የስፓኒሽ ፋሽን ብራንድ አምራች ኩባንያ ሴፒያ እጅግ የመጨረሻ ደረጃ ያለውን የወንዶች ምርጥ ሸሚዝ 3.0 የተባለውን አምርቶ ማስተዋወቁን ገለፀ፡፡ ይህ በአይነቱ የተለየ ሸሚዝ መድኃኒትነት ያለው መሆኑን የስፑኪ ካታጎሪ ዜና ዘግቧል፡፡
በአለማችን በተለይ ባደጉትና በኢኮኖሚ በበለጸጉት ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የፋሽንና የዲዛይን ስራ ውድድሮችና ፉክክሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትና ምጥቀቱ ለዚሁ ውድድር ታላቅ በር ከፍቷል። በርካታ የፈጠራ ስራዎችም ይካሄዳሉ። ካምፓኒዎች ከኩባንያዎች ጋር የበላይነትን ለመቀዳጀት ብርቱ ትንቅንቅ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡
ከሰሞኑ ከወደ ስፔን የተሰማው ዜና የአለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ሴፒያ የልብስ ፋሽንና ዲዛይን አምራች ኩባንያ በስፔን ውስጥ በጣም ታዋቂ ነው፡፡ ለአመታት ጥራታቸውን የጠበቁ ምርጥ ልብሶችን ሲያመርት ኖሯል፡፡ አሁን አምርቶ ለገበያ ያቀረበው ‹የደህንነት ሸሚዝ 3.0› በሚል የሰየመው ልብስ በአይነቱና በጥራቱ እንዲሁም በያዛቸው የተለያዩ ድብልቅ ውህዶች ( ንጥረ ነገሮች) ለጤና ተስማሚና ተመራጭ ሸሚዝ መሆኑን ኩባንያው ይገልጻል፡፡ የስፔኑ ሴፒያ ካምፓኒ አሁን ላይ ያመረተው ሸሚዝ 3.0 በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ቀደም በሸሚዝ ወይንም ልብስ አምራች ካምፓኒዎች ይህን አይነቱ ልብስም መድኃኒትነት ባለው መልኩ ስለመመረቱ የሚገልጹ መረጃዎች የሉም፡፡
በአይነቱና በጥራቱ የተለየው ይህ ሸሚዝ የለባሹን የጤና ደህንነትና ምቾት በአስተማማኝ ደረጃ ከመጠበቁም በላይ ጭንቀት ይቀንሳል፤ የደም ፍሰትን ያስተካክላል፤ የጉልበት (ኃይል) መጠንን ይጨምራል ይላል የስፑኪ ካታጎሪ ዜና።
የሴፒያ ካምፓኒ የመጀመሪያው ትውልድ የልብስ ምርቶች የሚላቸው በተለይ ሸሚዞች በአንገት አካባቢ የሚፈጠሩ የተለያዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባና ትንሽ እጥበት ብቻ የሚጠይቅ ነበር፡፡ የሴፒያ ኩባንያ የሁለተኛው ትውልድ የፋሽን ዲዛይንና የልብስ ምርቶች ደግሞ የበለጠ ለመተንፈሻ ስርአት የተመቹ ሆነው ብዙ የላብ ፈሳሽና ሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ናቸው፡፡
በልብስ ዲዛይን ስራ በየዘመኑ እየተጠበበ የመጣው ካምፓኒው አሁን ላይ ደግሞ ለዘመኑ ትውልድ የሚመጥን ያለውን የፋሽን ዲዛይንና አዲስ የሸሚዝ ምርት 3.0 የተባለውን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ እኛ ይህ ሸሚዝ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ስለሆነ ልብስም መድኃኒትም ነው ብለነዋል፡፡
ምርጥ ልብሶችን አስመልክቶ ካምፓኒው ይሄንኑ አዲስ የሸሚዝ ምርት 3.0 የተባለውን የደህንነት ሸሚዝ ብሎታል፡፡ የጤና ደህንነትን የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡ በዚህም ሴፒያ ካምፓኒ የደህንነት ሸሚዝ የሚል መለያ ሰጥቶታል፡፡በዚህ ዘመነኛ አዲስ ምርት ውስጥ ቀደም ሲል የነበሩት የአንደኛውና የሁለተኛው ትውልድ ምርቶች የነበራቸውን የተለየ ባህርያት ጨምሮ ባዮ ሴራሚክና ናኖ ፓርቲክልስ የተባሉ የለባሹን ደህንነት የሚጠብቁ ውህዶች ተካተውበታል፡፡
በሴፒያ ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት ባዮ ሴራሚክና ናኖፓርቲክልስ የተባሉት በልብሱ ውስጥ የሚገኙት ንጥረ ነገሮች በርቀት ያሉ በጸሀይ ብርሀን የሚለቀቁ ጨረሮችን (ፋር ኢንፍራሬድ ሬይስን ) መልሰው በማዘጋጀት ከነዚህ ጨረሮች የሚመነጨው ሙቀት የለባሹን ቆዳ ዘልቆ በመግባት ጡንቻዎቹን፤ መጋጠሚያዎችንና የደም ቧንቧዎችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ይህም የሚሆነው ቫሶሊዴሽንን በመርጨት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የኑትሪን ንጥር ነገሮች፣ ኦክስጅን፤ ነጭ የደም ሴሎች እንዲሁም የጸረ ሰውነት መከላከያ ለቆዳው እንዲደርሰው ያደርጋል፡፡ ሌሎች ካታቦላይት የሚባሉትን ለሰውነት የማያስፈልጉ ንጥሮች ከቆዳው ላይ እንዲወገድ ያደርጋል፡፡
በልብሱ ውስጥ ያለው የባዮ ሴራሚክ ቁስ ዩቪ–ኤ እና ዩቪ-ቢ የተባሉትን ከፍተኛ ጨረሮች መጦ በማስቀረት የለባሹን ቆዳ ከመጠቃት ይከላከላል፡፡ የጸሀይ ጨረርን በማንጸባረቅ የተመጣጠነ ሙቀት በመስጠት ለባሹን እንዲረጋጋና ምቾት እንዲሰማው ያደርጋል፡፡
የሴፒያ ካምፓኒ የመጨረሻው ምርጥ ሸሚዝ 3.0 የተጠቃሚውን የደም ዝውውር ያስተካክላል፡፡ ቆዳውን በመጠበቅ በመገጣ ጠሚያችን አጥንቶች ውስጥ ሕመም የሚፈጥርው ዩሪክ አሲድ እንዳይገነባ ያደርጋል፡፡እነዚህ ሁሉ ባሕርያት ተቀላቅለው ጭንቀትን ድካምን በመቀነስ በከፍተኛ ደረጃ የለባሹን ምቾት ይጠብቃሉ፡፡
የጀመርነው ምቹነት ባላቸው ልብሶች ነው፡፡ አሁን ግን ግባችን ፋሽን ላይ ሆኖ የሰውን ጤንነት የሚጠብቅ ምርት ላይ እንሰራለን፡፡ይህም ጤንነት በዘለቄታ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው ሲል የሴፒያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፌድሪኮ ሳየንዝ ከስፓኒሽ ኒውስ ኤጀንሲ ኢኢኤፍ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጿል፡፡
አትሌቶች የካምፓኒው ምርት የሆኑትን ባዮሴራሚክ ናኖሴራሚክ ፓርቲክሎችን ብቃታ ቸውን ለማሻሻል ሲሉ በመግዛት በጫማዎ ቻቸው ውስጥ መጠቀም ጀምረዋል ሲል ዘገባው ይገልጻል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2012
ወንድወሰን መኮንን