋል። በበጀት ረገድ እስካሁን በየዓመቱ ከሀምሳ ሚሊዮን ብር በላይ ሲመደብ የነበረ ሲሆን፤ ዘርፉ በሌሎች ፕሮጀክቶችም ሲደጎም ቆይቷል። የዘንድሮው ዓመት በጀትም በቅርቡ የሚጸድቅ ሲሆን የተያዘውን እቅድ ለማስፈጸም የሚበቃ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በመስኖ ልማቱ ከሚሳተፉት 80 በመቶ ቋሚ 20 በመቶ ደግሞ በጊዜዊነት መሬት በመከራየት የሚሰሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። አርባ አራት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ከ200 እስከ 300 ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ። በትልልቅ ከተሞችም በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ ዛሬም ድረስ በርካታ መሬቶች ጦም እያደሩ ነው። እነዚህንም ለመጠቀም እስከ 700 ሺህ ችግኝ በማዘጋጀት በከተሞቹ ዙሪያ በክፍት ቦታዎችና በመኖሪያ ቤት የከተማ ግብርናና ለማጠናከር ባለሙያ በመመደብ እየተሰራ ይገኛል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች በቤታቸውና አካባቢያቸው እንዳሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። ለቀጣይ ዓመትም በግንባታ ላይ የሚገኙት ግድቦች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ የሚቀርበውም የመሬት መጠን ሆነ የተጠቃሚው ቁጥር ይጨምራል።
በሰለጠነ የሰው ኃይል በኩል ያለውንም ክፍተት ለመሙላት በክልሉ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ጋር የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በተጨማሪም፤ ተጠሪነቱ ለግብርና ቢሮው ሆኖ ወጣቶችንና በሰርተፍኬት ደረጃ የሚያስተምር ማሰልጠኛ ማእከል ለማሰራት የማቋቋሚያ አዋጅ ተዘጋጅቷል። በገበያ ትስስር ረገድም ወቅት የጠበቁ ገበያዎች በመፍጠር አምራቹ ለኪሳራ ሳይዳረግ የሚገባውን እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ ወይዘሮ ጸዳለ ዮሀንስ በበኩላቸው፤ በዞኑ የመስኖ ቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ይናገራሉ። ቡድን መሪዋ እንደሚያብራሩት እስካሁን አምስት ሺህ 724 አርሶ አደሮች ተደራጅተው በዞኑ ላሉት ሃያ አንድ ወረዳዎች የሚከፋፈል 24 ሺህ 441 የአትክልት ችግኝ አዘጋጅተው አቅርበዋል። በተጨማሪም፤ ለበጀት ዓመቱ 277 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማቅረብ በእቅድ የተያዘ ሲሆን እስካሁን 70 ሺው ተዘጋጅቶ ቀርቧል።
በአጠቃላይ፤ በዞኑ 21 ሺህ 834 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ሺህ 600 ሄክታር እንደ አዲስ ይጨመራል። እስካሁን በተለያየ ደረጃ 127 ሺህ 389 አርሶ አደሮች የመስኖ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ጸዳለ፤ በዘንድሮው ዓመት 10 ሺህ 272 ወንዶችንና አንድ ሺህ 354 ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥም በፍራፍሬና ቡና፤ በመስኖ ሰብልና በጓሮ አትክልት 4613 የሚሆኑ ሥራ አጥ የነበሩ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የምእራብ ጎጃም ዞን አትክልትና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ታመነ ፍቅሬ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ በአዝርዕት፤ ቅመማ ቅመም፤ አትክልትና ጥራጥሬ የመስኖ ልማት 3 ሺህ 902 ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የሥራ እድል የሚፈጠር መሆኑን ይናገራሉ። የዘንድሮው የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ እስካሁን በመስኖ ሲጠቀም የነበረውን 201 ሺህ 230 አርሶ አደር ቁጥር ወደ 205 ሺህ 132 እንደሚያደርሰው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በዞኑ 37 ሺህ 240 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ አንድ ሺህ 253 ሄክታሩ አዲስ መሆኑን ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
በግብአት አቅርቦት ረገድም ለበጀት ዓመቱ 49 ሺህ 556 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በእቅድ የተያዘ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ከመኸር ተርፎ በየወረዳው የተቀመጠው ጥቅም ላይ ይውላል። የምርጥ ዘር አቅርቦት አዝርዕት 1227፤ አትክልት 394፤ የስራስር ተክሎች ሦስት ሺህ 350 በኩንታል ለመጠቀም እቅድ ተይዟል። በዘር አቅርቦት ረገድ ሽንኩርትና በቆሎ የተሻሻለ ዘር እጥረት፤ እንዲሁም የውሃ ፓንፕ አቅርቦት ክፍያ ክፍተት በመኖሩ ይህንን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ዘጠኝ ሺህ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የተጀመረ ሥራ መኖሩን በመጠቆምም ወደ ተግባር ሲገባ የመሬት አቅርቦት ችግር ይገጥማል ተብሎ በመሰጋቱ ችግሩን ለመቅረፍ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ በቂ የሰለጠነ የመስኖ ባለሙያ ባይኖርም የሰብል ልማት ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ