የአገሪቱን የትምህርትና ስልጠና ሥርዓት ለማሻሻል ባለፉት ሦስት ዓመታት የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያካተተ ጥናት ሲካሄድ ቆይቶ ካለፈው ነሐሴ 14 እስከ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት የጥናቱ ውጤት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን አካቶ በታዋቂ ምሁራን የተጠናው ይህ አገራዊ ጥናት አሁን ያለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ መሻሻልና መለወጥ የሚገባቸውን ጉዳዮችና ፖሊሲው በቀጣይ የት መድረስ እንዳለበት የሚያመላክቱ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል፡፡
የጥናቱን ውጤት መነሻ በማድረግ የአስራ አምስት ዓመታት አገራዊ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ፍኖተ ካርታው የመጨረሻ ቅርጹን ይዞ ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት እስካሁን ድረስ አጠቃላይ ህዝቡን ጨምሮ በአመራሩ፣ በትምህርት ባለሙያዎችና በምሁራን በርካታ ውይይቶች እየተደረገበት ይገኛል፡፡ እስካሁን በተደረጉ ውይይቶችም አጥኝዎች በርካታ ጠቃሚ ግብረ መልሶችን አግኝተው የመጀመሪያ ዙር ማሻሻያ ያደረጉ ሲሆን ፍኖተ ካርታው በቀጣይ አስራ አምስት ዓመታት ማሳካት የሚገባቸውን ዋና ዋና ግቦችም መለየትም ተጀምሯል፡፡
አሁን ባለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ላይ ለውጥ ሊደረግባቸው የሚችሉ ዋና ዋና ይዘቶችና በፍኖተ ካርታው ላይ በአዲስ መልክ የሚካተቱ መሰረታዊ ጉዳዮች መኖራቸውንም የትምህርት ሚንስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ ሰሞኑን በሰጡት አጠቃላይ መግለጫ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ እኛም በዛሬው ዝግጅታችን እነኝህን ለውጥ ሊደረግባቸው የሚችሉ የፖሊሲ ይዘቶችና የአዲሱ ፍኖተ ካርታ ማጠንጠኛ ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡
የተማሪዎች ትምህርት መግቢያ ዕድሜ
በፍኖተ ካርታው ላይ በመሰረታዊነት መለወጥ ይገባቸዋል ተብለው ከቀረቡና በአጥኝዎችና በምሁራን መካከል ክርክር ካስነሱ ጉዳዮች መካከል የመጀመሪያው የተማሪዎች ትምህርት መግቢያ ዕድሜ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያ በአሁኑ ሰዓት ያለው የተማሪዎች የትምህርት መግቢያ ዕድሜ ሰባት ዓመት ነው፡፡ በአዲሱ ትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ ደግሞ የትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ ስድስት ዓመት እንዲሆን አጥኝዎቹ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ይሁን እንጅ ሃሳቡ በፖሊሲ አውጭዎችና በሚኒስቴሩ ሰዎች በኩል ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ በመንግስት በኩል ለዚህ የሚቀርበው መከራከሪያ ደግሞ ሰማንያ በመቶና ከዚያ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ በአርሶ አደርነትና በአርብቶ አደርነት በገጠር የሚኖር እንደመሆኑ መጠን አሁንም ቢሆን በርካታ ትምህርት ቤቶች ከመኖሪያ ቤቶች ርቀው የሚገኙ በመሆናቸው ከሰባት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ይቸገራሉ የሚል ነው፡፡
በሌላ በኩል ምሁራኑ መሰረተ ልማቶች እየተስፋፉ በመሆናቸውና ትምህርት ቤቶች በየአካባቢው በቅርብ ርቀት እየተገነቡ በመሆናቸው የልጆች የመግቢያ ዕድሜ ወደ ስድስት ዓመት ዝቅ ቢል የሚጠቅም እንጂ ያን ያህል የሚጎዳ ነገር አይሆንም ባይ ናቸው፡፡ “ይሁን እንጅ ትምህርት ቤቶች ሩቅ በመሆናቸው አሁንም ቢሆን ከባድ ሙቀት ባለበት ከሦስት እስከ አምስት ኪሎ ሜትሮች ድረስ በእግራቸው የሚጓዙ፣ ትልልቅ ወንዞችን ተሻግረው የሚሄዱ፣ ዳገት የሚወጡ፣ ቁልቁለት የሚወርዱ የአርብቶና አርሶ አደር ልጆች በመኖራቸው ጉዳዩን በጥሞና እየተወያየንበት ነው” ይላሉ የትምህርት ሚንስትሩ፡፡ እናም ጉዳዩ ያለቀለት አለመሆኑንና በቀጣይ በሚደረጉ ተከታታይ ውይይቶችና ክርክሮች ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የጠቆሙት፡፡
የትምህርት መዋቅራዊ ለውጥ
ሁለተኛው ክርክር እየተደረገበት የሚገኘው ጉዳይ የትምህርት መዋቅራዊ ለውጥ ነው፡፡ አሁን ባለው ሥርዓተ ትምህርት የአጠቃላይ ትምህርት በሁለት ደረጃዎች ተከፍሎ የሚሰጥና በአስር ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ አወቃቀር ነው ያለው፡፡ ይህም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከአንድ እስከ አራትና ከአምስት እስከ ስምንት በሚል በሁለት ደረጃዎች የተከፈለ የስምንት ዓመት ትምህርት ሲሆን የሁለተኛ ደረጃውም እንደዚሁ ከዘጠኝ እስከ አስርና ከአስራ አንድ እስከ አስራ ሁለት በሁለት የተከፈለ ነው፡፡ አጠቃላይ ትምህርት የሚባለው አንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶችን የሚያጠቃልል ሆኖ ሳለ አሁን ባለው አወቃቀር አጠቃላይ ትምህርት የሚያልቀው ግን አስረኛ ክፍል ላይ ነው፡፡
“በአጠቃላይ ትምህርት ሥር ያለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከዘጠኝ እስከ አስርና ከአስራ አንድ እስከ አስራ ሁለት ያሉትን ክፍሎች ይዟል፡፡ ይሁን እንጂ አጠቃላይ ትምህርቱ አስር ዓመት ላይ የሚያልቅ ከመሆኑ አኳያ አስራ አንድና አስራ ሁለተኛ ክፍሎችን የያዘው የሁለተኛ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል ትምህርት በአጠቃላይ ትምህርት ሥር መካተት ያልነበረበት ከመሆኑም ባሻገር ዓላማቸውም የተለያየ ነው፡፡ ስለሆነም መዋቅሩ እንዲቀየር በአጥኝዎች ምክረ ሃሳብ ቀርቦ ክርክር እየተደረገበት እንደሚገኝ ያመላከቱት የትምህርት ሚኒስትሩ የመጨረሻ ውሳኔ ባይሰጥበትም ይሔኛው ሃሳብ በትምህርት ሚኒስቴር በኩልም ድጋፍ እያገኘ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
የመዋቅር ለውጡ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ የሚተገበር ከሆነም የትምህርት ደረጃ አወቃቀሩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡ የአጠቃላይ ትምህርት በአራት ደረጃዎች ተከፍሎ በአስራ ሁለት ዓመት የጊዜ ክልል ውስጥ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ይኸውም ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል ስድስት ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት፣ ሁለት ዓመት የመካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል አራት ዓመት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በዚህም አጠቃላይ ትምህርት የሚጠናቀቀው ልጆች አስራ ስምንት ዓመታቸውን ሲጨርሱ መሆን ይገባዋል የሚለው ጎልቶ እየወጣ ያለ መሰረታዊ ሃሳብ ሆኗል፡፡
የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ
በፍኖተ ካርታው መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል ተብለው እየተሰተራባቸው ካሉ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ሥርዓተ ትምህርት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል፡፡ ነባሩ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ከሚተችባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው ፖሊሲው ሙሉ በሙሉ በውጭው ዓለም ዕውቀትና ፍልስፍና ላይ የተመሰረተና ለሃገር በቀል ዕውቀቶች ቦታ ያልሰጠ መሆኑ ነው፡፡ “ይሁን እንጂ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ የዳበረ ሃገር በቀል ዕውቀት አለ” የሚሉት የትምህርት ሚንኒስትሩ፤ ስለሆነም አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ እነዚህን ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሃገር በቀል ዕውቀቶች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ አካቶ የሚይዝ ይሆናል፡፡ ለዚህም ጃፓኖችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
ጃፓኖች በሳይንስና ቴክኖሎጂ
እጅግ በጣም የመጠቁና የሰለጠኑ ህዝቦች ቢሆኑም ለባህላቸው ከፍተኛ ክብር ይሰጣሉ፡፡ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲያቸው የተመሰረተውም በባህላቸው ላይ ነው፤ የዘመናዊ ስልጣኔ አሉታዊ ጎን የማይጎዳቸው ስልጡን ህዝቦች የሆኑትም ለዚሁ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከባህል፣ ከትውፊትና ከሃይማኖት ወስዳ በከፍተኛ ደረጃ ልትጠቀምባቸው የምትችልባቸው በርካታ ሃገር በቀል ፍልስፍናዎችና ዕውቀቶች አሏት፡፡ ለአብነትም ጀርመኖች ከኢትዮጵያ ወስደው በዓለም ላይ ቁንጮ የሆኑበትን የመድሃኒትና የህክምና ሳይንስ መገኛ የሆነውን የጥንታዊ የግዕዝ ድርሳናት ጥበቦችና የዓለም የእውነተኛ ዲሞክራሲ ተምሳሌት የሆነውን የገዳ ሥርዓት ያነሳሉ፡፡
ከይዘት አኳያም አሁን ያለው ሥርዓተ ትምህርት በላይኞቹ የክፍል ደረጃዎች በአነስተኛ ደረጃ ካለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሌላ በዝቅተኛ ክፍሎች ላይ የሙያ ትምህርቶችን ያካተተ ባለመሆኑ ለሙያ የሚያዘጋጅና ፈጠራን የሚያበረ ታታ አልነበረም፡፡ ስለሆነም የትምህርት ሥርዓቱ ከዝቅተኞቹ ክፍሎች ጀምሮ የሙያና የክህሎት ትምህርቶችን ያካተተ ይዘት እንዲኖረውና ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምረው ሙያን እንዲለማመዱና ሥራ ጠባቂ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ መሆን የሚችሉ አምራች ዜጎችን የሚያፈራ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
የአሰለጣጠን ለውጥና የኢትዮጵያዊነት ኮርስ
አሰለጣጠንን በተመለከተም መሰረታዊ ለውጥ ይደረጋል፡፡ ይኸውም ከአጫጭር ስልጠናዎች ውጭ ማንኛውም ሰልጣኝ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ መሆን ግድ ይለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአስረኛ ክፍል በቴክኒክና ሙያና በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ገብቶ መሰልጠን የሚቻልበት አሰራርም የሚቀር ይሆናል፡፡ ከዚህም በአሻገር በሁለተኛና በድረ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲካተት ይደረጋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ቆይታም በመሰረታዊነት የሚለወጥ ይሆናል፡፡ በዚህም አሁን ያለው ዝቅተኛው የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታ ከሦስት ዓመት ወደ አራት ዓመት ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡ በሚጨመረው አንድ ዓመትም ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊነትን በመደበኛ ኮርስነት እንዲወስዱት ይደረጋል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት አገሪቱ የምትፈልገው በዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እርስ በእርሱ ተዋዶና ተቻችሎ የሚኖር፣ ሃገሩን የሚወድና ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ጠብቆ ሃገሩን ተባብሮ የሚገነባ ችግር ፈች ትውልድ በመሆኑ ይህንን የሚረዳ ትውልድ ለመፍጠር ነው፡፡ የፍኖተ ካርታው መነሻና በቀጣይ የአገሪቱ መሰረታዊ የትምህርት ፍልስፍና ሆኖ የሚያገለግለውም ማንነቱን በጥልቀት የሚገነዘብ፣ ኢትዮጵዊነቱን የሚወድና አገራዊ አንድነቱንም የሚጠብቅ ዘመኑን የሚመጥን ስልጡን ትውልድ መገንባት በመሆኑ የአሰለጣጠን ሥርዓቱም ይህንኑ መሰረት አድርጎ የሚቀየር እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2011
ይበል ካሳ