የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተት /Adverse Drug Event/ መድሃኒቶች ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነታቸው በሳይንሳዊ መንገድ ከተፈተሸ በኋላ በሰዎች ሲወሰዱ የሚፈጠር አላስፈላጊ ክስተት ነው፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው መስፈርት እንደሚያሳየው፤ በአንድ ሃገር ውስጥ ካለው የመድሃኒትና የጤና ተቋማት አቅርቦት አንፃር ከ100 ሺ ሰዎች መካከል 200 አላስፈላጊ የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተት ሪፖርቶች ከጤና ባለሞያዎች ይጠበቃሉ፡፡ የኢትዮጵያም የህዝብ ቁጥር ከ100 ሚሊዮን በላይ በመሆኑ ከስታንዳርዱ አንፃር ተሰልቶ በየአመቱ 20 ሺ የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተት ሪፖርቶች ይጠበቃሉ፡፡
ይሁንና በ2011 ዓ.ም 1 ሺ 400መቶ ዎቹ ብቻ ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 500 ያህሉ በየጊዜው ጥቅም ላይ ከሚውሉ መድሃኒቶች አንፃር ሪፖርት የተደረጉ ናቸው፡፡ 900 ያህሉ ደግሞ በአንድ ጊዜ ለብዙ ታማሚዎች መድሃኒት በመስጠት ሂደት በሚከሰቱ የጎንዮሽ ክስተቶች ምክንያት ሪፖርት የተደረጉ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ከመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶች ጋር በተያያዘ ለባለስልጣኑ የሚደርሰው ሪፖርት በጣም ትንሽ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የመድሃኒት ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ማእከል አማካሪ ወይዘሮ ኤልሳቤት ወልደማሪያም እንደሚሉት፤ ከአሁን ቀደም የጤና ባለሞያዎች የመድሃኒት የጎንዮሽ ከስተቶችን ለባለስልጣኑ ሪፖርት ሲያደርጉ የነበሩት የቢጫ ፎርምና 8482 የነፃ የስልክ ጥሪ መስመርን በመጠቀም ነበር፡፡ ይሁንና የሪፖርት ስርአቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ ብሎም ወቅታዊ መረጃዎችን በትኩሱ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለማቅረብ የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶችን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ/E-reporting/ እና በሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያ /medsafety/ አማካኝነት በድረ ገፅ ሪፖርት ማድረግ አስፈልጓል፡፡
የሪፖርት መተግበሪያዎቹ ከአለም ጤና ድርጅትና ከእንግሊዝ የመድሃኒትና የጤና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ /MHRA/ ጋር በመተባበር የተዘጋጁ ሲሆን ሁሉም የጤና ተቋማት እንዲጠቀሙባቸው ተደርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም በተለይ የጤና ባለሞያዎች በህክምና ሂደት ወይም ከመድሃኒት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸውን የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶችን በመተግበሪያዎቹ አማካኝነት በተቀላጠፈ ሁኔታ ለባለስልጣኑ ሪፖርት ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡
እንደ አማካሪዋ ገለፃ፤ ቀደም ሲል በነበረው የሪፖርት ስርአት የጤና ባለሞያዎች የሚያጋጥሟቸውን ክስተቶች በቢጫ ፎርም መዝግበው በፖስታ ቤት አማካኝነት ወደ ባለስልጣኑ ሲልኩ መዘግየትና አልፎ አልፎም መቅረት ጭምር ያጋጥማል፡፡ ይህም ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ከመድሃኒቶች አወሳሰድ ጋር በተያያዘ በሚያጋጥሙ አላስፈላጊ ክስተቶች ላይ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት ሆኗል፡፡ በመሆኑም የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተት ሪፖርቶች እንዳይዘገዩ አዲሱን የሪፖርት ስርአት መተግበር አስፈልጓል፡፡
ማንኛውም የጤና ባለሞያ መተግበሪያዎቹን በቀላሉ ሊያገኛቸውና ሊጠቀምባቸው እንደሚችል የሚገልፁት አማካሪዋ፤ ይህም የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶችን በቶሎ ሪፖርት በማድረግ ባለስልጣኑ የሚፈልገውን የሪፖርት ቁጥር እንዲያገኝ ያስችለዋል:: ቀደም ሲል የነበሩት የሪፖርት ስርአቶችም ከአዲሱ የሪፖርት ስርአት ጋር አብረው ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ የመንግስትም ሆኑ የግል ጤና ተቋማት መተግበሪያዎቹን በመጠቀም ክስተቶቹን ሪፖርት ማድረግ ይችላሉ፡፡
በአለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች አማካሪ አቶ መንግስተአብ ወልደአረጋይ እንደሚናገሩት፤ የአለም ጤና ድርጅት ሃገራትን በስትራቴጂና በቴክኒክ ያግዛል፡፡ በኢትዮጵያም በምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፍላጎት የመድሃኒት ደህንነትና ቁጥጥር ስርአትን ለማጠናከር በተዘጋጀው ጥናት ድጋፉን አሳይቷል፡፡ በጥናቱ መነሻነትም የመድሃኒት ደህንነትና ቁጥጥር ስርአት መዘርጋቱ፣ የህግ ማእቀፍና የሪፖርት ስርአት መኖሩ በጥንካሬ ተወስዷል፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርቱ የአለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ስታንዳርድ አንፃር ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሪፖርቱ የሚጨምርበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጥናቱ አመልክቷል፡፡
አማካሪው እንደሚሉት፤ ሪፖርቱን ለመጨመር ያልተማከለ አሰራር የሚኖርበት መንገድ በዋናነትም በርከት ያሉ የመድሃኒት ደህንነትና ቁጥጥር ስርአት ማእከሎች የሚኖሩበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት በመለየት በአለም ጤና ድርጅት በኩል የመደገፍ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሰረት በመድሃኒት ደህንነትና ቁጥጥር ዙሪያ መሰረታዊና ከፍተኛ ስልጠናዎች ለጤና ባለሞያዎች ተሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በወረቀት ሪፖርት ቢደረግ የመድሃኒቶችን የጎንዮሽ ክስተቶች ሪፖርት ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ አዲስ የኤሌክትሮኒክና የሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሪፖርት ለማድረግ የአለም ጤና ድርጅት ከእንግሊዝ የመድሃኒትና የጤና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ /MHRA/ ጋር በመሆን ቴክኖሎጂው እንዲዘጋጅና እንዲተገበር ተደርጓል፡፡
በቀጣይም መተግበሪያዎቹን በሚመለከት እታች ወርዶ ለጤና ባለሞያዎችና ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ መሰራት ይኖርበታል፡፡ መተግበሪያዎቹ ስራ ላይ እንዲውሉም የአለም ጤና ድርጅት ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የመድሃኒት ደህንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ እንደሚገልፁት፤ መተግበሪያዎቹን ጥቅም ላይ ከማዋል በፊት በቅድሚያ የመድሃኒት ጥራትና የደህንነት ችግሮችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም መድሃኒቶች ወደሃገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ጥራታቸውንና ደህንነታቸውን መለየት ይገባል፡፡ ይህም ቦታው ድረስ በመሄድ መድሃኒቶች በአግባቡ መመረታቸውን ማረጋገጥን ይጨምራል፡፡
ወደሃገር ውስጥ ከገቡ በኋላም በአየር ማረፊያዎች ላይ የናሙና ምርመራ ይደረጋል፡፡ ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ ሲውሉም ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸውን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል፡፡ ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላም መድሃኒቱ ታማሚዎች እንዲወስዱት ይደረጋል:: መድሃኒቶች ጥቅም ላይ ሲውሉ ምን አይነት የጥራትና የደህንነት ችግሮች እንዳሉባቸው ለማጥናት በባለስልጣኑ በኩል ስርአት ተዘርግቷል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ከመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶች ጋር በተያያዘ የተዘረጋው አዲሱ የሪፖርት ሰርአት ሁሉንም የጤና ተቋማት ያመካለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም ስርአቱ ተዘርግቶ የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶች ሪፖርት ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና የሪፖርት ስርአቱ የሚጠበቀውን ያህል ውጤትና፣ መጠን ማምጣት አልቻለም፡፡ በመሆኑም የሪፖርት ስርአቱ በደምብ ቢሰራበት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በመታመኑ አዲስ የኤሌክትሮኒክ ሪፖርት ዘዴና የሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያን ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ውጤቶች ሲመጡ ስርአቱን የማሻሻል ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ በሂደትም የመድሃኒቶችን ደህንነት ስርአት ከቲቢ፣ ከኤች አይቪ ና ከወባ ፕሮግራሞች ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ይህም ለህክምናው መሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ የስርአቱን ተደራሽነት በሚመለከት አሁንም ችግሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ተጨማሪ አማራጮችን በመጨመር ወደ ክልሎችም ጭምር ይበልጥ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሄራን ገርባ እንደሚያብራሩት፤ ባለስልጣኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን መካከል አንዱ መድሃኒቶች ወደ ሃገር ውስጥ ከመግባታቸው እና ወደ ገበያ ከመሰራጨታቸው በፊት እንዲሁም በሃገር ውስጥ ተመርተው አገልግሎት ላይ ከመዋላቸው በፊት ደህንነታቸውን፣ ፈዋሽነታቸውንና ጥራታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ባለስልጣኑ የመድሃኒቶችን ደህንነት፣ ፈዋሽነትና ጥራት እንዲሁም አግባባዊ የአመራረት ስርአት ላይ ኢንስፔክሽን በማካሄድ መድሃኒቶች የሚመረቱባቸው ሳይንሳዊ ጥናቶች በዶክመንት ተዘጋጅተው ዶክመንቱን የአለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በመገምገም የጥራት ምርመራ ያደርጋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ባለስልጣኑ የመድሃኒቶችን ደህንነት፣ ፈዋሽነትና ጥራት በዚህ ሁሉ መንገድ ካረጋገጠ በኋላ ገበያውን አልፈው የሚገቡ መድሃኒቶች ላይ የደህንነት ክትትል ይደረጋል:: መድሃኒት በራሱ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትልና ከመድሃኒቱ ጋር በተያያዘ የጎንዮሽ ክስተቶች ሊታዩበት ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በታካሚው ላይ ምንም አይነት ችግር ሳይፈጥሩ ተለምዷዊ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡ ፡ ይሁንና ከዚህ በዘለለ አላስፈላጊ የሆኑና አንዳንዴም መድሃኒቱን አስከማቋረጥ ድረስ የሚያደርሱ ክስተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲከሰቱም በየደረጃው ያሉ የጤና ባለሞያዎች ለተቆጣጣሪው ተቋም ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ ከዚህ በፊት ከመድሃኒት አጠቃቀምና አወሳሰድ ጋራ የሚፈጠሩ ስህተቶችና የመድሃኒት አላስፈላጊ የሆኑ ክስተቶችን እንዲሁም መድሃኒቶች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ የሚታዩ የጥራት ጉድለቶች ካሉ የቢጫ ወረቀት ፎርምንና የነፃ የስልክ ጥሪን በመጠቀም የጤና ባለሞያዎች ለባለስልጣኑ ሪፖርት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: በዚህ ሪፖርት ስርአትም ወደ ባለስልጣኑ የሚደርሱ ሪፖርቶች ቁጥር አነስተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ሲል የነበረው የሪፖርት ስርአት ጊዜ የሚፈጅና ቀልጣፋ አለመሆኑን በጥናት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ይህንንም መነሻ በማድረግ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር አዲስ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ የሪፖርት ስርአት መከተል አስፈልጓል፡፡ ይህም በተለይ የጤና ባለሞያዎች የሚያጋጥሟቸውን የመድሃኒት የጎንዮሽ ክስተቶችን በሞባይላቸው አማካኝነት የመተግበሪያ አፕሊኬሽኑን በመጠቀም በቀላሉ ለባለስልጣኑ ሪፖርት ለማድረግ ያስችላቸዋል፡፡
መተግበሪያው ስራ ላይ ሲውልም ከዚህ የበለጠ ማስተዋወቅና ግንዛቤ ማስረፅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን መሰረት አድርገው በሚመጡ ሪፖርቶች ላይም አግባባዊ የሆነ ርምጃ በመውሰድ ወደትግበራ መግባት ይጠበቃል፡፡ በቀጣይም ህብረተሰቡ ከመድሃኒቶች ጋር በተያያዘ የጎንዮሽ ክስተቶች ሲያጋጥሙት ራሱ ሪፖርት የሚያደርግበትን ስርአት ለመዘርጋት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
የጤና ተቋማት የመድሃኒት
የጎንዮሽ ክስተቶችን ሪፖርት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ
/E-reporting/ እና በሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያ /medsafety/ በቅርቡ ማስተዋወቁ ይታወሳል፡፡ አዲሱ የሪፖርት ስርአት
ኮምፒዩተርንና የሞባይል ስልኮችን በመጠቀም በባለስልጣኑ ድረገፅ አማካኝነት ክስተቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመላክ እንደሚያስችልና
ባለስልጣኑ የሚፈልገውን የሪፖርት ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ታምኖበታል፡፡
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2012
አስናቀ ፀጋዬ