በትልልቅ አገርአቀፍ፣ አህጉርአቀፍና አለምአቀፍ የፎቶ ግራፍ አውደርዕዮች ላይ ተሳትፏል።መንግስታዊ ካልሆኑ አህጉርአቀፍና አለምአቀፍ ድርጅቶች ጋርም ሰርቷል።በአለምአቀፍ መጽሔትና ጋዜጦች ላይም የፎቶ ግራፍ ጥበቦቹ በተከታታይ ያቀረበ ባለሙያ ነው።ይህ ስራው ምርጡ የአፍሪካ የፎቶግራፍ ባለሙያ በሚል በአንደኝነት ተሸላሚ ለመሆን አስችሎታል።በአገር ደረጃም የበጎ ሰው የሽልማት ድርጅት በፎቶግራፍ ዘርፍ የ2011 ዓ.ም ሽልማትን አበርክቶለታል።የዛሬው የ”ህይወት እንዲህ ናት” አምዳችን እንግዳ ያደረግናቸው ሰዓሊና የፎቶ ግራፍ ባለሙያው ሚካኤል ፀጋዬ ናቸው።ከእሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አዘጋጅተነዋል።
ማጂክ
በ1969 ዓ.ም ነበር ከአንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ከሚኖሩ ወላጆች ቤት እልልታ ተደመጠ።እልልታው ወንድ ልጅ መወለዱን ማብሰሪያ ነው። ሰፈሬው በእልልታው ተገርሞ ደስታውን ለመካፈል ወደ ትልቁ ቤት አመራ።ለታደሙት ገንፎ ተገንፎቶ ተበላ። ህጻኑ ይደግ ምርቃቱም ተደረገ። ይሄ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ባህል ስለሆነ ‹‹ እንኳን ማርያም ማረችሽ ብሎ ገብቶ ማርያም በሽልም ታውጣሽ›› በማለት መርቆ ወደቤቱ አመራ።ደስታው የወንድና የበኩር ልጅ የሆነላቸው ቤተሰብም ልጃቸውን እያሽሞነሞኑ ለቁምነገር እንዲበቃላቸው ይታትሩም ጀመር።ያሰቡት ተሳክቶ፣ የተመኙት ደርሶ የጓዳው እልልታ እና ምርቃት በአደባባይ አቁሞታል። በአገሩ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ጭምር ተዋቂነትንም አስገኝቶለታል።
ትምህርት ቤት እስኪገባ ድረስ መጠሪያ ስሙን ሰለሞን ያደረገው የዛሬው ሚካኤል፤ ቤተሰቦቹ ሚካኤልን አጠብቀው ስለሚወዱና ስለሚዘክሩ ስሙን እንደሰጡት ይናገራል።ሚካኤል ከልጆች ጋር የሚጫወተው ትምህርት ቤት ሲሄድ ብቻ ነው።ያውም ብዙ ችግር ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮች ላይ መሳተፍ አይወድም።በተለይ የቡድን ጨዋታ ላይ በፍጹም መሳተፍ እንደማይፈልገ ይናገራል። ምክንያቱ ደግሞ “እኔም እነሱን ማናደድ አልፈልግም። በእነርሱም እኔ መበሳጨትን አልወድም “ የሚል ነው።ብዙ ጊዜ በሁለት ሰዎች የሚጫወቱ ጨዋታዎችን ይመርጣል።በቤት ውስጥም ብዙ ጊዜ ከራሱ ጋር ማውራት የሚችልባቸውን ጨዋታዎች ያዘወትራል።
ሚካኤል ከቴነስ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ብዙ የሚያስታውሳቸው ነገሮች አሉት።ጨዋታውን ቢወደውም ካለመቻሉ ጋር የወጣለት ቅጽል ስም ደግሞ በይበልጥ ጨዋታውን እንዳይረሳው አድርጎታል።ማጅክ ቦንሰን በቴንስ ተጨዋችነቱ የሚታወቅ ሰው ነበር።እናም ሚካኤልን ጓደኞቹ ሲተርቡት ‹‹ማጂክ›› እያሉ ይጠሩት ነበር።
ሚካኤል ገና በልጅነቱ ነበር ዛሬ የደረሰበትን የስዕል ሙያ ያለመው።ደብተሮቹ ሁሉ በስዕሎች የተሞሉት ልጅ እያለም ነበር።ትምህርት ቤቱ ደግሞ ይህንን ችሎታውን የሚያዳብርበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ሙያውን ይበልጥ እንዲወደው አድርጎታል።ከመደበኛ ትምህርት ባሻገር በትምህርት ቤት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በስዕል ያስቀምጣል።ቀለም በመቀባትም እንዲሁ ይሳተፋል።
የሚካኤል አባት የባንክ ሰራተኛ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ በሽያጭ ባለሙያነት በተለያየ ቦታ ሰርተዋል። የትምህርትን ጣዕም በሚገባ የሚያውቁት ቤተሰቦቹ ትምህርት ለማይወደው ልጃቸው ፈተና ሆነውበታል።በጣምም ይናደድባቸው እንደነበር ይናገራል።ምክንያቱም ወንድሞቹ የሚያነቡት ፈልገው ነው።እርሱ ደግሞ ማንበብን ፈጽሞ አይወድም።ስለሆነም ፍላጎቴን አይጠብቁልኝም በማለት ይበሳጭባቸዋል።ያም ሆኖ ግን ስለሚወዱትና የመጀመሪያ ልጅም ስለሆነ የፈለገውን ነገር ያሟሉለታል።
እንደአብዛኛው የአዲስ አበባ ልጆች ከቤት ሳይወጣ ያደገው ሚካኤል፤ በቤት ውስጥ የፈለገው ነገር ይሟላለታል እንጂ ወጥቶ እንዲጫወት እድል አይሰጠውም።እናም በቤት የሚያዘወትረው ቴነስ በመሆኑ የልጅነት ፍላጎቱም ተዋቂ የቴነስ ተጫዋች ካልተሳካለት ደግሞ ጥሩ ሰዓሊ መሆን ይፈልግ እንደነበር አጫውቶናል።
ትምህርት
በትምህርቱ መካከለኛ የሚባል ተማሪ ቢሆንም ማጥናት ከማይወዱት ተርታራሱን ያስቀምጣል።የቤት ስራ መስራትም አይወድም።እንደውም አንድ ጊዜ በዚህ ስራው ትምህርት ቤት እንደተገረፈ ይናገራል።ታናናሾቹ ሲያጠኑ እርሱ በዚህ ደረጃ መጓዙ የሚያሳስባቸው ቤተሰቦቹ ብዙ ጊዜ ይገስጹታል።ግን አይሰማቸውም።ያም ሆኖ ግን ብዙዎች ማምጣት የማይችሉትን የ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና ውጤት አምጥቶ ነበር ዩኒቨርስቲ የገባው።
በካቴድራል ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርቱን “ ሀ” ብሎ የጀመረው ሚካኤል፤ በዚሁ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ዘልቋል።ከዚያ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ተዛወረ።እስከ 12ተኛ ክፍልም በዚሁ ትምህርት ቤት ተከታተለ።ይህ የትምህርት ደረጃ ሲጠናቀቅ ደግሞ በቀጥታ ያመራው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው።የኢኮኖሚክስ ትምህርትን ምርጫው አድርጎ ለሦስት ዓመት በዚያው ቢቆይም ማጠናቀቅ ግን አልቻለም።ምክንያቱም ሚካኤል በዚህ ዘርፍ ብዙም መማርና መቀጠል አልፈለገም።የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት እንደመጣለት ሲያውቅ በሁለት ምክንያት ዩኒቨርስቲውን ለመቀላቀል ወደደ።
የመጀመሪያው ቤተሰብ ለማስደሰት፤ ሁለተኛው ደግም ከጓደኞቹ ላለመለያየት ዩኒቨርስቲ እንደገባ ይገልጻል። ቆይታው ምርጥ የሚባሉ ጓደኞችን እንዳፈራና ከቤት ውጪ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያይበት ስላደረገው ወዶታል። ሆኖም ጊዜውን ያላግባብ እንዳቃጠለ ይናገራል።ከዚህ በላይ ጊዜዬ መቃጠል የለበትም በሚል የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ ለዛሬ ተዋቂነት የሚያበቃውን ትምህርት ለመማር ወደ ስዕል ትምህርት ቤት የገባው።
በስዕል ትምህርት ቤት የልጅነት ህልሙን እውን ለማድረግ ዓመታትን በትምህርት አሳለፈ።ዲፕሎማውን ይዞ ወደ ሥራ ተሰማራ።ከዚያ በላይ ትምህርቱን በከፍተኛ ደረጃ ባይቀጥልም የተለያዩ አገራት በመዘዋወር ስልጠናዎችን በመውሰድ አዳብሯል።በየእለት ስራዎቹም እንዲሁ የእውቀት አድማሱን ያሰፋል።
የጥበብ ጥሪ
ከስዕል ትምህርት ምረቃ በኋላ በቀጥታ ወደ ቅጥር አልገባም።ይልቁንም ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና የገቢ ምንጩን ለማስፋት በእናቱ ቤት ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነች ስቲዲዮ ሰርቶ ቡርሹን ከወረቀት ጋር ማገናኘት ጀመረ።በኤግዚቢሽኖች ላይም በመሳተፍ ሥራዎቹ ምን ያህል ድንቅ እንደሆኑ አሳየ።ይህ ደግሞ ለሌላ ሥራ የሚጋብዘውን አማራጭ አስገኘለት።ይኸውም ሀሳብ ፍለጋ በጀርመን ባህል ማዕከል ቤተመጽሐፍት( ጎይቴ) ለመጠቀም ሲሄድ የገጠመው ሲሆን፤ በቦታው የአንድ ሳምንት ወርክ ሾፕ ይሰጥ ነበር።እናም ሚካኤል ቤተመጽሐፍቱ ውስጥ ሳይዘልቅ ድንገት ተጠለፈ።አሰልጣኙ ‹‹የት ነው የምትገባው ወደ ክላስ ግባ እንጂ›› ሲል ለስልጠና ባለሰበው ምክንያት ጋበዘው።ከገባ በኋላ ግን ስልጠናውን በእጅጉ ወደደው።
ጥበብ ሲጠራ እንዲህ ነው የሚያስብል ከስልጠናው አገኘበት።ምክንያቱም ከገባ በኋላ የሚሰጠው ስልጠና ከሚያስበው በላይ የሚያስደስት ነበር።በዚህም አንድም ቀን ሳይቀር ስልጠናውን አጠናቀቀ።ከስቲዲዮ ወጥቶ ከሰዎች ጋር በመሆን መስረትን ይጠይቃልና ብዙ አቅምም ቸረው።ሰዎችንም አስተዋውቆታል፤ ከአሰልጣኙ ጋርም በጣም እንዲግባቡና የራሱን ካሜራ ሳይቀር እየሰጠው እንዲሰራ ረድቶታል።ከዚያ ተሻግሮም ሌሎች በስራዎቹ የሚረዱት ፎቶ ቤቶችም እንዲፈጠሩ ያገዘው በዚህ ስልጠና በመሳተፉ ነው።እናም ይህንን ስልጠና ‹‹ዓይኔን የገለጠልኝ ስልጠና ነው›› ይለዋል።
ሚካኤል ሁኔታዎች ያሰበበት ጫፍ ላይ አላደረሱትምና ሌላ አድማስ ፍለጋ መሮጥ እንዳለበት ማሰብም የጀመረው ይህንን አጋጣሚ ካየ በኋላ ነበር።እናም ሌላ ዕድሉን ፣ ሌላ ዕጣ ፋንታውን ተቀብሎ ፎቶ ግራፈርነትን እንጀራው እያደረገው መጣ።በሚያልመው የዋና ገንዳ ውስጥም ገብቶ በሙያው ማማ ላይ ለመድረስ ይሰራል።‹‹እኔ በሁሉ ነገር መልካም ሰው እንዲያጋጥመኝ የሚያደርግ እድል ተሰጥቶኛል።ብዙዎች የሚቸገሩበትን ካሜራ፣ ፎቶ ፕሪንተርና ቀለም ሳይቀር ከተለያዩ አካላት ድጎማ እየተደረገልኝ እንድሰለጥንም የሆነው ለዚህ ነው።እንጀራዬም ቢሆን በፎቶግራፉ ዘርፍ እንዲሆን ያገዘኝ ድንገት ተጠርቼ ነው ።›› የሚለው እንግዳችን፤ በተለይ የጀርመን ባህል ማዕከል በብዙ ነገር እንደረዳው ይናገራል።ከስድስት ወር በኋላ በፎቶ ኤግዚቢሽን ሳይቀር ተሳትፎ ብር እስከመከፈል እንዳደረሰውና እርሱም በኤግዚቢሽኑ ተዋቂነትን እንዳገኘ አጫውቶኛል።
የሥራ ጅማሮ
በጀርመን ተራድኦ ድርጅት(ጂቲዜድ) በአሁኑ (ጂ አይ ዜድ) አማካኝነት ስራን ‹‹ሀ›› ብሎ የጀመረው እንግዳችን፤ ሁለት ሜትር በሶስት ሜትር የሚሆኑ የወረቀት ላይ ማስታወቂያዎችን በመስራትም ነበር ሥራን የተለማመደው።ለዚህ የበቃው ደግሞ በወቅቱ ህትመት አለመኖሩ ነበር።እርሱም እነዚህን ትልልቅ የማስታወቂያ ቢል ቦርዶች በፎቶ እያነሳ ያስቀርና ይሰራ ነበር።ቀጥሎ የሰራበት ድርጅት አይ. ኤም.ኤፍ የተባለ የስደተኞች መርጃ ድርጅት ውስጥ ሲሆን፤ በስዕል ትምህርት ቤት አብራው የተማረችውን ጓደኛውን ታሪክ በፎቶ በመተረክ ነበር ሥራውን ሲያከናውን የቆየው።ሥራው የቀረበበት መንገድ ደግሞ በመጽሐፍ መልክ ነበር።
በቋሚነትም ሥራ የጀመረው በጂቲዜድ እንደነበር የሚያነሳው ሚካኤል፤ ‹‹ኢንጅነሪንግ ካፓሲቲ ቢውልዲንግ›› በሚል ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እነርሱ ለሚሰሯቸው ሥራዎች ፎቶ በማንሳት ሙያ ተቀጥሮ ሰርቷል።በዚህም ከጀርመኖች ባሻገር ብዙ አገራትን ተዋውቋል።በርከት ያሉ የሥራ እድሎችንም ይዞለት መጥቷል። ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎችን ይሰራ ነበር።ለዚህም ይመስላል አራት ዓመት በፍሪላንስ ከድርጅቱ ሳይለቅ የሰራው።ከድርጅቱ ከለቀቀ በኋላም ቢሆን ብዙ ደንበኞች ነበሩትና አደጉ ከሚባሉት አገራት ጋር ሳይቀር እንዲሰራ ሆኗል።ለአብነትም ከህፃናት አድን ድርጅት(ሴፍ ዘችልድረን)፤ ከአሜሪካን እርዳታ ድርጅት(ዩኤስ ኤድ) ጋር ሰርቷል።አለማቀፋዊ መጽሄቶችና ጋዜጦች ላይም እንዲሁ በፎቶግራፈርነት አገልግሏል።
በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ፎቶ አንሺዎች አለመኖሩ እንደጠቀመው የሚናገረው ሚካኤል፤ የውጪ አገር ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሰሯቸው ሥራዎች ከአገራቸው ፎቶ አንሺ ከማምጣት ለመዳን እርሱ ፎቶ እንዲያነሳላቸው ያደርጋሉ። እርሱም ሙያው ስለሆነ እንደሚሰራላቸውና በስራውም እንደሚደሰቱ አጫውቶናል።
ሚካኤል የአክሱም ሀውልት ተመልሶ አገር ውስጥ ሲተከል በፎቶግራፍ አንሺነት መሳተፉን ይናገራል። ይህም ከአገር ውስጥ ሥራዎቹ የተወደዱለት እንደነበር ያስታውሳል።በፎቶግራፍ ሰራው አገርን ብሎም አለምን እያስተዋወቀ ይገኛል።ጥበባዊና የራስ ፈጠራ የታከለባቸው ፎቶዎች በማንሳት የእርሱ ስራዎች ከሌሎች ልዩ መሆናቸውን ያነሳል።በቋሚነት ካገለገለባቸውና አለምአቀፍ የህትመት ውጤቶች ላይ በተደጋጋሚ ካሳተማቸው መካከል der Spiegel, Jeune Afrique and Enorm የተሰኙት በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በፕሬስ አገልግሎቶችም ላይ በብሉንበርግና ሮይተርስ የህትመት ውጤቶች ፎቶ ግራፎቹ በስፋት ታትመዋል።
ከአለምአቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ በፎቶግራፈርነት ያገለገለው ሚካኤል፤ በርካታ አለማት ላይ ተዘዋውሮ ፎቶዎችን አንስቷል።ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ Medecins sans frontiers, UNESCO እና ጂቲዜድ ይገኙበታል።በብዛት የሚታወቅበት የፎቶ ዘውግ ማህበራዊ ዘገባና ጥበባዊ ዘርፍ በመሆኑም በእነዚህ ብዙዎችን አስደምሟል፤ የተለያዩ የአለም አገራት ላይ በመሄድም አውደርዕዮችን አቅርቧል።ከእነዚህ መካከል ኒዮርክ፣ በርሊን፣ ማድሪድ፣ ሞሮኮ፣ አምስተርዳም፣ ማሊ፣ ማያሚ፣ ሳኦፖሎ ተጠቃሽ ናቸው።
ሚካኤል በተለያዩ የአውሮፓና አፍሪካ አገራት ላይ ተዘዋውሮ የፎቶ ኤግዚቢሽኖችን መሳተፉ በ2004ዓ.ም በአውሮፓ ህብረት አማካኝነት በተዘጋጀው የፎቶ ግራፍ ውድድር ላይ የአፍሪካ ፕሮፌሽናል ፎቶግራፈር ሆኖ በአንደኝነት እንዲመረጥና የዓመቱ የአፍሪካ ምርጡ ፎቶግራፈር እንዲባል አስችሎታል።በጎ ሰውም ተብሎ ለመሸለሙ ምክንያቱ ይኸው የፎቶ ግራፍ ጥበቡ ነበር።ቀለምን ከሸራ ጋር እያዋደደ ሲሰራ የቆየና በአጋጠመው የቀለም አለርጂ ምክንያት ሰዓሊነቱን ያቆመው ሚካኤል፤ ይህንን ሙያ በመልመዱ ደስተኛ ሆኗል።
ለፎቶ ማንሳት ምርጫ አለው
ብዙ ጊዜ በውጪ አገራት የፎቶ ግራፍ አውደርዕይ ሲያዘጋጅ በአዘጋጆቹ ጋባዥነት እንደሚገኝ የሚያነሳው ባለታሪኩ፤ ብዙ ጊዜ አዘጋጆቹ የሚያቀርቡት ሀሳብ ቢወስነውም እኔም ምርጫ እሰጣቸዋለሁ ይላል።ይሁንና ሀሳባቸው ካልተመቸው፤ የእነርሱ ያልሆነውን አንሳና አቅርብልን ሲሉት፤ የመብት ረገጣና ሌሎች ጉዳዮች ሲኖሩ ቅድሚያ ለህሊናው ይሰጣል።ስለዚህም ሀሳባቸውን አይቀበለውም።አገራትን የሚያስነካና የማንኛውንም ሰው ስብዕና በሚጥስ ሰራ ላይም መሳተፍ አይፈልግም።
አስተማሪው ፎቶ
አንዳንድ ሰዎች ባይቀበሉትም እርሱ ግን ‹‹አምኜበት ሰው አስተምሬበታለሁ›› የሚለው የመርካቶ ሴተኛ አዳሪዎች ህይወትን በፎቶ ያስቀረውን ነው።በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ አድናቆትን የቸረለት ነበር። እንደውም እዚህ ላይ እንዴት እንዳደረገው ሲናገር አጃኢብ ያስብላል።ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ከአራት ቀን በላይ ከልብስ መቀየሪያ ቤታቸው በመቀመጥ ካግባባቸው በኋላ ነበር ወደ ፎቶ ማንሳቱ የገባው። አሰሪው ድርጅት ጥምረት ለህይወት የተባለ ቢሆንም ሥራውን የሚሰራበትን ቦታ ያገኝ ዘንድ ብቻ ነበር የረዳው።ከዚያ ትርጉም ያለው የሴተኛ አዳሪዎች ህይወትን በፎቶ የማምጣቱ ድርሻ የእርሱ ሆነ።
በሴተኛ አዳሪዎች ህይወት ዙሪያ የሚሰራና እነርሱ ይህንን ተግባር ስራዬ ብለው ሲሰሩ አደጋ እንዳይገጥማቸው ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውነው ድርጅቱ ሚካኤልን ይህንን እንዲሰራ የመረጠውም እንደሚያደርገው ስላመነ ነው።እርሱም ቢሆን አላሳፈራቸውም።እንደውም ያልጠበቁትን ሁሉ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።በዚያ በተጣበበ ቤት ያንን ሁሉ ተግባር ሳይጣሉ ከውነው መውጣታቸውን በሚገባ በፎቶ አሳይቷል።ሁለት ሳምንት ሙሉ እነርሱ ጋር በመሆን ውስጠ ሚስጥራቸውን በፎቶ ገልጿል።
ሕይወት አስተማሪ ፎቶ ነው ለማለት የሚያስችሉ ነገሮች እንደነበሩበት ይናገራል።ምክንያቱም የፎቶው ባለቤቶች በይፋ ምን ሲሰሩ እንደነበረና ሕይወታቸውን እንዴት እየገፉ እንደሚኖሩ በአደባባይ ገለጻ እያደረጉ አስተምረውበታል።የሰዎችን ምልከታም አቃንተውበታል።መቼም በባህላችን ያየ ይፍረደኝ አይደል የሚባለው።ስለዚህም እነርሱ በፎቶ ብቻ ሳይሆን ኖረውበት ስላሉ ከስሜት ጋር ሆነው ነበር በአውደርዕዩ ፎቶውን ለታዳሚው ሲተነትኑ የነበረው።እናም እንግዳችንም በህይወቴ የሚያስተምር ሥራ ከሰራሁባቸው መካከል የመጀመሪያው ነው ይላል።
ሌላው እስካሁን ካነሳቸው ውስጥ በብዙዎች ዘንድ የታዩለትና አድናቆትን የቸሩለት ደግሞ አዲስ አበባን በፎቶ ካሜራው ያስቀረበት ነው።ከአዲስ አበባ ተነስቶ ብዙ ክልሎችን በማቋረጥ ያነሳቸውም እንዲሁ በብዛት ተመልካች ነበራቸው።ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራዎቹን በድረ ገጽ ላይ የጫነው በማሊው የአፍሪካ ፎቶግራፈር ውድድር ላይ የተሳተፈበትን እንደሆነ የሚያስረዳው ሚካኤል፣ በሲውዲን አገር ተዋቂ የነበረችው ጓደኛው ለውድድሩ እንዲቀርብ አድርጋለት ተቀባይነት አግኝቷል።በዚህም ከአፍሪካ አልፎ ዓለም ላይ እንዲታወቅ ሆኗል።ይህ ደግሞ በፎቶ ግራፍ ማንሳት ምን ያህል መስራት እንደሚችል አሳይቶታል።ብዙ ሰውና ሙያም ቀስሟል።
ድንቃድንቅ በውጪ አገራት
የሰው ፍላጎት መቼም በቀላሉ አይቆምምና የሚካኤልም ሥራ እንደ ወንዝ መፍሰሱን ተያይዞታል።ይህ ደግሞ ከዕለት ዕለት ተዋቂነቱን እያጎላው እንዲመጣ አድርጎት ታላቋ አሜሪካ ላይ አድርሶታል።በዚያም ‹‹ካዮጋ›› እየተባለ የሚጠራውን ጠመዝማዛና ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ አሻራን ያሳረፈ ወንዝ ታሪክ በፎቶ ለማሳየት ችሏል።ይህ የሆነው ደግሞ ከሃምሳ ዓመት በፊት ተበክሎ በመቃጠሉና የአሜሪካ መንግስት በዚያ ወንዝ ዙሪያ ሊሰራበት በመፈለጉ ነው።ሚካኤል ቻድ ላይም የሚሰራውን ቤተመንግስትና ትልቅ ፎቅ በፎቶ ጥበቡ አሳይቷል።በተለይ ፎቶ አንስቶ ካስደነቁት መካከል የጋናው የኳስ ጥንቆላ ጉዳይ በእጅጉ ገርሞት እንደነበር ያነሳል ።
በጋና ብዙ አለም አቀፍ ተጫዋቾች በጥንቆላው ያምናሉ።ስለዚህም የየራሳቸውም ጠንቋይ ጭምር ሊኖራቸው ይችላል።ስለዚህ እንግዳችንም ይህንን ተአምራዊ ክስተት በፎቶው ለማሳየት ከተለያዩ አለምአቀፍ ተጫዋቾች ጋር በመሆን ተዘዋውሯል።በዚህም በጥንቆላው ማንኛውም የእምነት ተከታይ እንደሚያምንበት ተመልክቷል።የተባለውን ሲያደርጉም በመቃብር ቦታ እየሄዱ ለአራትና አምስት ቀናት ሲያድሩም አይቷል።እንደውም አንድ ተጫዋች ያለውን ሲያነሳም እንዲህ ይላል።‹‹ነገ ግጥሚያ የምገባ ከሆነ ጨዋታው ላይ ኃይል ስለማገኝበት ጠንቋዩ ያለኝን አደርጋለሁ ።››
ይህ ድርጊታቸው የገረመው ሚካኤልም ስሜ ታቸውን በፎቶ ለማስቀመጥ ሲል በቀጥታ ወደ ጠንቋዩ ጓዳ አመራ።ቀደም ብሎ ማስፈቀድ ነበረበትና ጥያቄ አቀረበ።ምላሽ ግን ያገኘው ከደቂቃዎች በኋላ ነው።ምክንያቱም ጠንቋዩ መንፈሱን ማና ገር አለበት። እናም ወደ ውስጥ ገብቶ ሲመለስ የነበረውን የአለባበስና አጠቃላይ ሁኔታ መቼም አይረሳውም።ግን ሥራ ነውና በውስጡ ፍራቻ ቢኖርበትም ሊሰራበት ስለፈለገ ብቻ አራት ቀናትን ከእርሱ ጋር አሳለፈ።የሚያደርጋቸውን ሁሉም በፎቶ ቀምሮ ለእይታ አቀረበ።
ፈተና
‹‹የሀሳብ ምንጮቼ ግጥሞች፣ ሙዚቃዎች፣ መልከአምድር፣ ከጓደኛ ጋር የሚደረግ ውይይት፣ ዜናዎችና ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው።ስለዚህ ለእኔ ወራት የተለየ ትርጉም አላቸው።›› የሚለው ባለታሪኩ፤ ወራትን እንደማይመርጥና ሁሉንም በመጡበት ጊዜ የተለየ ቀለምና ማንነትን እንዲያንጸባርቁ አድርጎ እንደሚጠቀምባቸው ይናገራል።ይሁንና በተለያዩ ጉዳች እነዚህ የሥራ አማራጮቹን የሚያጠቡት ችግሮች ይፈጠራሉ።ለአብነትም ያለፉት ሦስቱ ዓመታት በአገሪቱ መረጋጋት አለመኖሩ በጣም ከባድ እንደነበሩበት ያስታውሳል።ከዚያ በፊት ደግሞ ይሰራበት የነበረው ስቲዲዮ ለአለርጂ አጋልጦት መቆየቱንም ያነሳል።ግን ዛሬ ይህንን ሊፈታለት የሚችል ስቲዲዮ እየሰራ በመሆኑ የስዕል ፍቅሩን ለማርካት እንደሚችልም ነግሮናል።ከዚህ ባሻገርም በተለያዩ አካባቢዎች ሲዘዋወር ያገኘውን ተሞክሮ ለአገሩ ልጆች ለማጋራት ከጀርመን ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ለበርካታ ጊዜያት ወጣት የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎችን ነጻ ስልጠና በማዘጋጀት ሰጥቷል።ዛሬም ይህንን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም አጫውቶናል።
ገጠመኝ
አፋር ላይ ነበር ሁነቱ የተከሰተው።ለፎቶ ሥራ ሄዶ ባለበት ወቅት በሌሎች አገራት በተለይም በውጪ አገራት ትልልቅ አደጋዎችን የሚያደርሰው አይነት አውሎንፋስ ተነሳ።በዚህም እርስ በእርስ እንዳይተያዩ ለሰዓታት ተገደቡ።ማንንም መኖሩን ለማረጋገጥ የማይቻልበትም ነበር።እንግዳችን ግን ይህንን ክስተት በፎቶው ለማስቀረት ይጥር ነበር።እናም የቻለውን ያህል ካነሳ በኋላ ግን ካሜራው በነበረው የአቧራ ብዛት ተበላሸ።ግን ምንም ቢሆን እንደማይቆጨው ይናገራል።ምክንያቱም በሰራው ሥራ ከስህተቱ ይማራል እንጂ ለምን አደረኩት ማለት አይወድምና ነው።
መልዕክተ ሚካኤል
እስክሪብቶ ያለው ሁሉ ገጣሚና ደራሲ ሊሆን አይችልም።የውስጥ ፍላጎትና ተሰጥኦን ይጠይቃል።በዚያ ላይ ማህበረሰቡ የለመደውና በፎቶግራፍር ዙሪያ ያለው አመለካከት እጅግ የተዛባ ነው።ፎቶ የሚነሳው በቱሪዝሙ ዘርፍ ብቻ አገርን ለማስተዋወቅ ታስቦ እንደሆነ ይታሰባል።አገር ግን በተለያዩ እሳቤዎች ልትተዋወቅ ትችላለች።ድክመቷ ሁሉ ታይቶ ለችግሯ እልባት የምታገኝበትን ምቹ ሁኔታም ማምጣት ይቻላል።ስለዚህ ሰው መማር ያለበት ይህም እንደሚቻል ነው።
‹‹ሰው በተፈጥሮው መማር ያለበት ከስህተት ነው።መሳሳትን ፈጽሞ መፍራት የለበትም።ይልቁንም ሲሰራ እንደሚሳሳት አምኖ እየተማረ የሚሄድ ከሆነ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል›› የሚለው ሚካኤል፤ ለመሳሳት ክፍት መሆን ያስፈልጋል።መሳሳት የለብኝም ከተባለ ግን መስራት ይቆማል። እናም ሰዎች ከእኔ ቢማሩ የምወደው መሳሳት በመስራት ውስጥ አለ። ስለዚህ ይህንን አምነው መስራትን ነው ይላል።
‹‹ከስዕል ስራም ሆነ ከካሜራ ሥራ እንዳርቅ የሚያደርገኝ ራሴን ለስህተት ክፍት ማድረጌና ስሳሳት እንደምማር በማወቄ ነው።ስለዚህም ስህተት ለእኔ አናጺዬ ነው›› ይላል።ሰዎችም በተሳሳቱ ቁጥር የማይቆጩ፣ መሳሳት ትልቅ ውጤት ያስገኛል ብለው የሚያምኑ፤ መሳሳት ይገነባል፤ መሳሳት አዲስ የፈጠራ ውጤትን ያስገኛል፤ መሳሳት መሰረትን ያስተካክል የሚሉ መሆን እንዳለባቸውም ይመክራል።እናም ይህ ምክረ ሀሳብ በውስጣችን ገብቶ እንማርበት በማለት ለዛሬ አበቃን።ሰላም!!
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው