“ጥንታዊቷ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልጅህን ከ12 ዓመቱ በፊት ስጠኝና ፊተኛ ካቶሊክ አደርገዋለሁ” የሚል መሰረታዊ መርህ ነበራት። ይህ አለምክንያት አልተባ ለም። ልጆች በልጅነታቸው የሚሰጣቸውን ማናቸውንም ዕውቀት ለመልካምም ሆነ ለክፉ ለመጠቀም፣ የ”ንፋስ ዕድሜ” ዘመና ቸው ጥሩ የህትመት ዘመናቸው ስለሆነ ነው። ማናቸውንም ነገር በልባቸው አትሞ ለማሳደግ፣ ይህ ዕድሜ፣ የሚመረጥበት ምክንያት፣ እንደ ንፁህ ወረቀት ወይም ፈሳሽ እንደሚመጥ ስፖንጅ ስለሚታሰብ ነው።
በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከፓትሪስ ሉሙምባ ዘመን ጀምሮ፣ የተነሱት ግጭቶች ያላባሩት በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ማዕድን ብዛት ምዕራባውያንንም ሆነ የአካባቢውን ልሒቅ ምሁራን ጭምር ስለሚያጓጓ ብቻ አልነበረም ፤ ዋነኛው ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ በአስተሳሰብ አለመስማማት የተነሳ የሚፈጠሩ “ሁሉን ለእኔ” የሚል አስተሳሰብ ውጤትም ነው። ይሁንናም፣ ሁሉም “ተቃዋሚ” ሃይሎች ሊባል በሚችል መልክ ለውጊያ የሚጠቀሙት ከገጠር ቀመስ ትምህርት ቤት በሚታፈኑና በሚሰለጥኑ የ5ኛ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ነው። የእነዚህን ልጆች ዕድሜ ስትገምቱት ከ11 እስከ 14ኛ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ለጋ ህጻናት ናቸው።
ምንም እንኳን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መብት ኮንቬንሽን እነዚህን ህጻናት ለጦርነትም ሆነ ለሥራ “ባርነት” መጠቀምን የሚከለክል ህግ ቢያኖርም አዋጊዎቹ ለጫካ ህግ በመገዛትና ዓለማቀፉን ህግ በመጣረስ ሲፈጽሙት ይስተዋላል። እንዲያውም ጦርነት የራሱ ህግ አለው እንጂ፣ በሲቪል የሰላም ህግጋት አይገዛም ነው የሚሉት።
የኡጋንዳው ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ (LRA) መሪ፣ ጆሴፍ ኮኒ የቅርብ ሰው ለመንግስት ጦር እጁን ከሰጠ በኋላ ሲናገር፣ የምንጠቀምባቸው ህጻናት (ግልገል አንበሶች) “ምን፣ ለምን”፣ ብለው የማይጠይቁና “እንዴትና የት” እንደሚደረግ የሚሰጣቸውን መመሪያ በማወቅ የሚፈጽሙ ከመሳሪያዎቻችን እንደ አንዱ የምንቆጥራቸው “ዕቃዎች” ናቸው። በውስጣቸው ፍርሃት የሚባል ነገር ስለሌለ እና ለማነሳሳት ቀላል ስለሆኑ በሥራቸው ውጤታማ ናቸው፤ ሲል ነው፤ የመሰከረላቸው።
ሥራቸውንም ሲያብራራ ወደ አንድ ዘመቻ ስንሄድ የማሸበሩን ሥራ ቀድመው እንዲያከናውኑ የምንሰጣቸውን መመሪያ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚቻኮሉ (የሚንቀዠቀዡ ማለት ይቀላል)፣ ሊገደሉ የሚችሉ ቢሆንም ዓላማችንን ለማስፈጸም ሁሌ ዝግጁ የሆኑ መሳሪያዎቻችን ናቸው፤ የመንደር ጎጆዎች አቃጥላችሁ፣ ከብት እየነዳችሁ ውጡ ከተባሉ፣ ያለጥርጥር ለማከናወን የማያመነቱና የሚፈጽሙ ናቸው፣ ሲል ነው፤ የተናገረላቸው።
ህጻናት በሚያገኙት ትናንሽ ነገር ሁሉ ስለሚገረሙ ከዘመቻ በኋላ በጓደኞቻቸው ፊት የዘንባባ ዝንጣፊ በጸጉራቸው ላይ ስንሰካላቸው “እከሌ እኮ ሶስት ዘንባባ አለው፤ እከሌ አምስት ተደርጎለታል “ በመባባል የጭካኔ ፉክክር እንፈጥርባቸዋለን፤ ይላል።
በካምቦዲያ ፖልፖት የተባለው ምህረት የለሽ መሪ ይህንኑ የጭካኔ ድርጊት በሥልጣን ዘመኑ ያለማሰለስ አድርጎታል። የሚመለመሉ ህጻናትን “የካምቦዲያ አበቦች “ የሚል ስም ይሰጣቸውና በሚሰማሩበት ስፍራ አዛውንትን፣ መምህራንን፣ ታዋቂ ሰዎችን በመግደል እንዲጀምሩ ያደርጓቸውና ለማንም ምህረት የሌላቸው አውሬዎች እንዲሆኑ ያበቋቸዋል። በጭካኔያቸውም ልክ በማሞካሸት ያበላልጧቸዋል፤ ልጆቹም ለበለጠ ጭካኔ ራሳቸውን ያዘጋጃሉ እንጂ፤ ፀፀት ሲያልፍም አይነካቸውም። ስለዚህ ነበረ፤ በፖልፖት አምስት ዓመት በማይሞላ አገዛዝ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ካምቦዲያውያን ለእልቂት የተዳረጉት።
“ፍንድቅ ፍክክ ያሉ አዳዲስ አበቦች ማበብ ያብባሉ፤ ግን ለቀበጥባጦች የስሜት ማብረጃ ሆነው ይቀራሉ።” አሌክሳንደር ፑሽኪን (ትርጉም በአያልነህ ሙላት)፤
እንዳለው፣ የእነዚህን እምቦቃቅላ ህጻናት እድሜ ለፍላጎታቸው በማጣመም፣ የክፉ ፍላጎታቸው ማጭድ በማድረግ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ አምባገነኖችና ወንበዴዎች ይጠቀሙባቸዋል። በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ሆነ በኡጋንዳ፣ በሴራሊዮንም ሆነ በአፍጋኒስታን፤ በፊሊፒንስም ሆነ በፓኪስታን፣ ይህ የአዋቂ አጥፊ ወንጀል ወጣትና ታዳጊ ልጆችን መሳሪያ በማድረግ ተፈጽሟል፤ እየተፈፀመም ነው።
የሥነ-ልቡና አዋቂዎች ህጻናትን እንደ ባለተስፋ ችግኝ ያይዋቸዋል። ችግኞችን በተደላደለ የአየር ጠባይ፤ አፈርና ምቹ የውኃ ፍሰት እንዲሁም ወቅት ላይ ከተከልናቸው ዛፍ ለመሆንና ፍሬያማነታቸውን ለማ ግኘት አንቸገርም። በዚህ ሂደትም ውጤ ታማነታቸውን አንጠራጠርም።
እንዲህም ሆኖ በሥርዓት ሣንተክልና ሳንንከባከባቸው ፍሬያማነትንና የአየር ንብ ረት መከላከያ ጋሻነታቸውን ማውራትም መጠበቅም አንችልም። ችግኞቹን፣ ለተከ ልንበት ዓላማ ማብቃት እንዲሁ ህጻናትን ለሚኖሩለት የህይወት ግብ ከማብቃት ጋር ይመሳሰላል።
ለዚህ ነው፣ አሁን በወጣቶቻችን ላይ ለመስራት ተግተን መቆም፤ ሳንተኛ መንቃት የሚገባን። ወጣቶችም አይዟችሁ ባይ ሲያገኙ ነገ እነርሱም አይዞህ ብለው ለመርዳት አያመነቱም። ሃገራችን የእርስ በእርስ መተጋገዛችንን እንጂ መገፋፋታችንን እና መቀናቀናችንን አትፈልግም፤ እኛም ለሰላሟ በጽኑ ልንቆምላት ይገባል። መቃወምም ካለ የሐሳብ ፍጭት ነው፤ መኖር ያለበት።
ህጻናትን፣ ከጠዋት ዕድሜያቸውም ጀምሮ መልካምነትን ካሳየናቸው በመልካምነት መንገድ መሄዳቸው ግልጽ የመሆኑን ያክል ካቀበጥናቸው “አጥሚቱ አልታኘክ አለኝ”፣ “ሶፋው ይቆረቁራል”፣ “ ላሚቱ ልትበላኝ ነበረ”፣ የማለት ዝንባሌ ሊያሳድጉ ይችላሉ። ስለዚህ መቅጣትም መቆጣትም በሚገባን ጊዜ የምንቀጣውን ያህል፣ በፍቅርም ማባበል የተገባ ነው። “ልጁን ከህጻንነት ሃሳቡ አትከልክለው” የሚልም አባባል አለና። ህጻናት እያጠፉና እየታረሙ፣ እየተጫወቱና እየተማሩ፣ እየሰበሩና እየተጠገኑ ይሄዳሉ እንጂ፤ በፍጽምናና በሥራ ዓይን እያየናቸው ልናስደነግጣቸው አይገባንም።
ስለዚህ የልጁ አባት የሆነ ሰው፣ በፍቅር ስም ሳያቀብጥም በሥነሥርዓትም ስም ልጁን በትንሽ ትልቁ ጉዳይ ሳያነውርና ሳይነዘነዝ፣ ልጁን ማሳደግ ይገባዋል፤ ማለቴ ነው።
ችግኝን የሚተክል ሰው፣ ተስፋን ነው፤ በምድር ላይ የሚተክለው፤ ምክንያቱም እርግጠኛ ሆኖና ምድርን በማመን ታሳ ድግልኛለች ብሎ የእጁን ፍሬ ለእርሷ ሰጥቷታልና። እንዲሁም ልጅን የሚወልድ ሰው ስጦታው ከላይ ቢሆንም የተሰጠውን ፍሬ ጠብቆ በምድር ላይ ለተወሰነለት ኣላማ ሊያሳድግ ተስፋን ሰንቋል። በአራሹና በወላጁ መካከል ያለውም ተመሳስሎ ይህ ነው።
አባቶችና ታላላቆች፣ ለልጆቻችን እንደ ችግኝ ተካይ አራሽና ኮትኳች የምንቆጠረው ያለምክንያት አይደለም። በልጆቹ ውስጥ የምንጨምረው፣ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ምግብ፤ ቅርርብና ትሽሽት፣ ልጆች በእምነት እንዲያድጉ መንገድ ይከፍትላቸዋል፣ ፈለግ ይጠርግላቸዋል።
በራቅናቸው ቁጥር በአለመፈለግ ስሜት ቁጠኛና ክፉ፣ ነጭናጫና ሆደ-ባሻ ሊያደ ርጋቸው እንደሚችል ሥነ-ልቡናዊ ጥናቶች ያመለክታሉ። ወላጆች እጃቸው ምንም ያህል ቢያጥር፣ ቢያጡና ቢነጡም ዋጋ የማያወጡበትን ጊዜና ትኩረት፣ ለልጆቻቸው መስጠታቸው ልጆቻቸው አለኝታና ተስፋ በማድረግ እንዲያብቡ ያደርጋቸዋል።
የደን ጥናትና የአትክልት እንክብካቤ ባለሙያዎች፣ ችግኞቹን በሳምንትና ከዚያም ባነሱ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት በማየት ጊዜ ስንሰጣቸው በህይወት የሚቆዩበትን እድሜ እንደምናረዝምላቸው ይናገራሉ። በጃፓን የተደረገ የሥነ ህይወት ጥናት እንደሚያሳየው አትክልቶች ክፉ ቃላትንና ክፉ አቀራረብን ከደግና መልካም ቃላት እንደሚለዩ አመላ ክተዋል። መናገር የማይችሉ ህጻናትም የእ ርግማንን እና የማጽናናትን፣ የማጣጣያና የማበረታቻ ቃላትን ልዩነት በሚገባ ይገነዘ ባሉ፣ ይላሉ የሥነ-ልቡና አጥኚዎች።
ይህንንም ከጨቅላነት ያለፈ ዕድሜ ላይ ያሉ ማለትም 10 ወርና ከዚያ በላይ ያላቸውን ልጆቻችሁን እስቲ ሞክሯቸውና እዩ። ስትቆጧቸው ያውቃሉ፤ ስታባብሏቸውና ስታደንቋቸው ይለያሉ። ይህ ደመነፍሳዊም በሎት ተፈጥሯዊ እውነት ነው።
ችግኞቻችንን ውጤታማ ለማድረግ መሬቱን ቀድሞ ማዘጋጀት፣ መለድለድ፣ ችግኝ ለመቀበል ማብቃትና ከዚያም ከተከሉ በኋላ አፈሩን በመኮትኮት ማላላትና ለጋ የሆነው የችግኙ ስር እንዲዘረጋጋ መርዳት እንችልበታለን። ልጆቻችንም ያልተገደበ አሳቢ አእምሮ፣ የተፍታታ ሩቅ እይታ እንዲኖራቸው ማድረግ የምንችለው በጠዋት ዕድሜያቸው ላይ ነው። ስለዚህ ለመሬቱ እንደሰጠነው እምነት ለእነርሱም የተለወጠ አስተሳሰብ እምነታችንን እንጣል።
“ከአፈር ላይ ወድቀው በ”ሻሪ ሽረት ህግ” ሥርን እየሰሩ፣
አድገውና ደርሰው፤ ፍሬ እንዲያፈሩ፣
ውሃ አየርና አፈር ከመጋገብናቸው፣
ችግኝ እፅዋቱ ህይወት ሰጪ ናቸው።
የሰው ልጅ እንዲሁ፤ ትልም ከተሰጠው፣
ከተደረገለት በላይ ነው፤ የሚያፈራው!!” (ያልታወቀ ገጣሚ)
እናም ችግኞችንና ህጻናትን ከአባባ ተስፋዬ፣ “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች” ብሒል ጋር አስተሳስረን ለፍሬ እንዲበቁልን በመትከል ሁለት ስለት ያለው ተግባር እንፈጽም። አንደኛው በረሃማነትን በመታገል የአየር ንብረትን መዛባትን መከላከል ሲሆን፣ ሁለተኛው በልጆቻችን ላይ ያለውን የእርስ በእርስ የጥላቻ ጫካ በመመንጠር፣ ልባቸውን በፍቅርና በምህረት ተክል፣ በይቅርባይነት መንፈስ በማነጽ የህይወት ውሃ ምንጭ ከውስጣቸው ፈልቆ፣ ምድር ሰፊና ለሰው ልጆች ሁሉ የተፈጠረች፣ ባለፀጋና ለሁላችንም የምትበቃ መኖሪያ መሆኗን ማስገንዘብ ይሆ ንልናል።
በሌላ አባባል፣ በአንድ በኩል በወጣቶ ቻችን ልብና አእምሮ ላይ የመግባባትና የአንድነት ችግኝ እየተከልን፣ በሌላ በኩል ከዓለም የሚያገኙትን እውቀት ከደመ- ነፍሳዊነት በወጣ መንገድ በቀጥተኛነት ተቀብ ለው እየተገበሩ ለዚህች ሐገር ብልጽግና መሰረት የተጣለውን ግብ እንዲያሳኩ እና ብቃቸው ማለት ነው።
በልባቸው የምንተክለው ተስፋ ምርኩዝ ሆኗቸው፣ በልባቸው የምናስቀምጠው እምነት ሃይል እየፈጠረላቸው ወደፊታቸውን በብሩህ ስሜት እንዲያዩ ማድረግ ይገባናል።
“ክፉ ችግኝ አረም ይጠራል “ ይላሉ፤ አባቶቻችን ። አረም ጠሪውን ችግኝ በዝምታ ካየነው አያድግም እንጂ፤ ካደገ አረም የተጣባው ሆኖ እድገቱ ለራሱም ለሌሎችም ዕጽዋት ጠንቅ ነው፤ የሚሆነው።
እዚች ላይ አንድ ምሳሌ ላክልላችሁ። ልጁ በምንኖርበት ሰፈር ውስጥ ከወላጆቹ ጋር የሚኖርና ዕድሜው አስር የማይሞላ ነው። ከወዳጆቼ መካከል አንዱን በይበልጥ ስለሚጠጋው ያወራዋል። አንድ ቀን በጋራ ሰፈር ውስጥ በቆምንበት እፍታ፣ ድንገት ጠራውና እንዲህ ሲል ጠየቀው።
“ቡቹ፣ ስታድግ ምንድነው የምትሆነው?” ሲል ወዳጄ ይጠይቃል።
“አናጢ!” (ልጅ ይመልሳል)
“ከዚያስ?”
“አረቄ ጠጣለሁ፤ ሚስቴን ደበድባለሁ።” (ልጅ ይመልስለታል) ጠያቂም በልጁ መልስ፣ ክትክት ብሎ ይስቃል። አንዳንድ ሰዎች በማያስቅ ነገር የሚስቅን ሰው ሲያዩ፣ ጥርሱ “ለእንትን” አይትረፍና ይላሉ፤ ለእኔ ግን አስደንጋጭ መልስ ነበረ። እውነት ነው፤ ትንሽ ፈገግ ያሰኛል፤ ግን ያሳስባል።
ይኼ ህጻን፣ የተዘራበትን ነው፤ ያፈራው። ያየውን ነው፤ የሚናገረው፤ የኖረውን ነው፤ የመሰከረው። ስለዚህ ልጆቻችንን እንደምንንከባከባቸው ችግኞች እናስባቸው። ደግ ደጉን ካሳየናቸው፤ የበለጠ ደግ ያፈሩልናል። ምርጥ ምርጡን ባናገኝ እንኳን ያለውን መልካም ካደረስንላቸው ትውልድ ይካሳል። ነገ የእነርሱ ናትና!! አለበለዚያ “አውሎ ነፋስ የዘራ ማዕበል ማጨዱ የታመነ ነው”፤ የትም አያመልጥም። የምናጭደው እንዲሁ የዘራነውን ነው፤ ላም ባልዋለበት ኩበት አይለቀምም እንዲሉ፤ እናቶቻችን።
ሃላፊነትንም በትንንሽ ደረጃ እናለማ ምዳቸው፤ መፈፀማቸውን እንከታተል፤ ግብረ-መልስ በየጊዜው እንስጣቸው፤ በማለዳ ዕድሜያቸው ጀምሮ መጨረስን ከተለማመዱ፣ ሲያድጉ ጀምረው አይተውም፤ አቅደው አይቀሩም፤ አብረው ጀምረው ጥለው አይጠፉም። ኧረ፣ ስለችግኝ ሳነሳ….እ… 4 ቢሊዮኑን ችግኝ እየተንከባከብን ነው፣ ወይስ ለአረም ተውነው? ወልዶ ከሚጥል፣ ተክሎ ከሚተው እጅና ወላጅ ይሰውራችሁ።
እስከሳምንት መልካሙን ሁሉ ተመኘ ሁላችሁ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረመ 24/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ